መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን ከሁሉም የሚበልጥ የሰለሞን መዝሙር ማለት ነው። የሁለት ፍቅረኛሞች ንግግር ተደርጎም ይወሰዳል። የፍቅረኞች ንግግር በግጥም ነውና ምት፣ ዜማ አለው። ሰለሞን ስለ ሙሽራውና ሙሽሪት፣ ስለፈጣሪና ስለ ቤተ ክርስቲያን የዘመራቸውን 1 ሺህ 5 መዝሙሮችን ይመለከታል። ሙሽራው ልዑል እግዚአብሔርን ሲወክል ሙሽራይቱ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት። መኃልይ እንደ ለዘብና ወረብ አይነት በፍጥነት የሚዘመር ጥዑም መዝሙር ነው። መዝሙሮቹ በተለያየ ስልት ዜማ ቢደጋገሙም ያው ስለፈጣሪና ቤተ ክርስቲያን ክብር፣ ቅድስና የሚመስክሩ ናቸው። ይህ መጣጥፍ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ስለነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ያላቸውን ራዕይ፣ ተስፋና መልካም ምኞት እንዲሁም በሀገርና በወጣቱ መካከል ያለን ጥብቅ ቁርኝት ደግመው ደጋግመው የገለፁበት መልዕክት ላይ የሚያተኩር ስለሆነ ርዕሴን “ መኃልዬ መኃልዬ ዘሻውያን “ ማለትን መርጫለሁ ። ሻውያን /ሺአውያን/millennials ማለት ደግሞ፦ በፈረንጆች አቆጣጠር ከ2000 ዓ.ም ጥቂት ዘመናት ቀደም ብለው የተወለዱትንና በአሁን ዘመን ዕድሚያቸው እስከ 30ዎቹ ያሉትን ትውልዶች፣ በሌላ አነጋገር ወጣቶችን እንደሚወክል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ይገልጻል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፈው ታህሣሥ ወር በሚሊኒየም አዳራሽ ለወጣቶች የብልፅግና ፓርቲን ሲያስተዋውቁ ያስተላለፉትን መልዕክት መነሻ በማድረግ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም የጻፉትን መወድስ ለጋዜጣው በሚያመች መንገድ ላጋራችሁ ወደድሁ። እግረ መንገዴን ስለ ፕሮፌሰር ትንሽ ልበል።
ፕሮፌሰር አለማየሁ ገ/ማርያም ( አል ማርያም ) በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርስቲ፤ ሳን በርናርዲኖ የፓለቲካል ሳይንስ፣ የኮንስቲቲውሽናል ሎው፣ የጁዲሽያል ፕሮሰስና ሲቭል ራይት መምህር ናቸው። ትንታጉ ጦማሪ ! በተባ ብዕሩ ! ላለፉት 12 ዓመታት ያለመታከት፣ ያለመሰልቸት በየሳምንቱ ቢያንስ አንድ መጣጥፍ ስለፍትሕ፣ እኩልነት፣ ዴሞክራሲ፣ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ ሰላማዊ ተቃውሞ፣ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ አንድነት፣ ዘረኝነት እኩይነት፣ ሰውነት፣ ኢኮኖሚያዊ ደባ፣ ሀቅ፣ ውሸት፣ ወዘተ . ፅፈዋል። ጦምረዋል። ፁሑፎችም ደርዝ ይዘው፤ ውሃ ልኩን ጠብቀው፣ በተጠየቅ፣ በአመክንዮ፤ የሚተነትኑ፣ የሚሞግቱ፣ የሚከስቱ ስለሆኑ ላለፉት 12 ዓመታት በመደመም፣ በስስት ለተከታተልናቸው ብዙ አትርፈናል። በዚህ አጋጣሚ እነዚህን መጣጥፎች ሰንደው በመፅሐፍ አሳትመው ለትውልድ ሊያቆዯቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ። የትውልዱን ትርክት፣ ሕልም፣ ራዕይ፣ ጥሪ፣ ጩኸት፣ ግርፋት፣ ሕመም በአንድነት አንሰላስለው የያዙ ናቸውና።
ፕሮፎ በዘሐበሻ፣ በሳተናው፣ በሀፍንግተን ድረ ገፆችና በጋዜጦች መፅሔቶች ያለስስት እንደ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው በሚራቀቁበት፣ በሚጠበቡበት፣ በሚቀኙበት፣ በሚፈላሰፉበት፣ በሚሳለቁበት፣ በሚመፅቱበት እንግሊዝኛ ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ መጣጥፎችን ከውስጣቸው፣ ከልባቸው አፍልቀዋል። ከሕመማቸው፣ ከሕመማችን ቃትተዋል። አምጠዋል። በዚህም አለማቀፉ ማህበረሰብ፣ የአሜሪካ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች፣ የውጭ ሀገራት ታዋቂ ሰዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣ ፓለቲከኞች፣ መገናኛ ብዙኃን ስለ ቀዳማዊ ኢህአዴግ አገዛዝ ማንነት፣ ምንነት በውል እንዲገነዘቡ በማድረግ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ጎን እንዲቆሙ አድርገዋል። ለኢትዮጵያ ልሂቃን፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በተዘዋዋሪም ለመላው ሕዝብ የሰላማዊ ትግል ጥበብ፣ ስልት፣ ሀሳብ አስታጥቀዋል። አቀብለዋል። በሀገራችን ዳር እስከ ዳር ለተቀጣጠለው የትግል ችቦ ክብሪት ሆነዋል። የሰላማዊ ትግል ኀልዮት ገዥ ሀሳብ ሆኖ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ የማንነት፣ የዘር፣ የጎሳ፣ የሀይማኖት፣ እጥር፣ ግድግዳ ሳያግዳቸው ሀሳብ ለማቀበል በየደጆች አንኳኩተዋል። በዚህም በሕይወታቸው ላይ ተዝቶባቸዋል። ያልስማቸው ስም ተሰጥቷቸዋል። በማንነታቸው ተሰድበዋል። በጠላትነት፣ በአክራሪነት ተፈርጀዋል። አይንህ ለአፈር ተብለዋል። በዚህ ሁሉ መሀል ለአመኑበት ደረታቸውን ነፍተው፣ አንገታቸውን ቀና አድርገው በድፍረት፣ በኩራት ተመላልሰዋል። ስለኢትዮጵያ በየአደባባዩ፣ በየምክር ቤቱ፣ በየእስቱዲዎው ጮኸዋል። ተናግረዋል። አንብተዋል። አልቅሰዋል። ለዛሬዋ የተስፋ ጭላንጭል አበክረው ጥረዋል፣ ግረዋልና። ፕሮፌሰርን እገረ መንገዴን ይህን ያህል እውቅና ከሰጠኋቸው፣ ከዘከርኋቸው ወደ ዛሬው መጣጥፌ ልዝለቅ። በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጥሪ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ዲያስፓራ ትረስት ፈንድ ሊቀ መንበር ናቸው።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብልጽግና ፓርቲን ለማስተዋወቅ በሚሊኒየም አዳራሽ ለተሰበሰቡት ወጣቶች ያሰሙትን ንግግር ባዳመጥኩ ጊዜ በአእምሮዬ ውስጥ ሁለት ዓይነት ስሜቶች ተንጸባርቀዋል።
የመጀመሪያው ስሜት ወደር የሌለው ደስታ ነው።
በእኔ የህይወት ዘመን ሰላምን ከፖለቲካ በላይ፣ ስብዕናን ከጎሳ በላይ፣ ትህትናን ከዜግነት በላይ፣ ፍቅርን ከጥላቻ በላይ እና ብልጽግናን ከድህነት በላይ ለወጣቱ የሚያስተምር ኢትዮጵያዊ መሪ በፍጹም ሰምቼም አይቼም አላውቅም ይላሉ ፕሮፌሰር የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርን ሲያደንቁ።
የኢትዮጵያ ገዥዎች ህዝቦች በአገዛዛቸው እግር ስር እንዲንበረከኩ ለማድረግ ኃይልን ሲጠቀሙ ነው የማውቀው። በ1960ዎቹ አጋማሽ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣንን ላይ የተቆናጠጠው ወታደራዊው ደርግ 60 ከፍተኛ የንጉሰ ነገስቱን ባለስልጣናት በጥይት በመደብደብ አሰቃቂ ወንጀልን ፈጽሟል። በኋላም በመደብ ትግል ሰበብ “ ቀይ ሽብር በማወጅ ” ባለምጡቅ አእምሮና ባለራዕይ የነበረ አንድ ትውልድ ፈጅቷል። ወደ 500 ሺህ ገደማ የሚሆኑ ወጣቶችን ጨፍጭፏል። እንዲሁም ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች የገቡበት ሳይታወቅ ቀርቷል። በዚህም የትውልድ ክፍተት በመፈጠሩ ሀገሪቱ የወላድ መካን ሆናለች። በተመሳሳይ መልኩ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝ በጎሳ “ፌዴራሊዝም ስም” “የጎሳ ትግል” ዘመቻ በማወጅ ከደቡብ አፍሪካው የጥቂት ነጮች የበላይነት ዘረኛ አገዛዝ (አፓርታይድ) በከፋ መልኩ በ10 ሺህዎች በሚገመቱ ወጣቶች ላይ እልቂት መፈፀሙን ፕሮፌሰር ይናገራሉ ። ካለፉት 20 ወራት ወዲህ ግን ሁኔታዎች መለወጣቸውን ፕሮፌሰር ያስረዳሉ። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ወጣቱን “ አደገኛ ቦዘኔ “ ብለው ሳይፈርጁ እንደ አባት፣ እንደ ወንድም መዘከር መምከራቸው ቀደም ካሉት ገዥዎች ምን ያህል የተለዩ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ለተገነዘበው ይህ ትልቅ እምርታ ነው። ወጣቱን መጠቀሚያ ማድረግ እንደማይገባ የሚያስጠነቅቅም ነው። “…ለፖለቲከኞች ወይም ለፖለቲካ ስትሉ አትሙቱ ወይም አትግደሉ። ላመናችሁበት ስትሉ አትሙቱ ወይም አትግደሉ።
የምርጫ ድምጽ ለመስጠት የምርጫ ካርድን እንጂ ድንጋይ አትወርውሩ። እኔን ወይም ደግሞ ፓርቲዬን ካልወደዳችሁ ድምጽ በመንፈግ ቅጡን እንጂ የመንገድ ላይ ነውጥን አትፈጽሙ። ፓርቲዬ ከተሸነፈ በ24 ሰዓት ውስጥ ስልጣንን በማስረከብ ታማኝ ተፎካካሪ ሆኜ እቀጥላለሁ። ፓርቲያችሁ የሚሸነፍ ከሆነ የህዝቡን ዳኝነት መቀበል እና ለሌላ ጊዜ በሀሳብ ልዕልና ለመታገል መዘጋጀት እንጂ አትሙቱ።
የእኛ ችግር የማንነት እና የጎሳ ፖለቲካ አይደለም። የእኛ ችግር ድህነት ነው። የእኛ ችግር የብልጽግና እጥረት ነው። የእኛ ችግር የሌሎችን ስሜት መገንዘብ አለመቻል ነው። እኛ የወንድሞቻችን እና የእህቶቻችን ጠባቂዎች እንጂ አሳሪዎች፣ ገራፊዎች እና አሰቃዮች አይደለንም። የጎሳ እና የኃይማኖት ጽንፈኝነትን በመጠቀም ስልጣንን በኃይል በመንጠቅ ህዝብን ከፋፍሎ የመግዛት አባዜ ጊዜው አልፎበታል።
ብልጽግና የአእምሮ ውጤት ሲሆን ድህነት ደግሞ የጉልበት እና የእብሪት ውጤት ነው። ያሰባችሁትን ነው የምትሆኑት። ምንጊዜም እራሳችሁን በድህነት ውስጥ የምትኖሩ አድርጋችሁ ከቆጠራችሁ ብልጽግናን በፍጹም ልትጎናጸፉ አትችሉም። ጥላቻን የምታስቡ ከሆነ ጥላቻን ቀፍቃፊ ትሆናላችሁ። ፍቅርን የምታስቡ ከሆነ አፍቃሪዎች ትሆናላችሁ። አሉታዊ ሀሳቦች አሉታዊ ድርጊቶችን ይወልዳሉ። አዎንታዊ ሀሳቦች አዎንታዊ ድርጊቶችን ይወልዳሉ። አሉታዊ ኃይል አቅመቢስ ያደርጋል። አዎንታዊ ኃይል አቅምን ያጎለብታል። ፍርሀት ድርጊት አልባ እና አለመለወጥን ይወልዳል። ድፍረት ድርጊትን እና ለውጥን ይወልዳል።
በመጨረሻም ሁላችንም የምናስበውን እንሆናለን።
ለመፍትሄዎች አስቡ። መፍትሄዎችን አሰላስሉ። በችግሮች ውስጥ አትዋኙ።
ብልጽግናን ለመጎናጸፍ ጠንክራችሁ ስሩ። ብልጽግናን ተመኙ። ብልጽግናን አልሙ። ለብልጽግና ተስፋ አድርጉ። ከድህነት ጋር ጓደኛ አትሁኑ ወደ ቁልቁለት ይወስዳችኋል። እናም በቁልቁለት መንገድ እንድትዘልቁ ያደርጋችኋል።
የአእምሮ ድህነት አለ። ጥላቻን የሚያራግቡ እና ኃይልን የሚጠቀሙ የአእምሮ በሽተኞች ናቸው። የመንፈስ ድህነትን አስወግዱ። እምነት የሌላቸው ሰዎች እምነታቸውን ወደ ገሀነም ይመራሉ።
በማንነታችሁ፣ በጎሳችሁ ወይም በዜግነታችሁ ምክንያት ለሃያ ዓመታት የምርኮኝነት አስተሳሰብ ስሜት እንዲሰማችሁ ስትማሩ ቆይታችኋል። እናንተ አሸናፊዎች እንጂ ምርኮኞች አይደላችሁም። እናንተ ድል አድራጊዎች የእጣ ፋንታችሁ መሪ መርከበኞች ናችሁ። የተሸናፊነትን ስሜት እያራመዳችሁ አሸናፊዎች ልትሆኑ አትችሉም። ሁልጊዜ ሁሉም ነገር ይቻላል የሚል አመለካከትን ያዙ። በጠንካራው የመደመር መሳሪያ በመታገዝ የጋራ ጠላት የሆነውን ድህነትን ተዋጉ። …” ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በምሳሌዊ አነጋገርም ወጣቱን እንደሚከተለው መክረዋል። ዘክረዋል።
“ በእያንዳንዱ ሰው ህልውና ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ተኩላዎች አሉ። አንደኛው ለሌሎች ሰዎች ጥረት እና ስራ ዋጋ የማይሰጥና የሚያጠለሽ በጥላቻ፣ በአድሏዊነት እና በመሳሰሉት እኩይ ምግባሮች የተሞላ መጥፎ ተኩላ ነው። ሰነፍ ነው፣ ሌሎች ጠንክረው የሚሰሩትን ሰዎች ስም ያጠፋል፣ ያጠለሻል። ይዋሻል፣ ይሰርቃል፣ ያጭበረብራል። እጅግ በጣም ስግብግብ እና እራስ ወዳድ ነው። ሌላኛው ተኩላ ደግሞ እውነት የሚናገር፣ ጠንክሮ የሚሰራ እና ጎረቤቱን የሚወድ እንዲሁም ለሌሎችም ይቅርታን ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነ ፍጡር ነው። ታሪክን በሚገባ የተገነዘበ እና መደመርን በመተግበር ብልጽግናን ለማምጣት ጥረት የሚያደርግ መልካም ተኩላ ነው። ከሁለቱ ተኩላዎች የትኛው ያሸንፋል ብላችሁ ብትጠይቁ መልሱ በገፍ እና በብዛት የተቀለበው ቅልብ ተኩላ የሚል ይሆናል። ለመጥፎው ተኩላ ምቀኝነትን፣ ሌብነትን እና ጥላቻን የምትቀልቡት ከሆነ እጅግ በጣም እያደገ ይሄድ እና መልካሙን ተኩላ ይውጠዋል፣ ይሰለቅጠዋል። ሆኖም ግን ለመልካሙ ተኩላ እውነትን፣ ታማኝነትን፣ መልካም አመለካከትን እና ለጋስነትን የምትመግቡት ከሆነ አጅግ በጣም እየገዘፈ ይሄድ እና መጥፎውን ተኩላ ይውጠዋል፣ ይሰለቅጠዋል።
ስለሆነም ምርጫው የእናንተው ነው። መልካምም ይሁን መጥፎ በእራሳችሁ ላይ የሚያድገውን እና በእናንተ ላይ ብቻ ተወስኖ የማይቀረውን ተኩላ ተጠንቀቁ። መጥፎው ተኩላ እናንተን እና በእናንተ ዙሪያ ያሉትን ሁሉ ይበላል። መልካሙ ተኩላ የሚያሸንፍ ከሆነ ደግሞ በዙሪያችሁ ፍቅርን፣ መልካምነትን እና ይቅርባይነትን ያስፋፋል። ስለሆነም ወጣቶች የእውቀት ኃይላችሁን በመጠቀም መልካም ነገርን ለመስራት እንድትችሉ ፈጣሪ ልቦቻችሁን እና አእምሯችሁን ያብራላችሁ። “ አሜ ን ።
እንደ መቋጫ
ሀገራችን የብላቴናዎች፣ የወጣቶች፣ የሻውያን፣ የሺአውያን ምድር ናት ። ከሕዝቧ 70 በመቶ ወጣት ነው። ይህ ባለሁለት ስለት ሰይፍ ነው። በአግባቡ ከተጠቀምንበት ድህነትን፣ ኋላ ቀርነትን፣ ዘረኝነትን፣ ጥላቻን፣ ልዩነትን፣ ሁከትን፣ ብጥብጥን፣ ቀውስን..፤ ቀነጣጥሶ ይጥላል። በአግባቡ ከተጠቀምንበት ፀጋ ነው። በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ደግሞ ህልምን፣ ርእይን፣ ተስፋን፣ እድገትን፣ ብልፅግናን፣ ሰላምን፣ እርቅን፣ አብሮነትን፣ ዴሞክራሲን፣ ፍትሕን፣ ሀገርን …፤ ይመነጥራል። በአግባቡ ካልተጠቀምንበት መርገም ይሆናል።
ይህ የህብረተሰብ ክፍል በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊ እና ፓለቲካዊ ጉዳይ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረለት ለሀገራችን ሁለንተናዊ ብልፅግና፣ ሰላም እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የማይተካ ሚና ይኖረዋል። በአንጻሩ ወጣቱ ተገቢውን ዙሪያ መለስ ትኩረት ካላገኘ፤ የስራ እድል ካልተፈጠረለት፣ በፓለቲካው በልኩ እንዲሳተፈ እድል ካልተፈጠረለት፤ ሰብዕናው በስነ ምግባር ካልታነፀ፤ በዚች ሀገር ላይ ተስፋ እንዲኖረው ካልተደረገ፤ በስሜት ሳይሆን በምክንያት የሚወስንበት ክህሎት ካላገኘ፤ ተቀራርቦ በመነጋገር በመቀባበልና ይቅር በመባባል እንዲያምን ቀጣይነትን ያለው እገዛ ካላገኘ፤ ስለሀገሪቱ መጻኢ እድል ተስፋን መሰነቅ ይቸግራል።
የፓሊሲዎቻችን፣ የፓለቲካችን፣ የኢኮኖሚያችን፣ የደህንነታችን፣ የህልውናችን …፤ ማጠንጠኛ፣ አስኳል ወጣቱ ሊሆን ይገባል። 70 በመቶ የሚሆነውን የህብረተሰብ ክፍል የዘነጋ ፓሊሲ፣ እቅድ፣ ብልፅግና፣ ዴሞክራሲ፣ የሕግ የበላይነት፣ እርቅ፣ ሰላም፣ ምርጫ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩንኬሽን ቴክኖሎጂ …፤ አንድ ጋት ፈቀቅ አይልም። ስለወጣቱ ስትራቴጂካዊ፣ መዋቅራዊና ተቋማዊ በሆነ አግባብ በሰከነ ሁኔታ ተንትኖ መፍትሔ ይዞ መቅረብ ግድ ይላል።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !
አሜን ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
(ሞሼ ዳያን)