- በኬንያ ለእርድ ከሚቀርቡ አህዮች 80 በመቶ ከኢትዮጵያ ይሄዳሉ
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ አህዮች በሕገወጥ መንገዶች ከአገር የሚወጡባቸው ሁኔታዎች ዝርያዎቹ እንዲመናመኑ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ የዓለም አቀፉን የብዝሃ ሕይወት ስምምነትን የሚጻረር እንደሆነ የኢትዮጵያ የብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ በኬንያ ቄራዎች ለእርድ ከሚቀርቡ አህዮች 80 በመቶዎቹ ከኢትዮጵያ እንደሚሄዱ ተጠቁሟል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ብዝሃ ሕይወት ዳይሬክተር አቶ አብርሃም አሰፋ እንዳሉት፣ አህዮች ወደጎረቤት አገራት በሕገወጥ መንገድ የሚሻገሩበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው፣ ድርጊቱ ዓለም አቀፍ የብዝሃ ሕይወት ስምምነቱን በመጣስ የአገሪቱን ዜጎች ጥቅም የሚጎዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቢሲኒያ፣ አፋር፣ ሀረርጌ፣ ኦጋዴን፣ ሲናር እና ኦሞ በመባል የሚታወቁ የተለያዩ የአህያ ዝርያዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ አብረሃም፤ የትኛው ዝርያ በከፍተኛ ደረጃ ለጥቃቱ ተጋላጭ እንደሆነ ጠለቅ ያለ ጥናት በማድረግ መለየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ይህም የችግሩን ሁኔታ በተገቢው መለየትና ማረጋገጥ ከማስቻሉም በላይ መከላከልና መቆጣጠር እንደሚያስችልም አስረድተዋል፡፡
በዓለም አቀፍ የእንስሳት መብት የኢትዮጵያ ተወካይና የብሩክ ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶክተር ደስታ አግቴ በጥናቶች አስደግፈው እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ ከስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ አህዮች አሉ፡፡
በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችም ሕልውናቸው በእነሱ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ተናግረዋል።
ዶክተር ደስታ እንዳሉት የቻይና ባለሀብቶች ኬኒያ ውስጥ አራት የአህዮች ሉካንዳ ቤቶችን ክፍተዋል። አንዱ ቄራ ደግሞ ከኢትዮጵያ ድንበር ላይ ተጠግቶ የተሠራ ነው። በአራቱ ቄራዎች በየቀኑ አንድ ሺ ሁለት መቶ አህዮች እንደሚታረዱ መረጃው አለን። ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት አህዮች የሚሄዱት ከኢትዮጵያ ነው።
አራጆቹ የትኞቹ የእህያ ዝርያዎች ከኢትዮጵያ እንደመጡ የሚያውቁ መሆኑንና ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በሕገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ የሚሄዱ እንደሆኑም እንዳረጋገጡላቸው ዶክተር ደስታ ተናግረዋል።
ፋብሪካዎቹ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የወጣባቸው ሲሆኑ በቄራ ሽፋን ከፍተኛ የባህላዊ መድሐኒት ፍላጎት ለማሟላት ተልዕኮ ይዘው የሚሠሩ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶክተር ደስታ አስረድቷል።
የብዝሃ ሕይወት ሀብት ተደራሽነት፣ ፍትሐዊና ሚዛናዊ ጥቅም ተጋሪነት ዳይሬክተሩ አቶ አሸናፊ አየነው እንደገለጹት፣ ብዝሃ ሕይወትን መጠበቅ፣ በዘለቄታ ጥቅም ላይ ማዋል እና ፍትሐዊና ሚዛናዊ ጥቅምን መጋራት የሚሉ ሦስት ዓላማዎች ያሉት ዓለም አቀፍ የብዝሃ ሕይወት ስምምነት በ1985 ዓ.ም (1992 እ.ኤ.አ) ፈርመው ተግባር ላይ ካዋሉት አገራት መካከል ኢትዮጵያ ተጠቃሽ እንደሆነች ተናግረዋል። በመሆኑም ከእንስሳቶቿ በፍትሐዊ መንገድ አገሪቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራርን ያካተተ ነው ሲሉም አክለዋል።
አቶ አሸናፊ አዋጅ ቁጥር 482/1998 ዓ.ም የጀኔቲክ ሀብት፣የማህበረሰብ ተያያዥ እውቀት እና የማህበረሰብ መብትን ጠቅሰው እንዳብራሩት፣ማንኛውም የ‹‹ጀኔቲክ›› ሀብት ለምርምርና ለእድገት (ዴቨሎፕመንት) ጥቅም ላይ ማዋልየሚያስችል ፈቃድ እንደሚያስፈልገው ይደነግጋል።
‹‹ዴቭሎፕመንት›› ማለት ማንኛውም እጽዋት ወይም እንስሳት ለመድሃኒት ቅመማ፣ለመዋቢያ ቁሳቁሶች እና በውሕደት ለሚፈጠሩ መገልገያዎች መስሪያ ለማዋል ከኢንስቲትዩቱ ፈቃድ ማግኘት እንዳለበት አስረድተዋል።
በመሆኑም እንደሚባለው በሕገወጥ መንገድ በገፍ ወደ ጎረቤት አገር የሚወጡ አህዮች ድብቅ ዓላማቸው ባህላዊ መድሃኒቶች ለመቀመሚያነት እንደሆነ ይነገራል። ይሄ ተግባር ዓለም አቀፍ ወንጀል ጭምር በመሆኑ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
‹‹በሰዎች ላይ ከሚፈጸመው በሕገ ወጥ ድንበር ማሻገር ወንጀል ባልተናነሰ በእንስሳት ላይ እየተፈጸመ ነው›› ያሉት በግብርና ሚኒስቴር የስጋ ላኪዎች (ቄራዎች) ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ጌዲዮን ይልማ ናቸው።
ዶክተሩ እንዳሉት፣ በየዕለቱ ወደ ጎረቤት አገር ቄራዎች የሚቀርቡ በርካታ ቁጥር ያላቸው አህዮች ከኢትዮጵያ በሕገወጥ ይቀጣሉ። ምክንያቱ ደግሞ የድንበር አካባቢ ጥበቃዎችና ሕጎች የተጠናከሩ አለመሆን፣የኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ብዝሃ ሕይት አሠራር በጣሰ መልኩ በርካሽ ገንዘብ የሚገኙ በመሆናቸው እንደሆነ አስረድተዋል። ችግሩ ከሚጠበቀው በላይ የሰፋ እንደሆነም ዶክተር ጌዲዮን አክለዋል።
ቻይናውያን ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የገነቡት የአህዮች ቄራ የሕብረተሰቡን ቁጣ በመቀስቀሱ እንዲቀር መደረጉ የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 22/2012
ሙሐመድ ሁሴን