አዲስ አበባ:- በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል የከተማ አስተዳደሩ በተጠባባቂነት ልዩ ተብለው የሚያገለግሉ 20 ፈጥኖ ደራሽ አዳዲስ አውቶቡሶችን ዛሬ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም ሊያስገባ መሆኑ ተገለፀ።
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ስምሪት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ፤ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ እስካሁን የነበረው አሰራር ተሽከርካሪዎችን ከመስመር ላይ በማዞር ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ባለበት አካባቢ እንዲሰማሩ ማድረግ እንደነበር በመግለፅ፤ አሁን ግን እነዚህ ልዩ ተብለው በተጠባባቂነት የሚገቡት 20 አዳዲስ አውቶቡሶች ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ባለበትና ሰልፍ በበዛበት በየትኛውም አካባቢ ተዘዋውሮ ለመስራት የተዘጋጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የእነዚህን አውቶቡሶች ስምሪት በዋናነት የአንበሳ አውቶቡስ ድርጅት የሚመራው ይሁን እንጂ፤ የትራንስፖርት ባለስልጣን ሊያዝበት እና በሚያመቸው መንገድ ሊጠቀምበት በሚችል አደረጃጀት የተዋቀረ ነው። ባለስልጣኑ ከመደበኛው አውቶቡሶች በተጨማሪ እነዚህን ተጠባባቂ አውቶቡሶች ህብረተሰቡ በሚሰጠው ጥቆማና ከፍተኛ ሰልፎች በሚታዩበት አካባቢ ያሰማራል ብለዋል።
እንደአቶ ዮሴፍ ገለፃ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚታየው ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር፤ በከተማ ያለው የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን ቀዳሚው ምክንያት ሲሆን፤ ሁለተኛው የመሰረተ ልማት ችግር ነው። ይህም የብዙሃን ትራንስፖርት ብቻ
የሚንቀሳቀስበት የተከለለ መንገድ ባለመኖሩ ሁሉም ተሽከርካሪዎች በተመሳሳይ መንገድ ይጓዛሉ። በዚህ ምክንያት የሚፈጠረው ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የምልልስ ጊዜውን በእጅጉ ያዘገየዋል። የትራንፖርት ስምሪት ክትትልና ቁጥጥሩ ጠንካራ ያለመሆኑና በቴክኖሎጂ ያለመደገፉም ችግሩን ከሚያባብሱት ምክንያቶች የሚጠቀሱ ናቸው።
አቶ ዮሴፍ አያይዘውም፤ በከተማዋ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር በዘላቂነት መፍታት እንዲቻል የከተማው አስተዳደር በቀጣይ 3ሺ የሚደርሱ አዳዲስ አውቶቡሶችን በቅደም ተከተል ለማስገባት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 25/2012
ፍሬህይወት አወቀ