( ክፍል ሁለት )
ስለ እውነትና እርቅ በተወሳ ቁጥር ከልዑል ፈጣሪ ለጥቆ መቼም ወደ አይነ ፣ እዝነ ህሊናችን ግዘፍ ነስቶ የሚመጣው ፣ በግርማ ጮሆ የሚሰማን ኔልሰን ማንዴላ / ማዲባ/ ነው ።የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አፓርታይድ ፣ ኤፍ ደብሊው ዴክለርክ ፣ …፤ ከዚያ ይከተላሉ ።ስለ እርቅ ሲነሳ ማዲባ አብሮ ስሙ ይወሳል። ማዲባ ሲወሳ እርቅ አብሮ ይነሳል ።የእርቅ ምልክት ነው።በገዘፈው ሰብዕናው ገልጦ በተግባር አሳይቶናል። ኑሮታል ።መስክሮታል ።እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1998 የእውነትና እርቅ ኮሚሽን ያጠናቀረውን ሪፖርት ማዲባ ከሊቀ መንበሩ ቀሲስ ዴዝሞንድ ቱቱ ከተረከበ በኋላ ባስተላለፈው መልዕክት ፤
” በሕገ መንግስታችን የተደነገገውን ዴሞክራሲና ሰብዓዊነት ለመጠበቅ እርቅ ያስፈልገናል።”ብሎ ነበር። አዎ ! ተቀራርቦ መነጋገር ፣ እርቅና መግባባት ከሌለ ሰላም ሊሰፍን አይችልም ።ሰላም ከሌለ አይደለም ሰብዓዊነት፣ ዴሞክራሲ ፤ የሀገር ህልውና ላይ አደጋ መደቀኑ አይቀርም። እንደኛ በውጥረት ፣ ውሉ በጠፋ ትብታብ እና ፅንፍ በረገጠ አቋም ላይ ለምትገኝ ሀገር ተቀራርቦ መነጋገር፣ መግባባትና መታረቅ የግድ ነው ።ከወራት በኋላ ሀገር አቀፍ ምርጫ ለምታካሂድ ሀገር ደግሞ የሞት ሽረት ጉዳይ ይሆናል። ብሔራዊ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በአለቀ ሰዓት ቢሆንም የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቀራርቦ ለማነጋገርና ይቅር ለማባባል እየሰራ መሆኑን ይፋ ማድረጉ ተስፋን የሚያለመልም ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ለመሆኑ ፖለቲካዊ እርቅ Political Reconcilation ሲባል ምን ማለት ነው ?
ኮሊን መርፊ ” THE FORGIVENESS MODEL OF RECONCILIATION ” በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቃው ጹሑፉ ፤ ” ፖለቲካዊ እርቅን የተሰበረ ግንኙነት የመጠገን ሂደት ነው ።” በታሪክ ምርኮኝነት፣ ሆን ተብሎ ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲባል በተነዛ የፈጠራ ትርክት፣ በማንነት ላይ በተዋቀረው ፖለቲካ፣ በግራ ዘመም አይዶሎጂ እና በሕዝበኝነት populism በተካረረ ልዩነት፣ ቁጭት መፍጠር እንደማታገያ ስልት በመወሰዱ ፣ በሴራ ኀልዮት በተጎነቆለ ጥላቻ ፣ ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲባል በሕዝቦች መካከል በተዘራ ልዩነት፣ አንድን ሕዝብና ሃይማኖት በመለየት እንደጠላት መፈረጅ እና በሌሎች ገፊ ምክንያቶች የተነሳ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ግንኙነት እጅግ ሻክሯል።በዚህ የተነሳ የአንዳንድ ፓርቲዎች አመራሮች አይደለም ቁጭ ብሎ ለመነጋገር አይን ለአይን እንኳ ለመተያየት ፍቃደኞች አይደሉም። በአሀዳዊና ብሔራዊ ፓርቲዎች መካከል ያለ ልዩነት ፤ ከለውጡ ወዲህ ደግሞ ትህነግና ጭፍሮቹ ከብልፅግና እንዲሁም ከአንድነት ኃይሎች ጋር የገቡበት የይዋጣልንና የብሽሽቅ ፖለቲካን ይዞ ወደ ምርጫ መግባት በእንቅርት ላይ እንዲሉ አሁን ባለው ቀውስ ላይ ቤንዚን እንደመጨመር ስለሆነ ብሔራዊ የእርቀ ሰላም ኮሚሽኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቀራርቦ በማነጋገር በመሀላቸው እርቅ ለማውረድ መንቀሳቀሱ ይበል የሚያሰኝ ነው።
ኮሊን ፖለቲካዊ እርቅ ሶስት ንጣፎች layers እንዳሉት ያትታል ።የላይኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንኙነት እንዲበላሽ ያደረጉ መግፍኤዎችን መለየት፤ እነዚህን ምክንያቶች ከፍ ብዬ ለማሳየት የሞከርሁ ሲሆን ኮሚሽኑ ግን ይበልጥ ዘርዝሮ ሊተነትናቸው ይችላል ።መካከለኛው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከሚፈጠር እርቅ የሚጠበቀውን ግብ ለይቶ ማስቀመጥ ነው። የተቀመጠው ግብ ውስን ሊሆን ይገባል ።ግቡ ቀጣዩን ምርጫ ሰላማዊ ማድረግ እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያሉ ልዩነቶችን ከማባባስ መቆጠብ ሊሆን ይችላል። እንደ ብሔራዊ እርቅ ያሉ ጉዳዮች ግን ከፓርቲዎች አልፈው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩና ተዋናዮቹም በርካታ ስለሆኑ በዚህ የእርቅ ሒደት የሚካተቱ አይደሉም። የታችኛው እርቁ የሚሳካበትን ስልት መንደፍ ነው። ከፍ ሲል የተነሱትን ሁለቱ የፖለቲካዊ እርቅ ንጣፎችን በጥንቃቄ መተግበር የእርቅ ሂደቱን ውጤታማ ያደርገዋል ተብሎ ይታመናል።
ኮሊን መርፊ በማስከተል ፤ ” ፖለቲካዊ እርቅ የሕግ የበላይነትን በስምምነት በጋራ የማረጋገጥ እንጂ ይቅር የመባባል ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። በእርቅ ሂደቱ ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ መቀመጥ የለበትም።…” ብሔራዊ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሊያካሂደው ያቀደውን እርቅ ከምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ ጋር ሊያያይዘው አይገባም። የዴስቲኒ ኢትዮጵያ አባላት የሄዱበት መንገድ ለዚህ ጥሩ አብነት ነው ።በብሔራዊ የእርቀ ሰላም ኮሚሽንና በባለድርሻዎች የተቀናጀ ጥረት በብልፅግና ፣ በኢዜማ፣ በአብን ፣ በኦፌኮ ፤ በኦነግ ፣ …፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ፖለቲካዊ እርቅ ሲወርድ በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ የሕግ የበላይነትን ማክበር ላይ መግባባት ላይ ይደረሳል ማለት ነው። ደጋፊዎቻቸውም ይህን ፈለግ ይከተላሉ ተብሎ ይታመናል።ቀጣዩን ምርጫ አንጻራዊ በሆነ ሰላምና መረጋጋት ለማካሄድ አስተዋጽኦ ከማበርከቱ ባሻገር በቅድመም ሆነ በድህረ ምርጫ ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን አበክሮ በመቀነስና በመከላከል ልዩነቶች ይበልጥ እንዳይባባሱ ያግዛል ።ከዚህ ባሻገር በቀጣይ ለሚታሰበው ብሔራዊ እርቅ ጥሩ መደላድል ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል ።
ሆኖም ስለ ሰላምና ስለ ይቅርታ መነጋገር የራሱ የሆነ ሂደትና ቅደም ተከተል እንዳለው አበክሮ ማጤን ያሻል። እዚህ ላይ የሰላም ፣ የእርቅ ፣ የሽምግልና አለማቀፍ ረቡኒው እና በአሜሪካ በሀሪሰንበርግ በሚገኘው ኢስተርን መኖናይት ዩኒቨርሲቲ የአለማቀፍ ግልግልና ዕርቅ ፕሮፌሰር የሆኑት ፤ እንዲሁም በቅርብ የተቋቋመው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል ሕዝቅያስ አሰፋ ፤ ” የሰላምና እርቅ ትርጉምና መንገዶች ፤ ” በሚለው መፅሐፋቸው ፤ ያነሷቸውን ቁም ነገሮች ፤ ሰላም ፣ ዕርቅ የራሱ መንገድ እና አካሄድ እንዳለው ያሳያሉ ።
“…ሰላም ለግጭቶች መነሻ የሆኑትን ልዩነቶች በሚገባ ከለየና ከመረመረ በኋላ ልዩነቶችን ለፈጠሩት ችግሮች ሁሉን ወገኖች የሚበጁ መፍትሔዎች መፈለግ ማለት ነው።…፤ ” ገፅ 26 _ 33 ፤ ሲሉ ሰላምን ይበይኑታል። ሰላም ግጭትን ማስወገድ አይደለም ።በቀዳማይ ኢህአዴግ እንደሆነው በደህንነት ፣ በፀጥታ ኃይሉና በካንጋሮ ፍርድ ቤቶች ግጭትን ማስወገድ ይቻል ይሆናል እውነተኛውን ሰላም ግን አያረጋግጥም ።የአስቸኳይ ጊዜ አውጆ ግጭትን ተቃውሞን ፀጥ ለጥ ማድረግ ይቻል ይሆናል ዘላቂ ሰላምን ግን ማስፈን አይቻልም። ለዚህ ነው ፕሮፌሰር ሰላም ለግጭቶች መነሻ የሆኑትን መርምሮ ለሁሉም ወገኖች የሚበጅ መፍትሔ መፈለግ ነው ያሉት ።አሁን በሀገራችን የሚከሰቱ ግጭቶች ከዚህ አንጻር ማየትን ይጠይቃል ።ፕሮፌሰር ከላይ በጠቀሱት መፅሐፋቸው የሰላም ስራ የራሱ እሴቶችና መርሆዎች እንዳሉት ያመላክታሉ ።
ሀ . መሰረታዊ የግጭት መንስኤዎችን መርምሮ የአመለካከት አድማስን ማስፋት ፤
ለ . ፍትሕ ፦ዘላቂ ሰላም ያለፍትሕ ሊገኝ አይችልም። ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካው ፍትሕ ባልተረጋገጠበት ሰላምን ማምጣት አይቻልም ።ለዚህ ነው የለውጥ ኃይሉ ተቋማት ላይ እየሰራ ያለው ።
ሐ . መግባባት ፦ፕሮፌሰር መግባባትን ሲበይኑት፤ አንዱ ሌላው ውስጥ ሲገባና ሌላውም መጀመሪያው ውስጥ ሲገባ ነው ይላሉ ፤ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ መግባባትን መፍጠር የማዕዘን ድንጋይ ነው። በግጭቶች ተሳታፊ በሆኑ ኃይላት መካከል መግባባትን ለመፍጠር ደግሞ ፤ መጀመሪያ የግጭቱ አካላት፣ የሚጋጩባቸው ምክንያቶች እና መፍትሔዎች ላይ መግባባት ይጠይቃል።
መ . የህይወት መተሳሰር mutuality
ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር የሰዎች ሕይወት የተሳሰረ መሆኑን በጥልቀት መገንዘብ ፣ መረዳት ይጠይቃል። የሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎቶች ተመሳሳይ ፣ ተቀራራቢ መሆናቸውን መገንዘብ ማለት ነው ።ሰው መከበርን፣ መወደድን ፣ መደመጥን ፣ ከፍ ከፍ ማለትን እንደሚሻ
ሁሉ በተቃራኒው ውርደትን ፣ መገፋትን፣ መጠላትን፣መናቅን፣መቆርቆዝን፣…፤ ማስወገድ ነው። ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ በዚሁ መፅሐፋቸው ስለ እርቅ ምንነትና መሰረታዊ አላባውያን fundamental elements እንደሚከተለው ይተነትናሉ ።
” እርቅ ማለት በከባድ ጠብና ይህም ባስከተለው መጎዳዳት ፣ ጥላቻና መፈራራት ምክንያት ተለያይተው፣ ተራርቀው ፣ ተቆራርጠው የነበሩ ሰዎች የወደመውን የጋራ ኑሮአቸውን እንደገና ለመገንባት የሚጓዙበት ሂደት ነው። እርቅ ጥልቅ የሰላም ግንባታ ዘዴና አላማ ነው። የእርቅ ሂደት የሚከተሉትን እርምጃዎች ያካትታል ።”
፩ኛ . በግጭቱ ተካፋይ የነበሩ ወገኖች በሌላው ላይ የፈፀሙትን በደልና ጉዳት በሀቀኝነት ማመን ፤
፪ኛ . በተፈፀመው በደል እውነተኛ ፀፀትን መግለፅ ፤
፫ኛ . የተበደለውን አካል ከልብ ይቅርታ መጠየቅ ፤
፬ኛ . የተበደለው አካል ከልብ ይቅርታውን በመቀበል ይቅር ማለት ፤
፭ኛ . ተበዳዩን ጉዳት ከመድረሱ በፊት ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ ፤
፮ኛ . በደሉ እንደገና እንደማይፈፀም አስተማማኝ የሆነ ማረጋገጫ መስጠት ፤
፯ኛ . ከግጭቱና ካስከተለው ጉዳት በመማር የሁለቱንም ወገኖች ጥልቅ ፍላጎትና ጥቅም የሚያራምድ፣ የሚያጎላምስና የሚያስተሳስር አዳዲስ ግንኙነቶችን መመስረትና ዕቅዶችን መንደፍ ፤
እንደ አርዓያ
የእርቅና እውነት የማፈላለግ ስራ በተወሳ ቁጥር ደቡብ አፍሪካውያንንና የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ / ኤ ኤን ሲ/ ቀድመው ወደ አእምሮአችን ይመጣሉ። እንደ ሕዝብ የባርነት ፣ የግፍ ፣ የጭቆና ፣ የዘረኝነትን ቀንበርን እንደ ደቡብ አፍሪካውያን የተሸከመ የለም ማለት ይቻላል። በገዛ ሀገራቸው ሁለተኛ ፣ ሶስተኛ ዜጋ ሆነዋል። ተዋርደዋል ።ተግዘዋል ።ታስረዋል። በጅምላ ተገድለዋል። ከፖለቲካ ፓርቲ ደግሞ እንደ ደቡብ አፍሪካዎች ኤ ኤን ሲ ፣ ኮሚኒስት ፓርቲ፣ ኢንዲያን ኮንግረስ ፣ አፍሪካን ፒውፕልስ ኦርጋናይዜሽን የተሳደደ፣ የታደነ ፣የተጋዘ፣ የታሰረ ፣ የታፈነ፣ የተሰቃየ የለም ማለት ይቻላል። ይሁንና በማዲባ እና በፓርቲው ኤ ኤን ሲ ፊታውራሪነት እውነትን አፈላልገው ይቅር መባባል ችለዋል ።እርቅን አውርደዋል። እነሱ ይሄን ካደረጉ የእኛዎቹ ፓርቲዎች ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ካላቸው እርቅ ለማውረድ ምን ይሳናቸዋል ! ?
ኔልሰን ማንዴላ ዘረኛውን የአፓርታይድ የነጮች አምባገነናዊ አገዛዝ ስለተቃወመ ብቻ የእድሜውን ሲሶ ያህል 27 አመታት በአንድ ጠባብ ጨለማ ክፍል ከከባድ የጉልበት ስራ ጋር በስቃይ በእስር አሳለፈ ።ሆኖም ይቅርባይነቱን አላስቀረውም ።
ይቅርባይነት በግለሰቦች ከፍ ሲልም በማህበረሰቡ ባህላዊ እሴቶች ፣ ወረቶች ላይ የታነፀ መሰረት ነው። በአንዳንድ ግለሰቦችና ማህበረሰቦች ይቅርባይነት የማንነታቸው አካል ሲሆን በሌሎች ደግሞ ይቅርባይነት የተሸናፊነት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ደቡብ አፍሪካውያን፣ ሩዋንዳውያን ፣ ኬንያውያን ፣ ኮሎምቢያውያን እንደ ሕዝብ በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። ወደ ግለሰብ ስንመጣ ግን ከመደጋገም አልፎ እሰልሰዋለሁ እንደ ኔልሰን ማንዴላ አርዓያነት ያለው ሰው የለም ።ከዚያ ሁሉ እስር ፣ ስቃይና እንግልት በኋላ በአፓርታይድ ላይም ሆነ በነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ላይ ቂም አልያዘም ።” ከ27 አመታት እስር በኋላ ተፈትቼ ነጻነቴን ለመቀዳጀት ወደ እስር ቤቱ መውጫ በር እየተቃረብሁ እያለ ጥላቻን ፣ ቂምን እስር ቤት ትቼው ካልወጣሁ ምኑን ከእስር ተፈታሁት ብዬ አሰብሁ ።”
ሁላችንም የአካል እስረኞች ባንሆንም የአስተሳሰብ እስረኞች ነን ማለት ይቻላል ።ጥላቻን ፣ ዘረኝነት ፣ ቂም በቀለን በአእምሮአችን ጓዳ ይዘን ስለምንዞር ።እንደ ማዲባ ትተነው ስላልወጣን ።
” Long Walk to Freedom ” (1995) በተሰኘው ድንቅ የራስ የህይወት ታሪክ መፅሐፉ ፤ ” በሀገሬ መጀመሪያ እንታሰራለን ከዚያ ፕሬዚዳንት እንሆናለን ።” ያለው ትንቢታዊ ንግግር በደቡብ አፍሪካ ሆኖ ለመመስከር በቅተናል። የቀደሙት ፕሬዚዳንቶች ታቦ ኢምቤኪ ፣ ጃኮብ ዙማ ሆኑ ስልጣን ላይ ያሉት ስሪል ራማፎዛ ጊዜው ይለያይ እንጂ እስርን ቀመሰዋታል ።የእኛ ” መሪዎችም ” በአካላዊ እስር ባይሆንም በፍርሀት ቆፈንና በማንነት እስር ላይ ናቸውም ፤ አልፈውማል ።በቀጣዩ ምርጫ በተለይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሸንፈው ወይም በጥምር መንግስት የሚመሰርቱ ከሆነ ብዙዎቹ በእስር አልያም በስደት ያለፉ መሆናቸውን ልብ ይሏል ።ማዲባ እንዳለው ከመንፈሳዊም ሆነ አካላዊ ምርኮም ሆነ እስር በዘላቂነት ነጻ ለመውጣት ይቅር መባባል ያስፈልጋል ።
የኢዜማው አቶ የሽዋስ አሰፋ በበዓል ሰሞን በebs “የቤተሰብ ጨዋታ” ላይ ከኦነጉ ኦቦ ቀጀላ መርዳሳ ጋር በአንድ ቤተሰብነት ቀርቦ በነበር ጊዜ ፤ ” ብዙዎች ፖለቲከኛ ሆነን የተወለድን ይመስላቸዋል ።” ብሏል። እንደ ተቀረው ሰው መዝናናት፣ መሳቅ መጫወት እንደሚችሉ ለማሳየት ።በነገራችን ላይ ኦነግም ፣ ኢዜማም ሆነ ብልፅግና ወይም አብን ዴስቲኒ ኢትዮጵያ በሶስት ዙሮች ባዘጋጀው የምክክር አውደ ጥናት ከመጠራጠርና ከመወነጃጀል ወጥተው መቀራረብ በመቻላቸው ከሌሎች ኢትዮጵውያን ጋር በአንድነት መክረውና ዘክረው ” የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በ2032 ” ይዘው መጥተዋል። እንግዲህ የእነ አቶ የሽዋስና ኦቦ ቀጀላ ቤተሰብነት የተጀመረው ከዚህ ነው ።ተቀራርበው መነጋገራቸው ያመጣውን ለውጥ አቶ የሽዋስ ስሜትን በሚነካ የዋህነት ለArts tv ሲናገር ፤ ” ከዚህ በኋላ እነ ኦቦ ቀጀላን ጉንፋን እንኳ እንዲይዛቸው አልፈልግም ።” ነበር ያለው ።ለዚህ ነው ብሔራዊ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች መካከል ሊያካሂደው ባቀደው ፖለቲካዊ እርቅ ላይ ተስፋ ያደረግነው።
ማዲባ ከፍ ብዬ በጠቀስሁት ተወዳጅ መፅሐፉ ሁሉም ጥላቻን ተምሮት እንጂ ከእናቱ ማህፀን ይዞት የተወለደ የለም ።ጥላቻን የተማረ አእምሮ ደግሞ ፍቅርንና እርቅን መማር አይቸግረውም እንዳለው የፖለቲካ ፓርቲዎቻችንም ምንም እንኳ በስተእርጅና ቢሆንም የይቅርታን አቡጊዳ መቁጠር አይከብዳቸውም ብለን እናምናለን።
ፈጣሪ ለእውነተኛ እርቅና ይቅርባይነት ያብቃን !!!
አሜን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 23/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )
fenote1971@gmail.com