አዲስ አበባ፡- ለዓድዋ ጦርነት ምክንያት በሆነውና የውጫሌ ውል በተፈረመበት ታሪካዊ ቦታ ላይ የተሠራው የይስማ ንጉስ የባህል ማዕከል ግንባታ ከታቀደለት ጊዜ በአራት ወር ቢዘገይም በሰኔ ወር እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ የካቲት 22 ቀን 2011 ዓ.ም በሠራው ዘገባ የባህል ማዕከሉ ከታቀደለት ጊዜ ቀድሞ እንደሚጠናቀቅ ተገልጾ ነበር። ለመሆኑ ግንባታው ምን ላይ ደረሰ ስንል የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅትን ጠይቀናል።
የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ሱፐርቫይዘር አቶ ጌታቸው አድጎ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ግንባታው 70 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን በመጪው ሰኔ ወር ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል። በተባለበት ጊዜ ያልተጠናቀቀበት ምክንያት ተጨማሪ ሥራዎች ስለተካተቱ ነው። ለተጨማሪ ሥራዎችም ተጨማሪ በጀት ተመድቧል። በአንዳንድ ክፍሎች ላይም የዲዛይን ለውጥ ተደርጓል።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የአሉምኒየም ሥራው ተጠናቆ የጣሪያና የውጭ ሽፋን ማሳመር ሥራዎች መቅረታቸውን ሱፐርቫይዘሩ አስታውሰው ቀሪ ሥራዎችም ቢሆኑ እስከ ዓድዋ በዓል ድረስ ሊደርሱ እንደማይችሉ ገልጸዋል።
ይስማ ንጉስ የባህል ማዕከል የተያዘለት በጀት 25 ሚሊዮን 734 ሺ 720 ብር የነበረ ሲሆን በተጨመሩ ሥራዎች ምክንያት አሁን ላይ በጀቱ 29 ሚሊዮን 594 ሺ 928 ብር መድረሱን አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል።
የይስማ ንጉስ የባህል ማዕከል የቀለም ቅብ ጥቁርና ነጭ ሲሆን፤ አሸናፊውን ጥቁርና ተሸናፊውን ነጭ ለመግለጽ ታስቦ የተሠራ ነው። አሸናፊነትን የሚያመለክት የእጅ ምልክትም በማዕከሉ ጣሪያ ላይ ይሠራል።
የውጫሌ ውል አንቀጽን የሚገልጽ የማዕከሉ ዋና መግቢያ በር ላይ የግዕዝ ቁጥር 17 ይኖራል። የባህል ማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ ሙዚየምና ካፍቴሪያ የሚኖረው ሲሆን፤ ሙዚየሙም ሆነ የባህል ማዕከሉ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያሳዩ መረጃዎችን ይይዛል ሲሉ ሱፐርቫይዘሩ አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2012
ዋለልኝ አየለ