አዲስ አበባ፡- 254 ሜጋ ዋት የኃይል የማመንጨት አቅም ያለው የገናሌ ዳዋ ሦስት የኤሌክትሪክ የኃይል ማመንጫ ግድብ ተመረቆ ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ትላንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ከ15 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች መካከል አንዱና የሁለት ክረምት ባለቤት በሆነው የገናሌ ወንዝ ላይ የተገነባው ገናሌ ዳዋ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ሥራ ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም ይመረቃል።
እያንዳንዳቸው 84 ነጥብ 7 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ሦስት ‹‹ተርባይነሮች››ያሉት ይህ ኃይል ማመንጫ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ 254 ሜጋ ዋት ወይም 1ሺ 640 ጌጋ ዋት ሰዓት ኃይል በየዓመቱ ያመነጫል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ግድቡ 110 ሜትር ቁመትና 426 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ 2 ነጥብ 57 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም አለው። የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ብሄራዊ የኃይል ቋት ይገባ ዘንድም ኃይል ማመንጫው ይርጋለም ከሚገኘው ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ጋር በኤሌክሪክ ኃይል ማስተላለፊያ አማካኝነት ተገናኝቷል።
ለውሃ ማስተላለፊያ የሚረዳ ከግድቡ ጋር የተገናኘ 12 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የውሃ ማስገቢያ ዋሻ ቁፋሮ የተከናወነ ሲሆን በጣቢያው ላይ 380 ሜትር ርዝመት ያለው ውሃ መልቀቂያ ዋሻም መገንባቱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቱ አሁን ላለበት ደረጃ የደረሰው የሲቪል፣ የኤልክትሮ ሜካኒካልና ስቲል ስትራክቸር ሥራዎችን በማካነወን ሲሆን፤ የዋና ግድብ፣ የውሃ መልቀቂያ ዋሻ፣ የውሃ ማስተንፈሻ፣ የውሃ ማስገቢያ ዋሻና የውሃ ማስተላለፊያ ዋሻ የግንባታ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁንም አመልክተዋል።
የሦስት ‹‹ዩኒቶች›› የኤሌክትሮ ሜካኒካል የተካላ ሥራ ተጠናቅቆ የደረቅና የውሃ ፍተሻ ሥራ በማከናወን ኃይል ለማመንጨት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል። ግድቡ ኃይል ከማመንጨት ባሻገር የአካባቢውን ወጣቶች በቀጣይ ጊዜያቶች በማደራጀት በዓሣ ሀብት ልማት ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እንደታሰበም አስረድተዋል።
ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፤ የፕሮጀክቱን የሲቪልና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎችን እየሠራ የሚገኘው ሲጂጂሲ የተሰኘ የቻይና ኩባያ ሲሆን፤ የማማከር ተግባሩን ደግሞ የአሜሪካው ኤም.ደብሊው.ኤች ከአገር በቀሎቹ አኪዩትና ኢንተግሬትድ ኩባያዎች ጋር በጥምረት አካናውነውታል። ፕሮጀክቱ በግንባታ ወቅት ለ1ሺ 500 ኢትዮጵያውያን ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
የገናሌ ዳዋ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በጉጂና ባሌ ዞኖች በሚገኙ የመዳ ወላቡና ጎሮዶላ ወረዳዎች አዋሳኝ፤ ከአዲስ አበባ 630 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ግንባታው በ2003 ዓ.ም የተጀመረው የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከካሳ ክፍያና ከውሃ ማስገቢያ ዋሻ ቁፋሮ ጋር ባጋጠመ ችግር ምክንያት ሦስት ዓመታትን ዘግይቷል። አጠቃላይ የፋይናንስ ወጪው 451 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው ከቻይና ኤክዚም ባንክ በብድር የተገኘ ነው። ቀሪው 40 በመቶ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሸፈነ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2012
አዲሱ ገረመው