
‹‹ዊንጌት መድሃኒዓለም አስኮ… ዊንጌት አዲስ ሰፈር አስኮ …›› በየቀኑ የምሰማውና የምኖርበት ሰፈር ረዳቶች ከአፋቸው የማይነጥሉት ቃል ነው።
ሦስት እንቁጣጣሽ በኪራይ ቤት አሳልፌያለሁ፤ ልክ እንደ አብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ ሁሉ የራስ ቤት መኖር አለመኖር ብዙም አያስጨንቀኝም። (ባገኝ እጠላለሁ ማለቴ ግን አይደለም)። ባሳለፍኳቸው ኪራይ ቤት የመኖር ዓመታት ሦስት ያህል ቤቶችን ለማየት ታድያለሁ። ሦስት ጊዜ ለቀያየርኩት የሥራ ቦታ ስል፤ ከፈረንሳይ-ራስ ደስታ፣ ከራስ ደስታ ፍላሚንጎ እንዲሁም ከአዲስ ሰፈር አስኮ አራት ኪሎ መንገዶችን ደጋግሜ ተገልግዬባቸዋለሁ። በእነዚህ ጊዜያት በርከት የሚሉ አጋጣሚዎችን ተቋድሻለሁ። ይገርማል፤ አይ ጊዜ።
የመንግሥት መሥርያ ቤት ሠራተኛ በመሆኔ ለትራንስፖርት ሲባል የሰማያዊውን መኪና (ፐብሊክ ሰርቪስ) መታወቂያ ቢሰጠኝም ብዙ ጊዜ በቤቴ ርቀትና በራሴም ስንፍና ምክንያት ግን ሰርቪሱ ያመልጠኛል። እናም የታክሲ ቋሚ ተሰላፊ ነኝ።
በጣም ረዣዥምና አሰልቺ የታክሲ ጥበቃ ሰልፎችንም የህይወቴ አካል ሆነዋል። ብዙ አይነት የትራንስፖርት አይነቶችን ተጠቃሚ መሆን ደሞ ግዴታዬ እንደሆነ አምናለሁ።
ዛሬም እንደ ሰሞኑ ሁሉ ከቢሮ አምሽቼ ወጥቼ እልህ አስጨራሽ ሰልፍ ላለመሰለፍ ስል ሐይገር ባስ ሲመጣ ታክሲ ምን አስጠበቀኝ ብዬ ከባሻገር ላለው ረጅም ሰልፍ ጀርባዬን ሰጥቼ ወደ ውስጥ ገባሁ። ባሱ ውስጥ ብዙ ሰው አልገባም።
ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ከጎኔ አንዲት ጎልማሳ ሴት መጥተው ተቀመጡ። ጎልማሳዋ በጥቁርና በነጭ የተዋበ፣ ጉራማይሌ የሆነ ገብስማ ፀጉር አላቸው፤ የእድሜያቸው ጀንበር የዘቀዘቀ ቢመስልም ከመሰሉት በተቃራኒው በጣም ንቁ ናቸው።
‹‹አቤት የዚህ ዘመን ልጆች ስንፍና ግን›› አሉና አናገሩኝ ‹‹እማ›› አልኳቸው ደንገጥ ብዬ አዎም አይደለምም ሳይሉ ወሬያቸውን ቀጠሉ ‹‹የናንተ ዘመን ደሞ የባሰበት ነው፤ ሰው እንዴት ከፒያሳ አራት ኪሎ፤ ከአራት ኪሎ ስድስት ኪሎ፤ ከስድስት ኪሎ አምስት ኪሎና መሰል ቦታዎች ለመሄድ የታክሲ ሰልፍ ይጠብቃል? እንዴትስ ለአምስት ደቂቃ መንገድ ብዙ ሰዓት ይቆማል?›› አሉኝ።
‹‹ሰልፍ ቢኖርም እኮ ቶሎ ቶሎ ታክሲ ይመጣል›› ብዬ መከላከያ ቢጤ ቃል ከአፌ ወጣች።
እስክጨርስ ራሱ አልጠበቁም
‹‹በተዘጋጋ መንገድ በታክሲ ከመሄድ እኮ በእግር ላፍ ላፍ ብሎ መሄድ ይሻላል፤ በዚያ ላይ እኔ ይሄን አልኩ እንጂ ሩቅ ሂያጆቹስ ቢሆኑ ሸገር፣ ሐይገር፣ አንበሳ፣ እንዲሁም ፐብሊክ ባሶች እነሱ ወደሚሄዱበት መንገድ ለመሄድ አፋቸውን ከፍተው እየጠበቋቸው አይደል እንዴ በጠነዛ ሰዓት ያውም አናት በሚተረትር ፀሐይ ላይ ተንቃቅተው ለደቂቃዎች ብሎም ለሰዓታት ተሰልፈው የሚቆዩት!›› አሉኝ አይደለም የሚል ሞራል ምክንያቱም ከሚያወሩት ወሬ መሐል ሐሰት አላገኘሁበትምና!
ጎልማሳዋ በስሜት ማውራት ይዘዋል፤
‹‹እኛ ድሮ ከቃሊቲ ስድስት ኪሎ የሚያህልና ከእዛም በእጥፍ የሚበልጥ መንገድ በእግራችን እንሄድ ነበር፤ ያም ይመስለኛል አሁን ሙሉ በሙሉ ጤነኛ ለመሆን የቻልኩት፤ ስኳር የለ የደም ግፊት የለ ሁሌም ሙሉ በሙሉ ጤነኛ ነኝ ራሴን እንኳ አሞኝ አያውቅ።››
‹‹በእርግጥ›› አሉ እንግዳዋ ሴት ‹‹በእርግጥ አሁን ያንን ያህል መንገድ በእግር ለመሄድ በህንፃ፣ በህዝብ ብዛትና በየቀኑ የህዝብ ቁጥራችንን ሌት ተቀን ሳይታክቱ በሚቀንሱት ብዙ ባለ አደጋ መኪናዎች ባሉበትና በሌሎቹም ጊዜ በራሱ መስፈርት በሚያመጣቸው መጣደፎች ምክንያት አሁን ሰው ሁሉ ያንን ያህል በእግሩ መሄድ ላይጠበቅበት ይችል ይሆናል። ግን ቢያንስ ታክሲ ለመጠበቅ ብሎ ግን ሰዓት ማባከን የለበትም።
‹‹እኔ አሁን በአንድ ድርጅት የፀሐፊነት ሥራ ነው የምሠራው ቀኑን ሙሉ ከመጻፊያ መሳሪያዬ ጋር ተፋጥጬና ተቀምጬ ስለምውል በቻልኩት መጠን በቀን የተወሰነ ጊዜ በእግሬ እሄዳለሁ፤ ሁሌም ከሥራ ቦታዬ የአንድ ታክሲ መንገድ ያህል ጠዋት ከቤቴም የዛኑ ያህል እጓዛለሁ። ታክሲ መያዣዬ ላይ ስደርስ ሰው ሁሉ ታክሲ ለመጠበቅ ሲንቃቃ ዓይና ይገርመኛል። እኔ እናትሽ ባዶ ሆኖ ያገኘሁትን ባስ ውስጥ አፈፍ ብዬ ግብት እላለሁ።
‹‹ብዙ ጊዜ ይሄ ያንቺ ዘመን ወጣት ባሱ ከሞላ መቆም ይደክማል ይልልሻል። ሰልፍ ሲጠብቁ መቆምስ አይደክም ያለው ማነው?›› አሉና ‹‹ጨምረው ደግሞ ካስፈለገ እየሄዱ መቆም አይሻልም ወይ?›› ብለው እኔን የጠየቁኝን ጥያቄ ራሳቸው መልሰው ‹‹ምንም ጥያቄ የለውም ቆሞ ከመቅረት ቆሞም ቢሆን መጓዝ ይሻላል፤›› አሉ።
ብዙ ጥሩ ወሬዎችን አውርተን የእድሜ ልምዳ ቸውን እያካፈሉኝ ሳናውቀው እሳቸው ከኔ መውረጃ ቦታ ቀድመው ወረዱ።
የእንግዳዋን ሴት ንግግር እንደ ቡና እየተጋትኩ ቤቴ ደረስኩ፤ ግን ሌላ ጊዜ ሰፈር ለመሄድ እጠቀም የነበረውን ባጃጅ ለመጠበቅ መሰለፌን ትቼ የአስር ደቂቃ የእግር መንገድ ምንም ሳይታወቀኝ ፉት ብዬ፤ እውነታቸውን ነው መቆምም የሚያምረው እየሄዱ ሲሆን ነው ለመቆም ለመቆም ማራመድ የሚችል መቆም ይበጃል።
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2012
ዳግማዊት ግርማ