ማንበብ የሚሉት ነገር ትምህርት ቤት እንደገባሁ አሳር መከራ ይሆኖብኝ ነበር፤ የትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ጨዋታውን የመንገድ ላይ ጨዋታውን እያሰብኩ ፈገግ ብልም ክፍል ስገባ ግን ፊቴ ጭፍግግ ይላል ።በአጠቃላይ ክፍል ስገባ ፊቴ የክረምት ደመና ይመስላል፤ በዚህ ምክንያት ማንበብና መማር ፀሬ ሆኑ።የአማርኛ መምህራችን የንባብ ክፍለ ጊዜ ብለው ያስነብቡን ነበርና ተራዬ እንዳይደርስ የማላደርገው የለም።ብዙውን ጊዜም ከፊት ከነበረው ቦታዬ ተነስቼ ጥግ እቀመጣለሁ። ይህም ውጣና አንብብ እንዳልባል ጭንቀት የፈጠረልኝ እልባት ነው።
እንደ ዛሬው ባይሆንም ያኔም አማኑኤል እህል በረንዳ አካባቢ ብዙ መኪኖች ይደረደራሉ።ከጀርባቸው ደግሞ በተወላገደ አጻጻፍ ማስታወቂያ ይለጠፍባቸዋል፤የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ አባቴ ወደ ትምህርት ቤት ሲወስደኝ መኪናው ላይ የተፃፈውን አንብብ ያለኝ ትዝ አለኝ፤ በትክክል ካነበብኩ እንደምሸለም ነገረኝ፤ እናም እየጨነቀኝ እና እየጠበበኝ አነበብኩት፤ “የጭንቀት አገልግሎት እንሰጣለን” ስል አነበብኩለት። ተሳቀብኝ፤ ደነገጥኩና ደግሜ እያንዳንዱን ፊደል እየቆጠርኩ አነበብኩት ፤ለካ “የጭነት አገልግሎት እንሰጣለን” ነው የሚለው፤ከማስታወቂያው በታች ደግሞ ስልክ ቁጥር አለው።
ትምህርት ቤት የምትገባው እንድታነብም ነው ፤ያነበበ ያበበ ይባላል ፤ይመረጣል። ለማንበብ መጣር አለብህ ተብዬ መመከሬን አስታውሳለሁ። “ጥራጥሬ እንሸጣለን” የሚለውን የእህል ነጋዴ ማስታወቂያ በዚሁ ጊዜ እንዳልሳሳት ተጠንቅቄ ግን ተጠራጥሬ ሳነበው ጥርጣሬ እንሸጣለን ማለቴንና አብሮአደጎቼ ሁሉ ንባቤን እያነሱ በተገናኘን ቁጥር የጨዋታ መክፈቻ አድርገው ያፌዙብኝ እንደነበር አይረሳኝም፤መሳለሚያ ክሊኒክ የሚለውን ማስታወቂያ ሳነበው መታከሚያ ክሊኒክ ማለቴን እንዲሁ። በእኔ መላምት ክሊኒክ ከተባለ ከፊት ያለው ስያሜ መታከሚያ የሚለው ቃል ነው በሚልና ተቀራራቢ ድምፅና ፊደሎች ስላላቸው ነበር። እነዚህ እንግዲህ ማስታወቂያዎችን ሳነብ የፈጠርኩዋቸው ስህተቶቼ ናቸው።የትራፊክ ደህንነት የሚለውን የትራፊክ ድህነት ብዬ ያነበብኩ ሲሆን፣ ተጠቂ የሚለውን ተጠየቂ ብዬ በክፍል አንብቤ ደግነቱ የጠየቀኝም አልነበረም።
እነዚህን መሰል እንከኖችን ተሸክሜ መራመድ እንደሌለብኝ በማመኔ ቀስ በቀስ ጋዜጦችን እና መፅሔቶችን ማንበብ ጀመርኩ ። ማንበቤ ደግሞ የንባብ ፍርሃትን እና ስህተትን አስወገደልኝ ፤አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ይወጡ የነበሩ ዜናን ጨምሮ የተለያዩ ጽሁፎችን መከታተል ጀመርኩ። የስብሃት ገብረ እግዚአብሄር እና የደራሲ መስፍን ሀብተማርያም አንዳንድ ጽሁፎችም ማንበቤ አይረሳኝም ።
ብላቴና እያለን ሳምቡሳና ብስኩት ለመብላት መሳለሚያ አካባቢ የምንገባበት ሻይ ቤት ነበር። የቡና ቤት ስዕሎችን ወግ ከማንበቤ በፊት በሻይ ቤቱ እግረመንገዴን ስዕሎቹን እያየሁ አደንቅ እና ከአጋሮቼ ጋር ጎን ለጎን ያሉትን የዱር አውሬዎችና የቤት እንስሳት ስዕሎች በማየት እናወራ ነበር ። የቤት እንስሳት በዱር አውሬዎች ፊት በኩራት ሊቆሙ እንደማይችሉ አውቃለሁ። እናም በግሌ ሳደንቅ የነበረውን ስዕል መጽሐፉን ካነበብኩት በኋላ በሻይ ቤት ገብቼ አቃቂር ሳወጣለት ፤ስዕሎቹን የሳለውም ለማጅ እንደሆነ እገምት ጀመር።
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ