ኬሊ የስምንት ዓመት ታዳጊ ነች። ወደ ሆስፒታል የገባችው የልብ ዝውውር ቀዶ ጥገና (ትራንስፕላንት) ለማድረግ ነው። የተቀየረላት ልብ የተወሰደው ደግሞ አንዲት በሰው ከተገደለች የ10 ዓመት ልጅ ነበር።
ኬሊ የተሳካ የልብ ዝውውር አድርጋ ከሆስፒታል ከወጣች በኋላ ግን ህይወቷ በአስፈሪ ህልሞች ተዘበራረቀ። በህልሞቿ የምታየው ደግሞ ልብ የሰጠቻትን ልጅ ገዳይ ነበር። የኬሊ አስጨናቂ ህልሞች እውነት መሆናቸው የተረጋገጠው ግን እናቷ ወደ ስነልቦና ባለሙያ ከወሰደቻት በኋላ ነው። እስከዚህ ቅጽበት ድረስ የልብ ሰጪዋ የ10 ዓመት ታዳጊ ገዳይ አይታወቅም ነበር። የኬሊ የሌሊት ህልሞች ተሰባስበው ስለገዳዩ አስገራሚ መረጃዎችን ሰጡ። ጊዜውን፣ መሳሪያውን፣ ቦታውንና የገዳዩን ልብስ ሳይቀር አጋለጡ። በመሆኑም ፖሊስ በዚህ መረጃ ተንተርሶ ገዳዩን በቀላሉ አድኖ በመያዝ ለፍርድ ማቅረብ ቻለ።
በሜይ 29፣ 1988 ዓ.ም ክሎር ሲልቪያ የምትባል አንዲት አሜሪካዊት በያሌ ሆስፒታል ውስጥ የልብ ዝውውር ተደረገላት። ልቡ የተሰጣት እዚያው አሜሪካ፣ ማይን ውስጥ ከሚኖር የ18 ዓመት ወጣት ነበር። በሞተር ሳይክል አደጋ እንደሞተም ለሲልቪያ ተነግሯታል። ሲልቪያ ቀዶ ጥገና ካደረገች ከቀናት በኋላ ግን ያለ ልማዷ ቢራ የመጠጣት ፍላጐት እንዳደረባት ተናገረች። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ የዶሮ ስጋ አምሮት አሰከራት። በዚህ የተነሳም የዶሮ ሬስቶራንት ማዘውተር ጀመረች።
በተጨማሪ የማትወደውን ቆስጣ መብላትና ቲም ኤስ ስለተባለ ግለሰብ ዘወትር ህልም ታይ ነበር። ሲልቪያ ራሷ ባደረገችው ጥረትና ማይን ውስጥ በሚታተም ጋዜጣ አማካኝነት እየተረዳች ልብ የሰጣት ሰው ቲም እንደሚባል አረጋገጠች። የቲም ቤተሰቦችን ከተዋወቀች በኋላ፤ ልብ የሰጣት ቲም የዶሮ ስጋ፣ ቆስጣና ቢራ እንደሚወድ አወቀች።
በኋላ ላይ ሲልቪያ አጠቃላይ ታሪኳን “A Change of Heart” በሚል መጽሐፍ አሳተመችው። የልብ ዝውውር የተደረገላቸው በርካታ በሽተኞች ከልብ ተከላ በኋላ አጠቃላይ ሰብዕናቸው፣ ባህሪያቸው፣ ፍላጐታቸውና አመጋገባቸው እንደተቀየረ ራሳቸው መስክረዋል። በቬና ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ የቀዶ ጥገና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ቤንጃሚን በንዝል እንደተናገሩት፤ 47 የልብ ተከላ ካደረጉ ህሙማን ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑት ሰብዕናቸው ተቀይሯል። በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች ደግሞ ከሦስት ህሙማን መካከል አንዱ የልብ ተከላን እንደሚፈራ ጠቁመዋል። በ1999 ዓ.ም አንዲት እንግሊዛዊት ወጣት እሷ ሳትፈልግ በዶክተሮችና በቤተሰቦቿ አማካኝነት ልብ ተከላውን እንድታደርግ መገደዷ ተገልጿል። የልጅቱ እንቢተኝነት የመነጨው ደግሞ በልብ ዝውውሩ ምክንያት የራሷን ማንነት እንዳታጣ ከመፍራት ነበር።
በልብ ተከላ ታሪክ ውስጥ በጣም አስገራሚ የሆነው የአሜሪካዊው ሶኒ ግራሐም ነው። ግራሐም የሌላ ሰው ልብ እንደሚያስፈልገው በዶክተሮች ከተነገረው በኋላ፣ ቴሪ ኮተል ከተባለ ራሱን በሽጉጥ ካጠፋ ግለሰብ ልብ ተወስዶ ተተከለለት። ግራሐም በ1995 ዓ.ም የልብ ተከላውን ቀዶ – ጥገና ካደረገ በኋላ ልብ ከሰጠው ኮተል ሚስት ጋር ተገናኘ። ግራሐም፣ ቼርሊ ከተባለችው የኮተል ሚስት ጋር በፍቅር ስለወደቀ እርሷን አግብቶ መኖር ጀመረ። ከ12 ዓመታት በኋላ ግን ግራሐም ልክ እንደ ኮተል ራሱን በሽጉጥ አጠፋ።
የሚያስገርመው ግን ቼርሊ ለሁለተኛ ጊዜ የህይወት አጋሯን ማጣቷ ሳይሆን፣ ልብ የተቀያየሩት ሁለቱ ባሎቿ ራሳቸውን በተመሳሳይ መንገድ አጥፍተው መሞታቸው ነበር። የብሪታንያው “ዴይሊ ሜል” ጋዜጠኛ በአንድ ወቅት እንዲህ የሚል ታሪክ ዘግቦ ነበር። በጣም ደካማ ክህሎት የነበረው ዘገምተኛ ማናጀር ከሌላ ሰው ልብ ተወስዶ ከተተከለለት በኋላ ድንቅ የሚባል የአርት ችሎታን ተጎናፅፏል። ታሪኩን አስገራሚ ያደረገው ደግሞ ልብ የሰጠው ሰውዬ አርቲስት መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ነበር።
ይህን የሰብዕና መለዋወጥ በተመለከተ በርካታ ሀኪሞች የተለያዩ አስተሳሰቦችን አንፀባርቀዋል። አንዳንድ የስነ ልቦና ባለሙያዎች የተቀየረው ልብ “አንድ አካል” መሆኑን መርሳት የለብንም ይሉናል። ይህ አካል (ልብ) በሰጪው ሰውዬ ውስጥ ከሚገኙ ማንኛውም አካል በላይ የሳይኪክ ኢነርጂን የያዘ ነው። ባዮሎጂ ባለሙያዋ ሊያል ዋትሰን እንደምትለው የሰውነት ክፍላችን አንዱ አካል የሆነው ልባችን፤ የባህሪያችንን አሻራና ስሜታችንን የያዘ ነው። ሊያል ዋትሰን ጨምራ ስትናገር፤ ከኛ ጋር ንክኪነት ያላቸው የሰውነት ክፍሎቻችን በሙሉ ባህሪያችንን የሚይዙበት ዕድል አላቸው።
ብዙዎቹ የህክምና ሰዎችና የስነ – ልቦና ባለሙያዎችን ያስማማው ግን “ሴሉላር ሜሞሪ” የሚለው ነው። ሴሉላር ሜሞሪ ራሱን የቻለ ፅንሰ – ሐሳብ ሲሆን ሰብዕናችንንና ማስታወሻዎቻችንን መዝግቦ የሚይዘው አዕምሯችን ብቻ አይደለም ይላል። ማስታወስ ራሱን የቻለ ሒደት እንደመሆኑ መጠን በሌሎች የሰውነታችን ሲስተሞች ውስጥም ሊፈጠር ይችላል።በተለይ ደግሞ እንደ ልባችን ያሉ የሰውነት ክፍሎች የአዕምሮ ተግባር የሆነውን ማስታወስን በውስጣቸው ሊይዙ ይችላሉ ይላል።
አብዛኞቹ የሴሉላር ሜሞሪ ጥናቶች በሳይንቲስቶች የተረጋገጡ ናቸው። ነገር ግን ብዙዎቹ ሆስፒታሎች የልብ ሰጪዎችን ቤተሰቦች በመደበቃቸው አብዛኛዎቹ ታሪኮች ምስጢር ሊሆኑ ችለዋል። ታሪኮቹ ቢገኙ እንኳን ስምና አድራሻቸው አብረው አልሰፈሩም። በዘመናዊ የህክምና ዓለም ውስጥ ልብን ጨምሮ ሌሎችን የሰውነት ክፍሎች ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው ማዘዋወር የተለመደ ተግባር ሆኗል። ልክ ከላይ እንደጠቀስናቸው ዓይነት ታሪኮች፣ አሁንም ቢሆን ቀዶ ጥገና አድርገው የሚነሱ በርካታ ህሙማን የተለየ ባህሪ፣ ጣዕም፣ አስተሳሰብና ሌሎች እንግዳ ሰብዕናን እንደሚያንፀባርቁ በሴሉላር ሜሞሪ ጥናት ተደርሶበታል። ይህ ደግሞ ህክምናው ከሞት ሊያድን ይችል ይሆናል እንጂ ተፈጥሯዊ አለመሆኑን ይጠቁማሉ።
በተጨማሪም የእያንዳንዱ ሰው የሰውነት ክፍል የራሱ ባህሪ፣ ሰብዕና እና ስሜት እንዳለው ከማረጋገጡ በላይ የሁሉም ሰው የሰውነት ክፍሎች የተፈጠሩት በልካችን ተሰፍተው መሆኑን ይጠቁማሉ።
በአንድ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች የተሰበሰበው የጣት አሻራ አንድም መመሳሰል እንደሌለው ተገልፆ ነበር። አንድ ሚሊዮን ሰዎች፣ አንድ ሚሊዮን የተለያየ የጣት አሻራ እንዳላቸው ስንመለከት ማንም፣ ማንንም እንደማይመስል እንገነዘባለን። የልብ ተከላ ታሪኮችም የሚናገሩት ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ የልብ አሻራ እንዳለው ነው።
በእርግጥ ታሪኮቹ ያስተማሩን ትልቁ ነገር በልቦቻችን ውስጥ ትንንሽ አዕምሮዎች መኖራቸውን ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ከልብ ተከላ በኋላ የሚከሰቱት የባህሪ ለውጥና የሰብዕና መዘበራረቅ መንስኤ፣ ምናልባት የሰዎች ትክክለኛ የልብ አሻራ ተወግደው በምትኩ የማይመለከታቸው አሻራዎች በመግባታቸው ይሆናል። ዋናው ቁምነገር ግን ልባችን የራሱ አዕምሮ እንዳለው መገንዘባችን ነው። የሐገሬ ሰው “ይሄ ልበ ቢስ!” የሚለው ቀደም ብሎ የሴሉላር ሜሞሪ ሳይንስ ገብቶት ይሆን?
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 22/2012
ሙሐመድ ሁሴን