በአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር በየካ ክፍለ ከተማ በተገልጋይና በአገልጋይ መካከል ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ታዝበናል። አቶ ብርሃኑ ዘውዱን ጨምሮ ስድስት ሰዎች በክፍለ ከተማው የቤቶች ጽህፈት ቤት ግቢ ይወያያሉ። የመጡበትን ምክንያት ስንጠይቅም በቤት ጉዳይ አገልግሎት ፈልገው ሲሆን ለሳምንታት ተመላልሰውም አልተሳካላቸውም፡፡
አቶ ብርሃኑ የወረዳ 2 ነዋሪ ናቸው። ከወረዳ ጽህፈት ቤት እስከ ፍርድ ቤት ያለውን ሂደት ጨርሰው የጀመሩት የቤት ጉዳያቸው ወደ ክፍለ ከተማ የተላለፈ ቢሆንም፤ ክፍለ ከተማው በየቀኑ የተለያዩ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን አምጡ በማለት እያጉላላቸው እንደሚገኙ አብራርተዋል:: ተገልጋዮቹ ሥራ ፈትተው በመምጣታችው ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን በከንቱ እያባከኑ እንደሆነም በስሜት ይናገራሉ፡፡
አቶ ገብረ ኪሮስ ሳህሉ የየካ ክፍለ ከተማ የቤቶች የጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ ከተገልጋይ የሚመጡ በርካታ ቅሬታዎች መኖራቸውን በመግለፅ፤ የቢሮው ዋነኛ ሥራ ከተለያዩ ተቋማት የሚመጡ ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ማስተናገድ ሲሆን፤ ከወረዳዎች፣ ከከንቲባ ጽህፈት ቤት፣ ከተለያዩ ተቋማት፣ ከዚህ በፊት ከዋና ሥራ አስፈጻሚ ደብዳቤ የተፃፈላቸው፤ ውሳኔ የተወሰነላቸው አካላት ጉዳይ ወደ ክፍለ ከተማው እንደሚመጣና ሁሉም አካላት እንደየአመጣጣቸው እንደሚስተናገዱ ይናገራሉ።
እንደ አቶ ገብረ ኪሮስ ገለጻ፤ ስለተገልጋዮች ምልልስም ሲያስረዱ ዋናው ምክንያት ባለጉዳዮች ይዘውት የሚመጡት ጉዳይ መሆኑንና አንዳንዴም በቤት ጉዳይ ወረዳው መልስ ሳይሰጣቸው በቀጥታ ወደዚህ የሚመጡ ባለጉዳዮች መኖራቸውንም አብራርተዋል፡፡ ከወረዳው መልስ የተሰጣቸውም ቢሆኑ ስማቸው ስለተላከ ብቻ ቀጥታ ቤት የሚያገኙ መስሏቸው እንደሚመጡ ተናግረዋል፡፡
የተለቀቁ የቀበሌ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍና ባለጉዳዮችን ለማስተናገድ ወረፋ እንዳለ የሚገልፁት አቶ ገብረ ኪሮስ፤ በወረፋ ቅድሚያ የሚሰጣቸው አካላት መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ካለው የመኖሪያ ቤት ችግር አንፃር የቤት አሰጣጥ ሂደቱን ሲያስረዱም፤ ለምሳሌ በአንድ ወረዳ አስር ቤቶች ቢለቀቁ ሰባ ሰላሳ አሠራር ዘዴን በመከተል 70 በመቶ ለወረዳ፣ 30 በመቶ ለክፍለ ከተማ ቤቶች ይሰጣል፡፡ ይህ የሚሆነው ፍትሐዊ አሠራር እንዲሰፍን ለማድረግ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ ባለፈው ዓመት በርካታ ህገወጥ ተብለው የተለዩ ቤቶች ነበሩ። በዘንድሮ ዓመት ግን ህገወጥ ሆነው የተገኙና የተለቀቁ ቤቶች የሉም። ክፍለ ከተማውም ገንብቶ የሚሰጠው ቤት የለም ይላሉ። ከወረዳ ለሚመጡ ነዋሪዎች ወደ ክፍለ ከተማ የሚጻፍላቸው ለመረጃ እንጂ መስተናገድ ያለባቸው እዚያው ወረዳቸው ውስጥ በመሆኑ ተጨማሪ ወጪና ጉልበት ማውጣት የለባቸውም፡፡ ከወረዳ አቅም በላይ ከሆነና የሚያስተናግዳቸው ካጡ ግን የማናስተናግድበት ምክንያት የለም በማለት አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም፤ ከከተማ አስተዳደሩና ከኤጀንሲ የተጻፈላቸው ባለጉዳዮች ወረዳ ካሉት ምንም ገቢ ከሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በኢኮኖሚም የተሻሉ በመሆናቸው ወረፋ መጠበቅ የግድ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው ብለዋል፡፡
ወይዘሮ አልማዝ ተመስገን በዚሁ ክፍለ ከተማ አገልግሎት ፈልገው ረዝም ላለ ጊዜ የተመላለሱ ባለጉዳይ ናቸው። ይሁን እንጂ፤ በቦታው ላይ ባለሙያዎች ቶሎ ቶሎ በመቀያየራቸው ምክንያት ጉዳያቸው አሁንም እንደ አዲስ እየታየ መሆኑን ገልጸው፤ በቦታው የሚተካው ባለሙያ ደግሞ በትክክል በደንቡ እና በመመሪያው ላይ በቂ እውቀት የሌለው፤ ለመወሰን የሚቸገር ነው። በዚህም ለመመላለስና ለእንግልት ተዳርጌያለሁ ይላሉ፡፡
እንደወይዘሮ አልማዝ ከለውጡ ወዲህ ያሉ ባለሙያዎች ደግሞ ብዙም መመሪያውን አያወቁትም ለመወሰንም ይቸገራሉ፡፡ እንዲያውም ከቦታው ላይ የተነሱ ሰዎችን እንድንጠይቅ ይመሩናል ይላሉ:: ሁሉን ነገር ወደ ማዕከል በመላክ ከዚያ ምላሽ የሚፈልጉ ከመሆናቸውም በላይ አንድ ደብዳቤ ለማጻፍ አስራ አምስት ቀን የሚያመላልሱ አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ጉዳዬ መቋጫ አላገኘም በማለት አብራርተዋል፡፡
በርካታ ባለጉዳዮች በአሁኑ ወቅት እያጋጠማቸው ያለው ችግር መመሪያ ያለማወቅ፤ ውሳኔ የመስጠት፣ እንደሆነና በዚህም ባለጉዳይ የማመላለስ እና የማጉላላት መሆኑን ይጠቀሳሉ:: በጽህፈት ቤቱ አሠራር ሰኞ፣ ረቡዕና አርብ የባለጉዳይ ቀን መሆኑ ቢገለፅም አብዛኛው ሠራተኛ፣ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ቢሮ እንደማይገኙና ምልልስ እየበዛባቸው እንደሆነ በምሬት ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2012
ወርቅነሽ ደምሰው