አዲስ አበባ፡- ለምስል ቀረጻ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ አነስተኛ በራሪ አካላት (ድሮኖች) በአውሮፕላኖች ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት ለመቆጣጠር የሚረዳ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የኤር ናቪጌሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ክብረዓብ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጡና በግለሰብ ጭምር የሚንቀሳቀሱ ድሮኖች በአውሮፕላኖች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ከወዲሁ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል።
በተለይ በኤርፖርቶች እና በትላልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች አካባቢ ተጠግተው እንዳይበሩ የሚያደርግ ህግ ማጽደቅ ካልተቻለ የአውሮፕላን አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ።
እንደ አቶ ሽመልስ ገለጻ ድሮኖች በኤርፖርቶች አካባቢ በምን ያህል ርቀት መብረት አለባቸው?፣ ምን ያህል መጠን እና ፍጥነት ያላቸው ድሮኖች ደግሞ ወደሃገር ውስጥ ገብተው መንቀሳቀስ ይችላሉ? የሚሉ የደህንነት እና የጉምሩክ ህግ ማዕቀፍ ያላቸው መመሪያዎች ወጥተውም ተግባራዊ መደረግ አለባቸው።
ስጋቱን ለመቀነስ በግለሰብ ደረጃ የሚገቡ ድሮኖች እንዲቆሙ ቢደረግም ለግብርና፣ ለመንገድ እና ባቡር ግንባታዎች የሚያስፈልጉ ድሮኖች ግን በልዩ ሁኔታ እንዲገቡ ሲደረግ ቆይቷል። ይሁንና ቴክኖሎጂውን መገደብ ሳይሆን የቁጥጥር ስርዓቱን ማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ የህግ ማጽደቁ ጉዳይ ሊፋጠን ይገባል።
በእንግሊዝ ሀገር በድሮኖች እንቅስቃሴ ምክንያት ለሁለት ሰዓታት ያክል የአውሮፕላን ጉዞዎች መታገዳቸው አንዱ የጥንቃቄ ማሳያ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሽመልስ፤ በኢትዮጵያ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት መከላከል ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ ባለስልጣኑ የእራሱን ህግ አውጥቶ ተግባራዊ ለማድረግ ቢሞክርም የድሮኖችን እንቅስቃሴ ቁጥጥር ማድረግ የሚገባው የደህንነት አካላት ናቸው በሚል ሳይጸድቅ መቅረቱን አስታውሰው ይሁንና በአየር መንገዶች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቆጣጣር ከመከላከያ፣ ከደህንነት እና ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። በቋሚነት ችግሩን ለመከላከል ድሮኖችን ከጉምሩክ ጀምሮ እስከ አየር ላይ እንቅስቃሴያቸው ድረስ መቆጣጠር የሚያስችሉ ህጎች መጽደቅ እንዳለባቸው አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የቅድመ ምዝና ወይም ኦዲት ሪፖርት መሰረት ከአፍሪካ ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱን ገልጿል። በመጀመሪያ ደረጃ የአቪዬሽን አሠራር እና አጠቃላይ ኦዲት የግብጽ፣ ጋና እና ደቡብ አፍሪካን ሲቪል አቪዬሽኖች በልጦ በ91 ነጥብ 78 ውጤት ከአፍሪካ አንደኛውን ደረጃ አግኝቷል። እንደ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን መረጃ፣ የመጀመሪያው ምዘና የኢትዮጵያ የአቪዬሽን አሠራር መሻሻሎች እንዳሉት ያሳየ ውጤት ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2012
ጌትነት ተስፋማርያም