አዲስ አበባ፡- “የፓርቲ መመስረትና መፍረስ ፌዴራሊዝምን ያጠፋዋል ወይም ይገነባዋል ብዬ አላምንም” ሲሉ የቀድሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ እና የዲቦራ ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ ተናገሩ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ተፅፎ ለንባብ የበቃው የመደመር ማዕቀፈ እሳቤ በእርሳቸው አተያይ ጥሩ አስተሳሰብ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
አቶ አባዱላ ገመዳ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንደገለፁት፤ፓርቲ ሊመሰረት አሊያም ሊፈርስ ይችላል፡፡ በመመስረቱና በመፍረሱ ግን ፌዴራሊዝምን ያጠፋዋል አሊያም ይገነባዋል ብለው አያምኑም፡፡ የቀድሞው ኢህአዴግ ሲፈጠር በመጀመሪያ የነበሩት የአሁኖቹ ህወሓት እና አዴፓ ናቸው፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች ከመተባበር ወደ ግንባር እንሂድ ብለው ሲነጋገሩ እና ኢህአዴግን ሲመሰርቱ በወቅቱ የትግራይም ሆነ የአማራ ህዝብ አልተወያየበትም፡፡
“እኛም ኦህዴድን እንመስርት ብለን ከህዝባችን ጋር አልተወያየንም፡፡ ስለዚህም መሪ ድርጅቶችን ሰዎች ይፈጥሯቸዋል፡፡” ሲሉ ጠቅሰው፤ የፓርቲ መመስረትም ሆነ መፍረስ ፌዴራሊዝምን እንደማያጠፋው አመልክተዋል:: “የፌዴራሊዝም መሰረታችን ፓርቲዎች ሳይሆኑ ህገ መንግስቱ ነው፡፡ ፌዴራሊዝም ሊጣስ የሚችለው ህገ መንግስት የሚባለው ሰነድ ሲነካ ነው፡፡
ስለዚህ ህገ መንግስታችን የፌዴራል ስርዓቱ የአገራችንን መሰረታዊ ችግሮች መፍትሄ ነው ብሎ አስቀምጧልና መፍትሄነቱን እሱ ይዞ ይቀጥላል፡፡ ፓርቲዎች ቢመሰረቱም በህገ መንግስቱ ይመራሉ እንጂ ህገ መንግስቱን አይመሩትም፡፡” ብለዋል። አያይዘውም፤ ምንም እንኳን በህገ መንግስቱ ሊሻሻሉ የሚችሉ ነገሮች ሊኖሩ ቢችሉም ትልቁ ምሰሶ ህገ መንግስቱ እንደሆነ አስረድተዋል:: ህገ መንግስቱን የሚነካ ካለ ደግሞ እርሱ እብድ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
አቶ አባዱላ፣ “የመደመር ማዕቀፈ እሳቤ እንደ እኔ አመለካከት ጥሩ አስተሳሰብ ነው ብዬ አምናለሁ:: ማዕቀፈ እሳቤውንም ደጋግሜ አንብቤዋለሁ፡፡ መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ያካተተ ነው፡፡ አንደኛ፤ ልማታዊነትን አስተካክሎ ያስቀመጠ ማዕቀፈ እሳቤ ነው፡፡ እንዲህም፤ የልማታዊ አስተሳሰብን ጉድለቶች ማለትም ኢህአዴግ ግለቱን ጠብቆ ባለመሄዱ የፈጠራቸውን ጉድለቶች አርሞ በትክክል አስቀምጧል ብዬ እገምታለሁ፡፡” ብለዋል፡፡
“ተበትኖ የትም መድረስ አይቻልም፡፡” ያሉት አቶ አባዱላ፣ “ያለን አንድ አገርና አንድ ህዝብ ነው፤ አንዱ ዘንድ ሀብት ሌላው ዘንድ እውቀት አለ፤ አንዱ ዘንድ ጉልበት ሲኖር፤ ሌላው ዘንድ ደግሞ ሌላ ነገር አለ፡፡ መደመር የሚለው ይህን ሁሉ ወደ አንድ እናምጣው ነው፡፡ የራሳችንን ብቻ ሳይሆን ከጎረቤቶቻችን ጋርም ሰላም እንፍጠር፤ ስለዚህም ማዕቀፈ እሳቤው በመደመር አንድ ላይ እንራመዳለን፤ ለውጥ እናመጣለን የሚል ነው፡፡ በመሆኑም በእኔ እምነት ትክክለኛ እሳቤ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን መቀባበል ያስፈልገዋል፡፡” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2012
አስቴር ኤልያስ