የእናት አምሳያ፣ የማይበርድ ፍቅር ማኖሪያ ፣ የኑሮ ወንዝ ማጥለያ፣ ውብ የታሪክ ርስት፣ አኩሪ ውርስ መልክዓ-መሬት ናት እናት ፤ ኢትዮጵያ!!
የኢትዮጵያ ፍቅር ገጽ በገጽ የማይታይ፤ ስውር ስፌት ነው። ከደማችን ጋር የተሳሰረ፣ ደም የሚያስከፍልና ያስከፈለ፣ መስዋዕትነቱ በማያቋርጥ የትውልዶች ፍቅር የታተመ ነው።
እስራኤላውያን በብዙ መከራ ሳቢያ በዓለም ዙሪያ ከመበተንና ታላቅ የተባለውን ግፍ ያለምህረት ጨልጠውና የመጣባቸጣውን የሂትለርን ጭፍጨፋ ካስተናገዱ በኋላም ወደቀደመው ምድር ሲሰባሰቡ መርሃቸው የነበረው፣ “ባለ ሐገር መሆን ታላቅነት ሲሆን ለሐገርህ መሞት ደግሞ የበለጠ ታላቅ ነው፤” ነው፤ በሚል መሪ ቃል ነበረ።
እኛ ኢትጵያውያን በታሪካችን አንድ ጊዜ መልክዓ ምድራዊ ይዞታችን ወደ ምስራቅ፣ እስከ ህንድ ውቅያኖስ ሲሰፋና በሰሜን ምስራቅ እስከ ኑቢያ ስንዘረጋ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ስንመጠን እንኑር እንጂ ከምድር የተጻፈ ታሪክ ጋር የሚተካከል ረዥም ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን። ያለፈው ሃምሳ ዓመት ታሪካችን ደግሞ አሁን ካለው ቅርጽ የሰፋና የግዛት ስፋቷ እስከ ቀይ ባህር የተዘረጋ ነበረ።
አሁን ያለችን ኢትጵያ የህዝቧን ብዝሃነት ጠብቃ የቆየችው እንደሚባለው በእመቃና በጭፍለቃ ሳይሆን፣ እርስ በእርስ በተሳሰረ የረዥም ዘመናት መስተጋብር ውጤት ነው። እንደሚባለው በአፈና ሆኖማ ቢሆን ፣ ቀይ ህንዶች በአሜሪካ ፣ በሐዋኢ የፓሲፊክ እስያውያን ፣ እንዲሁም የጃፓን ዝርያዎች በላቲን አሜሪካ የደረሰባቸውና በሞዛምቢክ ፖርቱጋሎች በሃገሬው ህዝብ ላይ የፈጠሩት የማንነት ቀውስ ይፈጠር ነበረ። ግን አልነበረም፤ ሁሉም በራሱ ባህልና ቋንቋ ማንነትና አስተሳሰብ እየኮራ የኖረባትና ያለባት አንዱ ያንዱን እየቀዳ፣ እየተዋሰና እያላመ ፣ እያጣፈጠ የሚጠቀምባት፣ በነገር ሁሉ፣ የመሳሳብ ሃይሉ ከመገፋፋት በላቀ የሰፈነባት ሐገር ናት ፤ ሐገራችን ኢትዮጵያ!! በማንኛውም ሐገር እንደነበረ ሁሉ በደሃው ህዝብ ላይ የፍትህ፣ እጦት ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል አለመኖርና ስልጣንንም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያለመጋራት ፣ ጭቆና በእኛም ሐገር ነበረ።
ነገር ግን ፣ የሰሜኑ ሰው ሲኖር እንኳን ገናን፣ ጥምቀትን፣ መውሊድን፤ አረፋን፣ ሮመዳንን፣ ትንሳኤንና ዘመን መለወጫን (በጋራ ቅዱስ ዮሐንስ ይሉታል)፤ እያከበሩ በማይታይ ስውር ስፌት ተሳስረውና ተከባብረው ሲሆን ወደ ወሎ ስትሄዱ የሰው ስም ራሱ ምስክር ነው። እንደ ይመር ዓሊ፣ መሐመድ ነጋሽ፣ አህመድ ወልዱና አሚና ቸኮል ሲጠሩ ለጆሮ የማይቆረቁርና የአኗኗሩ ድርና ማግ ሆኖ መስማት የተለመደ ነው። ወረሒመኑና ወረገኑ፣ ወረባቦ፣ ቦረናና ጫቀታ፣ ከሎ የቦታ ስያሜዎች ናቸው። ጎንደር ብትሄዱ እንደ ገብሬና ከበደ፣ ፍትዊና አስገዴ የጎንደሬው ስም ነው፤ ወደጎጃም ብትመጡ ዳንግላ የቦታው ስም አርማጮና ገሶ የመሳሪያ ስም ቡልቲና ነጋሳ የሰው መጠሪያ ሆኖ ታገኙታላችሁ። ማነው ምድሪቱን በወጥነት ያንዱ ብቻ ያደረገው። አልነበረምም፤ አይደለምም።
ትግራይ ላይ ሲናገሩ እንኳን ፣ ክብሪትን ክርቢት፣ ጥገናን ጽገና ፤ ጠመንጃ ብረት፣ ሱሪን ሱሪ መንገድን ምንገድ… ወዘተርፈ ብለው ብቻ ሳይሆን በአንድ ወንዝ ምለውና ተጣጥበው የሚኖሩባት አድባር ጭምር ናት። እነዚህ አጠራሮች ከአገባብ ውጭ ዘዬ አከል ናቸው። (ዘዬ የአንድ ቋንቋ ልዩ አነጋገር ነው) ወደመሐል ሐገር ስንመጣ “ጠላት (ለለባ) ቅስቀሳ ቢያበዛም እኛ ሉጋም(ልጓም) ጨብጠን ፣ መልካው ( የወንዝ ጠባብ መሻገሪያ) ላይ እየተገናኘን ነበር የምንተገትገው፤ ብለው ነበር የሚያወጉት፤ በጠላት ወረራ ወቅት። “ሠቅ” ለሸዌው ቀበቶም መቀነትም ነው፤ ጨፌ ላንዱ ምክር ማድረጊያ ቤት ቢሆን ላንደኛው ረግረጋማ ርጥብ መሬት ነው። ያንዱ ጫካ ለሌላው ደን ቢሆንም አንዱ የአንዱን ይተረጉምበታል።
ዛሬም ይህ እንዲሆን በትናንትናና በዛሬ መካከል ያለው ትውልድ ፊታውራሪነቱን ወስዶ ከልቡ መትጋት ይጠበቅበታል። ለአሁኑ ዘመን ወጣት ማሳየትም ይገባዋል። ሐገራችንን ለመጠበቅ ይህ ትውልድ ወይም ኢትዮጵያውያን በዓለም ዙሪያ መበተን፣ ቁም ስቅላችንን ማየትና ሌላ ዘመናዊ ሒትለር በሀገራችን ተፈጥሮ የዘር ዕልቂት ሊደርስብን አይገባም። በሃገራችን የነበረው ዘግናኙ፣ ማእከላዊ እስር ቤት የፈረሰው ሌላ መዘዝና ክፉ ትውስታን ለማስቀረት ታስቦ ነው። ራሳችን ላይ ክፉ አንግሰን፤ ኦሽዊትዝ፣ ዳቻውና ሶቢቦር ሊገነባብን አይገባም። (ስፍራዎቹ የሒትለር የእልቂት ካምፖች ናቸው።) ሰላምን ለማጣጣም እና የመግባባት ህብስት አብረን ለመቁረስ በመከራ አለንጋ መገረፍ የለብንም ።
ሌላ ሌላውን እንተወውና ፣ ከእስራኤላውያን የምንማረው ያለቻቸውን ምድር በሁሉም መስክ የተከበረች፣ የተፈራችና የማትበገር በማድረግ በከበቧት ጠላቶቿ ፊት የብቃት ምልክት መሆንን ነው። እኛ ደግሞ በፍቅር በክብርና በዲሲፕሊን በታነጸ ብቃት ተከባብረንና ታፍረን የምንገነባት ብልጹግ ሐገር ማድረግ ነው፤ ያለብን። በዘፀአት (ምልሰት) የተሰራች ሳይሆን እግዚአብሔር ሰርቶ የሰጠን ነባር ውብ ሐገር አለችንና!!
እውቁ ባለቅኔ ፤ መምህሩና በኋላ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የነበረው፣ ዮፍታኼ ንጉሴ፡- በጣሊያን ወረራ ወቅት በየስፍራው የጎበዝ አለቆች ሳይበታተኑ በቅንጅት፣ ሊዘጋጁና ሊመክቱ እንደሚገባቸው ለመጠቆም በማሰብ እንዲህ ሲል ገጥሞ ነበረ።
“ሐገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ፤
ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ።” (1929ዓ/ም)
የእንቧይ ካብ የማይረጋ ፣ የቀልድ ቀልድ የመሰለ እርስ በእርሱ የማይያያዝና የማይቆም ነው። በባለቅኔው እምነት ፣ በህብረት ውስጥ አሸናፊነት ፣ በህብረት ውስጥ ጉልበትና ብቃት እንዳለ ጠንቅቆ ያውቅ ነበረና ነው፤ ያገሩን ሰው ሐገር ለማቆም በአንድ እንቁም፤ ሲል ያሳሰበው።
በአንዳንድ ኃላፊነት በጎደላቸው አካላት፣ የተሰጠችን ሐገር እንዳትኖረን፣ እንድናፍርና እንድንሳቀቅ መድረሻ ቢስነት እንዲሰማንና እንድንጠራጠር እየተደረገ ላለው ጥረት መዋጮ ሰጪና በርጋጊ መሆን የለብንም። ሲገፉን ለመገፋት ፤ ሲያሳንሱን ለማነስ የተዘጋጀን ብርድ ላይ እንዳደረ ብረት የቀዘቀዝንና የነፈሰ ንፋስ የሚያላጋን ፣ ለመጣውም ጥያቄ ምላሽ የማንሰጥ ስጉዎች መሆን አይገባንም። ስንጠራጠርና ስጋት ሲሰማን አፍራሹ ሃይል ጉልበት ያገኛል።
እንደ እስራኤላውያን በሁሉም ረገድ በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብ ለመቆም እንኳን ባንችል፣ በሐሳብ ተለያይተን ነገር ግን፣ ኢትዮጵያን በሚመለከት ርዕሰ ጉዳይ ላይ በሃሳብ ከሚለያዩን ጋር በአንድነት ቁጭ ብለን በመነጋገር በእኩልነት አንድነቷን የጠበቀች፤ በመንፈሳዊ አንድነት የሰከነች፣ ልዩ ልዩ እምነቶቿን እንደባህሎቿ ሁሉ የምታከብር፣ ልጆቿን በዘር ልክፍት ሳይሆን በላቀ ዕውቀት የምታንጽና የምታሳድግ፣ ያልተነካ የከርሰ ምድር ሐብቷን በጋራ በመጠቀም በፍትሐዊ መንገድ የምታከፋፍል ድንቅ ሐገር እንድትሆን መስራት ይጠበቅብናል።
ስውር ስፌት አይታይም ግን ጥብቅ ነው፤ አይመዘዝም። በልዩነቱ መጣበቁ ውበቱ የሆነ፣ አንድነት ነው። ስውር ስፌት ብርቱ ነው፤ አይዘረዘርም ቁልፍ ነው። የእኛ ኢትዮጵያውያን ጥምረት እርበርስ የተጋመደና በተገኘው ክር እንኳን ያልተሰፋ መሰሉ መሰሉን ያጋመደ ሥነ-ልቡናዊና አእምሯዊ ስፌት ነው። እኛን ኢትዮጵያውያንን በቋንቋ ዘውግ ለመዘርዘርና እንደብር ሳንቲም ለመበተን የሚሯሯጡት ወገኖች ያልገባቸው እንደ ህዝብ ከብርነት ወደመዳብነት ከመውረድ ይልቅ ብርነታችን ላይ የተጣበቅን ድምሮች መሆናችንን ነው። አንዳንዶች፣ ሲያወርዱን ወርደን ለመቀነስ የምንጣደፍ ክብራችንን የማናውቅ ህዝቦች ሳንሆን ሊያቀልሉንና ሊያዝጉን ለሚወዱት ወገኖች የምንሰጣቸው ምላሽ የማይጠብቁት ሁሌ የተወለወለ አንድነታችንን ነው። እኛ፣ ኢትዮጵያውያን አንዳንዶች እንደሚያስቡት በሰም የተጣበቅን ጥርሶች ሳንሆን ተፈጥሮ በረቂቅ ጥበቧ የገመደችን ፈትል ነን።
እርስ በእርሳችን ተፈራርተን የተቀራረብን ሳንሆን ተዋድደን የተዋሃድን ህዝቦች ነን። በባዕድ ምድር እንኳን ስንገናኝ “ኢትዮጵያዊ ነህ ፤ ነሽ ?“ ለመባባል የማንፈራ፤ ፍቅርና መስዋዕትነታችንን የምናውቅና አንዳችን በአንዳችን ልዩ ውለታ ያልታሰርን፣ ገጽታችን ያግባባን፣ እርስ በእርሳችን፣ ባልተወጋ የረቂቅ መርፌ ስፌት የተሳሰርን ግጣሞች ነን። ኢትዮጵያ፣ ከሰሜን መተማ ወሰን፣ እስከ ደቡብ ወልወል፣ ከምስራቅ ደወሌ እስከ ምዕራብ ጋምቤላ ጫፍ ብቻ ሳይሆን በመልክዓ-ህዝብ ጭምር የተዋደድን ለሚጠላን የአስፈሪነት ምልክት የሆንን ህዝቦች ነን።
አንዴ በመሬት፣ ሌላ ጊዜ በውሃ ጦስ፣ አንዴ በቋንቋ ዘውግ፣ ሌላ ጊዜ በእምነት ዞግ፣ ሊከፋፍሉንና ሊደፍሩን ቢሞክሩም ሁልጊዜ በአምላኳ ተራዳኢነትና በህዝቧ የግንባር ሥጋነት የግዛት ልእልናዋ ሳይደፈር የቆየች ነች፤ ኢትዮጵያ ። የማንኛውም ሐገር ዋነኛ የጠላት ምርኩዝና በትር የሚነሳው ከውጭ ሳይሆን ከውስጥ ነውና ውስጣዊ ጠላቶች በህዝብ ስምና ታርጋ በሚያወጡት ልፍለፋም ሆነ፣ የመደራጃ ፍላጎታቸውን ለማሳካት በፈለጉት መንገድ ራሳቸውን የዲና መሳሪያ ማድረግ ይችላሉ።
በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ የተነሱ የውስጥ ጠላቶቿ፤ ፈተኗት እንጂ አላሸነፏትም፤ አስወጓት እንጂ አልረቷትም። ከደጃች ሃይለሥላሴ ጉግሳ እስከ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፤ ከተግባቢ ባንዳ እስከ አስካሪ ድረስ ብረት ወድረው ለጠላት አድረው ቢሰለፉም አንገዳገዷት እንጂ አልጣሏትም፤ አስወረሯት እንጂ አላንበረከኳትም። ስለዚህ ማንህም ብትሆን ስለእርሷ ክፉ ከሚያስቡ ጋር ክፉ አትዶልት፤ ክፉ ከሚያደርጉት ጋር አትተባበር፤ ክፉ ከሚያወሩት ጋር ክፉ አታውራ።
አንዳንዱ ሰውማ አስቂኝ ነው፤ አስተምራ አበልጽጋና አሻሽላ ባለማዕረግ ባደረገችው ሐገር ላይ ቆሞ የቆመባትን ሐገር አታስፈልገኝም ሲል ይደመጣል። “በማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ” እንዲሉ አበው፤ ቀድመው ባላገርና ዜጋ ያደረገቻቸውን የምትክ ሳይሆን ዋና ሐገር ለመርገም ፤ ምን ብርቱ ምክንያት እንዳገኙ አይታወቅም።
ለእኛ መልካሙ ነገርና የሚያዋጣን ፣ የሚናፍቀንን ብልጽግና በማምጣት በድህነት ላይ ጌታ መሆን ፤ የሚያጋጨንን በመተው በመገፋፋት ላይ አዛዥ መሆን እንጂ አንካሳና ጎርባጣ መንገድ ከቶውንም አይጠቅመንም። ይህችን ሐገር ለማቆም በስውርና በግልጽም የተደከመውን ድካም ማንም አልነገረን ይሆናል። እንኳንስ ሐገርን ያህል ባለብዙ መልክ ፣ ባለብዙ ባህል፣ ባለብዙ ሃብት ምድርና ህዝብ ቀርቶ አንድን ቤተሰብ በሁለት እግሩ ለማቆም ታላላቆች የሚከፍሉት ዋጋ የዋዛ አይደለም።
አንድ ድንቅ ታሪክ ላጋራችሁ። እናት ከቀን ስራዋ በተጨማሪ ፣ የሌሊት ተረኛ ነኝ፤ ብላ ወደ ሥራ ቦታዋ ትሄድና ትመጣለች ፤ እስከ መኪና መሳፈሪያ ቦታዋ ድረስ ሁልጊዜ አሳፍሯት የሚመጣው የ14 ዓመት ልጇ፣ ትምህርት ቤት ስለወላጆቻቸው ብዙ ለሚያወሩት ጓደኞቹ እርሱም ስለወላጅ እናቱ ለማውራት አስቦ ሊሆን ይችላል። አንድ ቀን የሥራ ቦታዋን ማየት ፈልጎ በምትሳፈርበት የከተማ አውቶቡስ ተደብቆ ተሳፍሮ ይሄዳል ።
ሁሉም ሰው ከሚወርድበት ስፍራ ትወርድና ወደ ምትናገርለት መስሪያ ቤት ሳይሆን ሌላ ቦታ ትሄዳለች ፤ ቀስ ብሎ በዚያ ምሽት ይከተላታል። ከዚያም ሲከተላት ወደ አንድ አነስተኛ ሆቴል በጓሮው በር ትገባለች። ጥቂት ቆይቶ ተከትሏት ሲገባ ሽርጥ አድርጋ ወደ ኩሽናው ስታመራ ያያታል። ከዚህ በላይ ማየት ስላልፈለገ ጥሎ ይወጣል።
ጠዋት ጠዋት ወደት/ቤት ልትሸናቸው ከቤት ስትወጣ ሁለመናዋ ወጥ ወጥ ለምን እንደሚል ይገባዋል ፤ እናም እማ፣ ከየት ነው፤ የምትመጪው ? ሲላት፣ ከፋብሪካ ነው አለችው።
ምን ፋብሪካ ነው የምትሰሪው?
ጨርቃ ጨርቅ ነዋ!
ወይ የኔ እናት ለነገሩ የትም ሰራሽ የት ፣ የኔንና የእህቴን ህይወት ለመለወጥ አይደል የምትተጊው። ከዛሬ ጀምሮ ለእኔም አንቺ በምትሰሪበት ሆቴል የምግብ አቅራቢነት ሥራ ፈልጊልኝና ላግዝሽ እንጂ ብቻሽን 16 ሰዓት እየፈጋሽ እኛን መካከለኛ ደረጃ ገቢ ካላቸው ሰዎች ትምህርት ቤት አታስምሪንም፤ ይላታል።
እንዴት አወቅክ ፤ ልጄ?
ትናንት ማታ እስከመጨረሻው ልሸኝሽ ፈልጌ፣ ተከትዬሽ አወቅኩ። አሁን እንዴት ማወቄ ሳይሆን የሚረባው፣ እንዴት እንደምረዳሽ ማወቁ ላይ ነው፤ አላት።
ለእኔ አለችው፤ ለእኔ ትልቁ እርዳታ አርፋችሁ፤ ከመንገዳችሁ ሳትዛነፉ፣ እናም ሳትታክቱ ትምህርታችሁን ብዙ ሳይደላችሁም ቢሆን መከታተላችሁ ነው፤ አለችው። በዚሁ ተስማምተው፤ ሁለቱም ልጆቿ ለከፍተኛ ትምህርት በቁላት።
ስለዚህ ፣ ሐገርህንና እናትህን ፣ ልትረዳት ባትችል አታስተጓጉላት፤ ልታሞግሳት ባትችል አታንጓጥጣት፤ ልታክማት ባትችል እንኳን አታሳምማት፤ ልታበለጽጋት ባትችል እንኳን አታደህያት ፤ ከሚያደኸዩዋት ጋርም አትተባበር፤ ለሰላሟ ባትተጋ እንኳን ለሁከቷ አታዋጣ፤ ለመረጋጋቷ ባትተባበር እንኳን ለሽብሯ ከሚያሴሩት ጋር አትወዳጅ፤! በዝምታህ በትንሹ እንኳን ቢሆን ታግዛታለህ፤ በኋላም ከክፉ ጸጸት ትድናለህ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 23/2012
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ