አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የሚገኙ የውሃ ተቋማት መረጃ ለመሰብሰብ የሚያግዘው ቆጠራ መጀመሩን የውሃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ቆጠራው በአገሪቱ የሚገኙት የውሃ ተቋማት የት እንደሚገኙና ለምን ያክል ሰው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ለማወቅ የሚያስችል መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
የውሃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የውሃ ተቋማት ቀደም ብሎ በተደረገ ቆጠራ 600 ሺ እንደሚደርሱ ቢገለጽም መረጃው የተሟላ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አሁን የተጀመረው ቆጠራ ግን ዘመናዊ በሆነ መንገድ የሚሠራ በመሆኑ የመረጃ ክፍተቱን እንደሚሞላ አመልክተዋል፡፡
ቆጠራው በአገሪቱ የሚገኙት የውሃ ተቋማት የት እንደሚገኙ፣ ለምን ያክል ሰው አገልግሎት እንደሚሰጡ እና ስርጭቱ ምን ያክል እንደደረሰ እንደሚያመላክት ተናግረዋል፡፡ ቆጠራው ከተጠናቀቀ በኋላ የመጠጥ ውሃ ያላገኙ አካባቢዎች መለየት እንደሚያስችልና የመስመር ብልሽቶችን በወቅቱ ለመጠገን እገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡
ለቆጠራው 3925 ታብሌቶች መዘጋጀታቸውን በመጥቀስ፤ ቆጠራው በሚካሄድባቸው ወረዳዎች አራት ሺ ቆጣሪዎችና አምስት መቶ አስተባባሪዎች ስልጠና እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ ለታብሌቶቹ ገዥ 61 ሚሊዮን ብር፣ ለቆጣሪዎቹ ክፍያ 11 ሚሊዮን ብር እንዲሁም አጠቃላይ ሥራ ማስኬጃው 100 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቁመዋል፡፡ ገንዘቡ በኢትዮጵያ መንግሥትና በአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ የተገኘ መሆኑን ተናረዋል፡፡
የውሃ ተቋማት ቆጠራው ለአስራ አምስት ቀናት የሚቆይ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ባለው የጸጥታ ችግርና የተወሰኑ ወረዳዎች ባላቸው ስፋት ቀኑ ሊራዘም እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የመቁጠሪያ ታብሌቶቹ ባትሪም ይሁን ሌላ እክል ከገጠማቸው ተቀያሪ ታብሌቶች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 1/2011
በመርድ ክፍሉ
ፎቶ፡- ሀዱሽ አብርሃ