አዲስ አበባ ፡- በኢትዮጵያ በህዋ ሳይንስ የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ሳተላይት ለመገንባት የመጀመሪያው ወሳኝ ጉዳይ የሰለጠነ የሰው ሀይል ነው፡፡ የሰለጠነ የሰው ሀይል እውቀትን፣ ቴክኖሎጂን፣ ገንዘብን ገበያንና ስራን ማምጣት ይችላል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ሀይል ማሰልጠን ያስፈልጋል:: ለዚህም በሰው ሀይል ልማት ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
“ኢንስቲትዩቱ የሰው ሀይል በማብቃት ረገድ ከፕሮጀክቶቹ ጋር አብሮ በማሰልጠን፣ በትምህርት መስክ እና በሚገነባቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች፤ ለምሳሌ በኮሙኒኬሽን ማእከል ውስጥ ምን ያህል ሰው ማሰልጠን እንዳለበት በጀት በመያዝ እየሰራ ነው” የሚሉት ዶክተር ሰለሞን፤ የተወሰኑ ሰልጣኞች ውጭ ሀገር እንዲሰለጠኑ በማድረግ በተለያየ መንገድ የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት እየተሰራ ቢሆንም፤ በአንድ ጊዜ እራሱን የሚችል ባለሙያ ማፍራት አዳጋች እንደሆነ ያብራራሉ፡፡
እንደ ዶክተር ሰለሞን ማብራሪያ፤ ባለፈው ኢትዮጵያ ያመጠቀቻት ሳተላይት ስትሰራ ከፍተኛውን ድርሻ ኢትዮጵያውያን ኢንጂነሮች እንዲወስዱ በማድረግ ተጠቅማለች፡፡ ይህንን ደረጃ በደረጃ በማሳደግ ሳተላይት በማበልጸግ ሂደት ከተለያዩ ሀገራት ጋር በመተባበር፤ ኢንጂነሮችን አብሮ በማሰልጠን እስከፍጻሜው የሚያደርሱበትን አቅማቸውን፣ እውቀታቸውን በማሳደግ፣ በቀጣይ ራሳቸውን ችለው እንዲሰሩ አቅም እንዲፈጥሩ እየሰራ መሆኑን ይናገራሉ::
ዶክተር ሰለሞን አያይዘውም፤ ወደ ህዋ የመጠቀችው “ETRSS-1” የሚል መጠሪያ ያላት የኢትዮጵያ ሳተላይት ደህንነቷ ተረጋገጦ፤ ሙሉ በሙሉ በተሳካ ሁኔታ ስራ እየሰራች፣ መረጃዎች እየላከች መሆኗን ገልጸው፤ በቀጣይ ለባለድርሻ አካላት በሳተላይት መረጃ (ዳታ) አጠቃቀም ላይ ያተኮረ አጠቃላይ ማብራሪያ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል:፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2012
ወርቅነሽ ደምሰው