ኢንዱስትሪ ከተማነቷ ከከተሞች ቀድሞ ስሟ እንዲጠራ አስችሏታል። ብዙዎች የኢትዮጵያ ዱባይ እያሉ ያሞካሿታል። ከተማዋን የኢንዱስትሪ እምብርት ብንላትም ቢያንሳት እንጂ በልኳ አይገልጻትም።
ለኢትዮጵያም ለከተማዋም ወሳኝ በሆኑ ግዙፍ እንዱስትሪዎች ተከባ ትገኛለች። ዱከም ሕዝቦቿ ተፋቅረው የሚኖሩባት ከተማ ናት። የመዝናኛ፣ የንግድ፣ የኢንደስትሪና የመገናኛ ከተማ በመሆን ተምሳሌት ተብላም ትጠቀሳለች። እንደውም ኢትዮጵያውያን ተሰብስበው ቁርጥ ስጋ የሚበሉባት ከተማም ናት።
ለብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያነትም የሥራ ዕድል አሳታፊነትም ትመቻለች። ለኢንቨስትመንት ሳቢ በመሆኗም እንኳን ከአገር ቤት ቻይናውያን ባሕር አቋርጠው ከትመውባታል። ግዙፉ የቻይናውያን ባለሀብቶች የሆነው ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን በ350 ሺ ሔክታር መሬት ላይ ዱከም ኢንዱስትሪ ዞን ላይ ተንጣሎ ይገኛል።
ከትናንት በስቲያ በአዳማ ስልጠና ላይ የሚገኙ ሁለት ሺ የሚጠጉ ከየክልሉ የተወከሉ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በንድፈ ሃሳብ እየቀሰሙት ያለውን በተግባር ለመገንዘብ እንዲያስችላቸው በዱከሙ ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ተገኝተዋል።
አመራሮቹ በቁጭትና በእልህ ወደክልላቸው ሲመለሱ እንደዱከሙ አይነት ኢንደስትሪ ዞን ለማስፋፋት እየተመኙ ተመልክተናል። በጉብኝቱ ከተሳተፉትና አስተያየት ከሰጡን መካከል ከሶማሌ ክልል የተወከሉት አቶ ኢብራሂም አብድል ቃድር፤ ዱከም የኢንዱስትሪ ዞንን በመጎብኘታቸው ብዙ ነገር ለመመልከት እንዳስቻላቸው ይናገራሉ።
የልብስ ስፌት፣ የአልሙኒየም ምርትና በርካታ ሥራዎች አገር ውስጥ መሠራታቸውን ተመልክተዋል። የሶማሌ ክልል ለሥራው ምቹ በመሆኑም የዱከምን ተሞክሮ ወደክልላቸው ለማስፋፋት ጥረት እንደሚያደርጉም ይገልጻሉ።
ከጋምባሌ ክልል በጉብኝቱ የተሳተፉት አቶ ኩዌት ሉል በተለይ ከብረታ ብረት ሥራ ጋር ተያይዞ ሰፊ ምርት ማምረት መቻሉን በመልካምነት ያነሳሉ። ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ለወጣቶች የተፈጠረው ዕድልም በበጎነት የሚጠቀስ መሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም ወደክልላቸው በማስፋፋት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
ከአማራ ክልል የተሳተፉት አቶ ፍቃዴ ዳምጤም፤ ለወደፊቱ አቅም የሚፈጥርና በርካታ ልምዶች በመቅሰም በሁሉም አካባቢዎች የሚያስፋፉበት አጋጣሚ በዱከም መመልከታቸውን ይናገራሉ። በጨርቃ ጨርቅና በሌሎቹ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ለሴቶችና ለወጣቶች በርካታ የሥራ ዕድል መፈጠሩን መስክረው የተማከለ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም ይናገራሉ።
ባንኮች፣ ቢሮዎች፣ ሕክምና ጣቢያዎች፣ ሱፐር ማርኬቶች በአንድነት መገኘታቸው ጥሩ ነገር መሆኑን ይናገራሉ። የአማራ ክልል ለግብአትነት የሚሆኑ በቂ ምርቶች እንዳሉት በመጥቀስም፤ ወደክልላቸው ሲመለሱ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር፣ የተሻለ አመራር በመፍጠር፣ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅና ባለሀብቶችን በማስገባት በኩል ሰፊ ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚገባ ነው አቶ ፍቃዴ የሚያብራሩት።
እየተካሄደ ያለውን ሪፎርም ባግባቡ ለማሳካትና ከግቡ ለማድረስ እንዲያስችላቸው ከንድፈ ሃሳብ እስከ ተግባር አቅም ለመገንባት፣ እውቀትና ልምድ ለማካበትና ተመልሰው በአካባቢያቸው እንዲያስፋፉትና እንዲያጎለብቱት ተስፋ ተጥሎባቸዋል ይላሉ የፓርቲው የሕዝብና ዓለም አቀፍ ዘርፍ አስተባባሪው አቶ አወሉ አብዲ።
ላለፉት 27 ዓመታት በተተገበረው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ያን ያህል ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱንና ግብርና መር ቢባልም ያለፉትን ጊዜያት ዘርፉን ያልተሻገረበትና ያልዘመነበት ሁኔታ እንደነበረ ያስታውሳሉ። ለኢንዱስትሪ ዘርፉም ትልቅ ግብዓት ሊሆን በሚችል ደረጃ ያልበቃ እንደነበረም ይጠቁማሉ።
ከጥር 16 ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ በአዳማ ከተማ ስልጠና ላይ የሚገኙት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ስልጠናም እስከ የካቲት 2 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ መገለጹ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2012
ዘላለም ግዛው