አቧራማውን ጥርጊያ መንገድ አልፈው ከመንደሩ መሀል ሲደርሱ ያልተበረዘው ነፋሻ አየር ይቀበልዎታል። ይህኔ የደከመ አካል በርትቶ በአዲስ ሀይል ይታደሳል። ዓይኖችም ውብ ተፈጥሮ ይቃኛሉ። በዚህ ስፍራ የተለየ ውበት አለ። የገጠሩ ባህልና ወግ የአካባቢው መለያ ነው። ንግግሩ፣ ጨዋታውና ለዛው ከመሀል አገር ይለያል።
አሁን ከከተማው ግርግርና ከመኪኖች ጭስ ሽታ ርቀናል። ከአዲስ አበባ ተነስተን፤ የአባይ በርሀን አቋርጠን 265 ኪሎ ሜትሮች ርቀናል። ከብቶች በሜዳ ከተሰማሩበት፣ ልጆች በሜዳ ከሚቦርቁበት፣ ማርና እሸት ተቆርጦ የእህል ክምር ከሚቆጠርበት የገጠር መንደር ደርሰናል። ከምስራቅ ጎጃሟ ብቸና ሸበል በረንታ ወረዳ፤ «የዕድ ውሀ» ከተማን አልፈን፤ «የጁ ባይሌ» ቀበሌ ስንገባ እንግድነታችንን የገመተው አገሬ በአክብሮት ተቀብሎ አስተናገደን።
አለፍ አለፍ ብለው የሚታዩ ቤቶች የአጥራቸው ውበት ልዩ ነው። ከጥቁር ድንጋይ ተጠርበው በወጉ የታጠሩ ግቢዎች የባለሙያውን እጅ ያስመሰግናሉ። ደማቋ ጸሀይ በአናት ዘልቃ ለመግባት እየበረታች ቢሆንም ነፋሻማው አየር በቀላሉ እጅ አልሰጠም። እያረፈ በተነሳ ቁጥር የደከመውን ማበርታት ይዟል።
ከአርሶ አደር መንበሩ ዳምጤ ቤት ደርሰናል። የከተሜ መኖሪያ ከሚመስለው ሳሎናቸው አጎዛ ተነጥፎልን አረፍ እንዳልን ነው። የተቀመጥንበት መደብ ይመቻል። የቤታቸው አያያዝ አስገራሚ ነው። በወጉ እበት የተለቀለቀው መሬት ከሲሚንቶ ወለል ያስንቃል። የግርግዳው ቀለም ለጌጥ ከተሰቀሉ ስፌቶች ጋር ተዳምሮ የቤቱን ድምቀት ጨምሮታል። የመጋረጃውን ውበት፣ የቤቱን አያያዝና ንጽህና ሳያደንቁ ማለፍ አይቻልም።
የመኝታ ክፍሉ ጽዳት ይማርካል። ጎላ ብሎ የሚታየው አልጋ በክር በተዘጋጀ የእጅ ስራ ተውቧል። የሳሎኑ በርና መስኮቶች በብረትና በመስታወት መሰራታቸው አካባቢው ፍጹም የከተማ እንዲመስል አድርጎታል። በእርግጥ የምንገኘው በገጠር ነው። ልዩ ስሙ «ጌዲዮን» ከተባለ ጎጥ፤
ዓይኖቼን ከግርግዳው አልነቀልኩም። መደዳውን የተደረደሩ ፎቶግራፎች ትኩረቴን ስበውታል። በስርአቱ ከተሰቀሉት ፎቶዎች መሀል የልጆቻቸውን ለይቻለሁ። ሁሉም ከዩኒቨርሲቲ በተመረቁበት ልብስ ይታያሉ። በአንድ ጥግ የተቀመጠው ዘመናዊ ብፌ በማራኪ ዕቃዎች ታጅቧል። ንጽህናው በመጠበቁ በአቧራ አልቆሸሸም።
ቀና ሲሉ ከጣራው ዝቅ ብሎ የተሰቀለው የሶላር መብራት ይታያል። ምሽት ላይ በዚህ እልፍኝ ጨለማ ይሉት ነገር አይታሰብም። ጭስ አልባው የባዮ ጋዝ ምድጃም ያሻን ቢሰሩበት ምቹ ነው። ከግቢው መሀል በተቆፈረው ጉድጓድ የከብቶች እዳሪ እየተብላላ በቀጭኑ ቱቦ ወደቤት ይደርሳል። ሻይ ለማፍላት፤ ወጥ ለመስራትና ሌላውንም ለማብሰል በቀላል መንገድ ተዘጋጅቷል።
የእመት ማናህሎሽ ታዬ ማጀት ቤት ያፈራውን በረከት እንደያዘ በጎንዮሽ ይታያል። የእንጀራው ሌማት ሙሉ ነው። የጤፉ ጉሽጉሽት/ጎታ ሙሉ ነው። በወጉ የተሰናዳው ጓዳ በሸክላና በብረት ድስቶች፣ በእንስራና በቤት ዕቃዎች ተሞልቷል። የባለሙያዋ እማወራ እጅ የዋለበት ጉሽ ጠላ ከክዳኑ አምልጦ ለአፍንጫ ይደርሳል። ቤቱ የመልካም ወጥና የትኩስ እንጀራ ሽታ እየናኘበት ነው።
ወይዘሮዋ የዛሬውን መልካም ኑሮ ሲያስቡት የትናንቱን ድካማቸውን አይረሱም። አሁን በሳቸው ጎጆና በልጆቻቸው ህይወት ለውጥ ተገኝቷል። እሳቸው ስምንት ልጆች ወልደው ሲያሳድጉ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። ከአንዲት የገጠር ሴት የሚጠበቁ ከባድ ግዴታዎች ሁሉ አልቀሩላቸውም። የዛኔ በንጽህና ጉድለትና በጭስ ጉዳት ሳቢያ ለትራኮማ ህመም መዳረግ የተለመደ ነበር። የማህበረሰቡ ግንዛቤ ማነስም ብዙዎችን ለከፋ ችግር ዳርጓል። ዛሬ ግን ልጆቻቸው እሳቸው ባለፉበት አስቸጋሪ መንገድ እንዳይጓዙ የበኩላቸውን አድርገዋል። እነሱንም ለማስተማር ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል። አሁን ሁሉም በተማሩበት የሙያ መስክ በስራ ላይ ይገኛሉ። በትምህርት ላይ ያሉት ደግሞ ምሽት በሶላር ብርሀን ያጠናሉ።
ምግባቸውንም በጭስ አልባውና ማገዶ ቆጣቢው ባዮጋዝ ያበስላሉ፤ መኝታ ቤታቸው ለብቻ ነው። ለማንበቢያ የሚሆን ክፍልም ለይተዋል።
ማናህሎሽ እንደሚሉት፤ ለዚህ ለውጥ መገኘት ዋንኛው ምክንያት በአካባቢው መለመድ የጀመረው የጤና ኤክስቴንሽን ድጋፍ ነው። በዚህ ሂደት የአካባቢው ነዋሪ ህይወት ተለውጧል። ህብረተሰቡ በመጸዳጃ ቤቶች አጠቃቀም፣ በቤት አያያዝና በምግብ ዝግጅት ያዳበረው ግንዛቤ ከፍተኛ ነው። ዛሬ ከብቶችና ሰዎች በአንድ አያድሩም። የእህል ማከማቻና የዕቃዎች ማስቀመጫም በወጉ ተለይቷል።
በባህርዛፍ በተከበበው ነፋሻማ ግቢ ጎንበስ ቀና የሚሉት የቤቱ አባወራ አርሶአደር መንበሩ በጤና ኤክስቴንሽን የተገኘውን ለውጥ ከህብረተሰቡ እፎይታ ጋር ይመዝኑታል። ዛሬ በአካባቢው የጤና ባለሙያዎች መኖር የአኗኗር ዘይቤያቸውን ጭምር አዘምኖታል። እንደ አርሶአደር መንበሩ አባባል፤ ቀድሞ በቤተሰብ ምጣኔ፣ በንጽህና አጠባበቅና በቤት አያያዝ ምንም ግንዛቤ አልነበረም። የመጸዳጃ ቤቶችና የከብቶች ማደሪያ ባለመለየታቸውም ህብረተሰቡ ለህመም ሲዳረግ ቆይቷል። ለቲቢ፣ ለወባና መሰል በሽታዎች የነበረው ቅድመ መከላከልም ደካማ ነበር።
ዛሬ ግን ይህ ሁሉ ያለፈ ታሪክ ነው። ከቤተሰቡ በዘለለ የንጽህና ጠቀሜታ ለእንስሳት ጭምር እንደሚበጅ ግንዛቤ ተገኝቷል። ከግቢ እስከ መኖሪያ ቤት አያያዝ ያለው ልማድ በጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ደግሞ ህብረተሰቡ በጤና ውሎ እንዲያድር ምክንያት ሆኗል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የሸበል በረንታ ወረዳ አስተዳደር ሀላፊ አቶ ከፍአለ አላምረው እንደሚሉት፤ በወረዳው የጤና ኤክስቴንሽንን ፕሮግራም ለማሳካት በአስራ ስምንት ቀበሌዎች የጤና ቡድን ተዋቅሯል። ሞዴል ቤተሰብ ለመፍጠር በነበረው እንቅስቃሴም 92 በመቶ ያህሉን ስኬታማ ማድረግ ተችሏል። ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው ደግሞ ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት መስራትና ግንዛቤን በማስፋት ነው።
ህብረተሰቡ የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ በተደረገው ጥረት 98 በመቶ ያህል ልምዱን ማዳበር ተችሏል። በጭስ አልባ ምድጃና በእጅ መታጠቢያ አጠቃቀም ዘዴም ውጤታማ ተሆኗል። በቆሻሻ ማስወገድ ላይ የነበረንን ልማድ ለመቀየር በተደረገው ሂደትም በሲሚንቶ የተገነባ ሽታ አልባ መገልገያ ተግባራዊ ሆኗል።
እንደ ሀላፊው ገለጻ፤ በወረዳው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተደራሽ በመደረጉ ህብረተሰቡ ጥቅሙን አውቆ እየተገለገለበት ይገኛል። በዚህ እንቅስቃሴ የወረዳና የቀበሌ አመራሩን ጨምሮ ሌሎች ሴክተሮች ተሳታፊ መሆናቸውም ለመልካም ውጤት መገኘት አስተዋጽኦ አለው።
በአሁኑ ጊዜ በሁሉም ቀበሌዎች የጤና መድህን ሽፋኑ 92 ነጥብ 3 በመቶ ደርሷል። በወረዳውም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መረጃ በሁሉም ጤና ኬላዎች ተግባራዊ ሆኗል። ከስድስቱ ጤና ጣቢያዎች አራቱ ደግሞ ለካርድ ክፍል መረጃ አገልግሎት የሚውል የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ናቸው።
ዶክተር አሸናፊ ቤዛ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ጄኔራል ናቸው። በሀገር አቀፍ ደረጃ በጤናው ዘርፍ ከተያዙ ቀዳሚ አጀንዳዎች መካከል የወረዳ ትራንስፎርሜሽን ዋነኛው መሆኑን ይገልጻሉ። የወረዳ ትራንስፎርሜሽን በህብረተሰቡ ጤና ላይ እንደማተኮሩ ፍትሀዊና ጥራት ያለው አገልግሎት ማድረስን ዓላማው ያደርጋል። እንቅስቃሴውን በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ባለው ሂደትም ከጤናው ሴክተር በዘለለ በትምህርትና በግብርና፣ በሴቶችና ህጻናት፣ እንዲሁም በፍትህና በወጣቶች አሳታፊነት የታገዘ ተግባር ያከናውናል።
የወረዳ ትራንስፎርሜሽን የህዝቡን ባለቤትነት በማረጋገጥ ላይ ያተኩራል። ከሚኒስቴር ተቋማት እስከወረዳ ባለው ሰንሰለትም ስራውን በባለቤትነት የመወጣት ባህሉ የዳበረ ነው። እስካሁንም በሀገሪቱ በሚገኙ ወረዳዎች ይህን የአሰራር ልምድ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።
ዶክተር አሸናፊ እንደሚሉት፤ አንድ ሺህ ከሚሆኑት ወረዳዎች 155 ሞዴሎችን በመለየትና ከተለዩትም የተሻለ አፈጻፀም ያላቸውን 49 ወረዳዎችን በመምረጥ የጤና ትራንስፎርሜሽኑን ያሳኩትን ለማወቅ ተችሏል። ከነዚህ ወረዳዎች መካከልም የተቀመጡትን የመመዘኛ መስፈርቶች በትክክል አሟልተው የተገኙ ስምንት መሆናቸው ተረጋግጧል።
ከስምንቱ ጠንካራ ወረዳዎች መካከል አምስቱ በአማራ ክልል የሚገኙ ሲሆን፤ የተቀሩት ሶስቱ ደግሞ በደቡብ ክልል ይገኛሉ። ከሶስቱ የአማራ ክልል ወረዳዎች አንዱ የሆነው የሸበል በረንታ ወረዳም በሀገሪቱ ለሚገኙ መሰል ወረዳዎች ሞዴልነቱን የሚያስመሰክር አፈጻጸም እንዳለው አረጋግጧል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ወረዳዎችን መሰረት አድርገው ከተከወኑት ተግባራት ባሻገር በጤና ጥበቃ በኩልም ለወረዳ ትራንስፎርሜሽን ቅድሚያ ትኩረት ይሰጣል።
የጤና መሰረተ ልማት በአግባቡ እንዲተገበር ለማስቻል የጤና ባለሙያዎችን ዕውቀት በትምህርት ለመደገፍ እየተሞከረ ነው። በጤና ኬላዎች ላይ ያለውን የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ቁጥር ለማሳደግም ጥረቱ ቀጥሏል። የጤና ኬላዎችን ግንባታ በተሻለ ዲዛይን ለማሻሻል እንቅስቃሴ መኖሩን የሚገልጹት ዶክተር አሸናፊ፤ በወረዳ የሚገኙ አመራሮችን በመለየት በጠንካራ ስልጠና ደረጃቸውን የማሳደግ ሂደት ስለመጀመሩ ይናገራሉ።
በሸበል በረንታ ወረዳ ለተመዘገበው ስኬታማ የጤና ኤክስቴንሽን ውጤት ታላቁን ሚና የተጫወቱት በየዘርፉ የሚገኙ አመራሮች ስለመሆናቸውም ይመሰክራሉ። በወረዳው ከየሴክተሩ የተቀናጀው ቡድን አካባቢያዊ ጤናን ጨምሮ በየዘርፉ ተገቢውን ግንዛቤ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል። ይህ ተሞክሮም በመላው ሀገሪቱ ዳብሮ ሌሎች ወረዳዎች የሚተገብሩት ይሆናል።
በወረዳው የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ በቂ ግንባታ አለመኖርና መሰል ችግሮች መኖራቸው ተስተውሏል። የአንዳንድ ጤና ኬላዎችም ይዞታቸው ከደረጃ በታች እንደሆነ ይታወቃል። ይህን በተመለከተ ህብረተሰቡ ባለው አቅምና ፍላጎት የጀመረው ግንባታ እንደነበር የሚገልጹት ዳይሬክተሩ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላትም በዘመናዊ መልኩ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል ይላሉ።
በተያዘው በጀት ዓመት በሀገሪቱ 155 ወረዳዎችን ሞዴል የማድረግ ስራ ይከናወናል። 200 የጤና ኬላዎችም ይገነባሉ። የጤና ኤክስቴንሽን እንቅስቃሴውን በባለቤትነት የተረከቡ ባለሙያዎችና ህብረተሰቡ በቅንጅት ሲንቀሳቀሱ መንግስትም በሚፈለገው ሁሉ ከጎናቸው ለመቆም ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ዶክተር አሸናፊ ያረጋግጣሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 1/2011