አዲስ አበባ፡- በህገወጥ መንገድ የኢትዮጵያን ፓስፖርት ለማግኘት የሞከሩ ከ20 በላይ የጎረቤት አገራት ዜጎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ በህገወጥ መንገድ ለውጭ ዜጎች የተሰጡ 29 ፓስፖርቶችም በኤርፖርትና በኢንተርፖል ዳታ ቤዝ ውስጥ በማስገባት አገልግሎት እንዳይሰጡ መደረጉ ተጠቅሷል፡፡
የኢምግሬሽን የዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ደሳለኝ ተሬሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ከ20 በላይ የጎረቤት ሀገር ዜጎች የተለያዩ ማስረጃዎች፤ ማለትም የቀበሌ መታወቂያና የልደት ሰርተፊኬት በማቅረብ በህገወጥ መንገድ የኢትዮጵያን ፓስፖርት ለማግኘት ሲሞክሩ በኤጀንሲው ሰራተኞች ተይዘው በህግ ተጠያቂ ሆነዋል፡፡ በተለያየ ጊዜ ከደላሎችና ከኤጀንሲው ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር በህገወጥ መንገድ ለውጭ ዜጎች የተሰጡ 29 ፓስፖርቶችን በኤርፖርትና በኢንተርፖል ዳታ ቤዝ ውስጥ በማስገባት አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርጓል፡፡
በተጨማሪም፤ በፓስፖርት እና በኤርፖርት የኢሚግሬሽን አገልግሎት አሰጣጥ በተያያዘ በህገወጥ ተግባር ተሳትፈው የተገኙና የተጠረጠሩ ሁለት ሰራተኞች በህግ እንዲጠየቁ የተደረገ ሲሆን፤ ዘጠኝ ሰራተኞች ደግሞ ከስራ ታግደው ጉዳያቸው በዲስፕሊን እየታየ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሌሎች ምግባረ ብልሹ ሰራተኞችን ለመለየትና ርምጃ ለመውሰድ የማጥራት ስራ እየተሰራ መሆኑንም በመግለፅ፣ ህብረተሰቡም ህገወጥ ደላሎችና ሰራተኞች፤ እንዲሁም በህገወጥ መንገድ የኢትዮጵያን ፓስፖርት የያዙ የውጭ ዜጎች ሲመለከት በመጠቆም ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ የአፍሪካ ሀገራት ለቪዛ ጥያቄ የሚሰጡትን ምላሽና የሰዎችን ነፃ ዝውውር የማሳለጥ ተግባር የሚገኙበትን ደረጃ አስመልክቶ በሚያወጣው ሪፖርት ላይ ኢትዮጵያ ከአመታት በፊት ከነበረችበት 50ኛ ደረጃ ወደ 18ኛ ደረጃ ከፍ ብላለች፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2012
መርድ ክፍሉ