የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተማሪዎች የደንብ ልብስ አሠርቶ ቢያሰራጭም ተማሪዎች በአግባቡ እየተገለገሉበት አለመሆኑን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ። የደንብ ልብሱን ከመደበኛ ስፌት ውጪ በማሳጠር፣ በመቅደድ እና በመተልተል ከሥነ ሥርዓት ውጪ ለብሰው የሚታዩ ተማሪዎች በየትምህርት ቤቶች ይስተዋላሉ።
ተማሪ ጽዮን ሞላ በዳግማዊ ምኒልክ መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናት። ከዚህ ቀደም ተማሪዎች በቤተሰብ አማካኝነት የደንብ ልብስ እንደ ፍላጎታቸው ያሰፉ እንደነበርና አሁን ላይ ግን የተሰጠው የደንብ ልብስ በተማሪዎች መካከል እኩልነትን መፍጠሩን ትናገራለች። ተማሪዋን በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ስናገኛት የሚገባውን የደንብ ልብስ አሟልታ አልለበሰችም ነበር። ለምን? ስንልም ጠየቅናት። ‹‹ዘመናዊ›› ነን በሚል አስተሳሰብ የተሰጠውን ልብስ በትክክል የማይጠቀሙበት ተማሪዎች መኖራቸውን ራሷን ምስክር አድርጋ ታዝባለች።
ተማሪዎች ትምህርት ቤት የሚሄዱበት ዋነኛ ዓላማቸውም ትምህርታቸውን መከታተል እንጂ የተለያዩ ፋሽኖችን ለማሳየት እንዳልሆነ በመጥቀስ፤ በተለይ አዲስ የተሰጣቸውን የደንብ ልብስ እንደ አዘቦት ልብሳቸው እንዳሻቸው በማድረግ እየለበሱት ነው ትላለች ተማሪ ጽዮን። ትምህርት ቤት ውስጥ ይህ ዓይነት አስተሳሰብ እንደማያስፈልግና ተማሪዎች ለአለባበስ ሥነ ምግባር ተገዢ መሆን እንዳለባቸው በመምከር እርሷ ከድርጊቱ እንደምትቆጠብ ገልጻለች።
የዳግማዊ ምኒልክ መሰናዶ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ኪዳነማርም አረጋይ እንደሚሉት፤ የከተማ አስተዳደሩ ለተማሪዎች የደንብ ልብሱን ሲያድል የዳግማዊ ምልሊክ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ከተጠቃሚዎቹ መካከል ናቸው። ይህ በተለይ አቅም የሌላቸውን ወላጆች ከማገዝ አኳያ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። በልብስ የሚመጣውን ጫና ለማስቀረትም ይረዳል።
የደንብ ልብሱ በበቂ ሁኔታ የተሰራጨ ቢሆንም፣ ሁሉም የደንብ ልብስ ተማሪዎች ባለቸው ተክለ ሰውነት ልክ ያልተሰፉ በመሆናቸው ጥቂት ተማሪዎች እስከአሁን በነባሩ የትምህርት ቤቱ የደንብ ልብስ እየተገለገሉ ይገኛሉ። በቅርብ ቀንም ለእነዚህ ተማሪዎች በልካቸው ተሰፍቶ ይደርሳቸዋል። ዘግየት ብለው ከተለያዩ አካባቢዎች በዝውውር የሚመጡ ተማሪዎችን ጨምሮ ለሁሉም የደንብ ልብሱን የማሟላቱ ሥራ እንዲጠናቀቅ አልባሳቱ የተሰጡ ሲሆን ለተማሪዎች የማሰራጨቱ ሥራም እየተከናወነ ይገኛል።
የደንብ ልብሱ የደረሳቸው የተወሰኑ ተማሪዎች መንግሥት አሠርቶ ከሰጣቸው ውጪ ሌላ ቅርጽ በማስያዝ እያሰፉት ነው የሚሉት ምክትል ርዕሰ መምህሩ፤ አዲሱ የደንብ ልብስ ለወንዶች ሱሪ፣ ሰደርያ፣ ሸሚዝና ከረበትን ያሟላ ሲሆን፣ ለሴት ተማሪዎች ደግሞ ሸሚዝ፣ ቀሚስና ሰደርያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
አልባሳቱ ለተማሪዎቹ ሲሰጡ እንደ ቁመታቸው መጠን ቢሆንም አሁን ላይ ሴቶች ቀሚሱን የማሳጠር፣ ማንገቻ የማድረግ፣ ሁሉንም አሟልቶ አለመልበስና ሌሎች ያልተፈለጉ ምልክቶችን በደንብ ልብሳቸው ላይ የመደረብ ህገ ወጥነት እንደሚታይባቸው አብራርተዋል።
ወንዶች ተማሪዎች ደግሞ ሱሪውን በማጥበብና ባልተፈለገበት ቦታ ላይ ዚፕ እንደሚያስገጥሙ፤ ከረባቱንም እንደማያደርጉትና አንዳንዶች ልብሱን የሚለብሱት ትምህርት ቤት በር ላይ ሲደርሱ ብቻ እንደሆነም ጠቁመዋል። ‹‹ነገሩ በዚህ ከቀጠለ ደንብ ልብሱ ይበላሻል።
ክፍተቱን የሚጠቀሙት ሌሎች ያልደረሳቸውን ተማሪዎች እንደ ሽፋን በመጠቀም ነው። ከዚህ አኳያ ትምህርት ቤቱ ክፍተቱን ለመሙላትና የአለባበስ ስነ ምግባርን ለማስጠበቅ ብዙ ሥራ ይጠበቅበታል። ወላጆችም በቂ ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል›› ሲሉ መፍትሔ አመላክተዋል።
ተማሪዎቹ ላይ የተለየ ፍላጎት የሚታይባቸውም ከዕድሜ ጋር ተያይዞ ለፋሽንና መጤ ባህል ተጽእኖዎች ስለሚጋለጡ መሆኑን በመግለጽ፤ ‹‹የተሰፋውን ልብስ በሌላ መልክ ቢቀይሩት ጥብቅ የዲሲፕሊን ዕርምጃ እንደሚያስወስድ ተማሪዎችም ወላጆችም መገንዘብ ይኖርባቸዋል›› ብለዋል።
የአጼ ናኦድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ወይዘሮ ጸሐይ ካሳ በበኩላቸው፤ ዕድሉ ለሁሉም ተማሪዎች መዳረሱ አስደሳች ቢሆንም፤ የተሰጠውን የደንብ ልብስ በአግባቡና አሟልቶ አለመጠቀም ግን ከሥነ ምግባር ውጪ ነው ይላሉ።
እንደ እርሳቸው ገለጻ በአጼ ናኦድ የመጀመሪያ ትምህርት ቤት ውስን ተማሪዎች የተሰጣቸውን የደንብ ልብስ በአግባቡ የመያዝ ችግር እንዳለባቸው ገልጸዋል። ‹‹ከረባቱን በፍጹም አይፈልጉትም።
በር ላይ ጠብቀን ነው ከረባት አድርጉ ብለን የምንቆጣጠራቸው። እርስ በእርሳቸውም ይሰራረቃሉ። የሚሸጡም አሉ። ሲጠፋባቸውም ምን መደረግ እንዳለበትና የጠበባቸው እንዴት ማድረግ እንዳለባቸው የሚጠቁም መመሪያም ለትምህርት ቤቶች አልደረሰም›› በማለት ርዕሰ መምህርቷ በተማሪዎች ደንብ ልብስ ዙሪያ ያለውን ችግር ያብራራሉ።
ትምህርት ቤት ውስጥ ከሚደረገው ቁጥጥር በተጨማሪ ተማሪዎች የተሰጣቸውን በአግባቡ አሟልተው እንዲለብሱ በተለያየ መንገድ ምክር እንደሚያገኙም ገልጸዋል። በትምህርት ቤቱ 90 በመቶ ያህል የደንብ ልብስ ለተማሪዎቹ መዳረሱንና የቀረው ግን አንዳንድ ተማሪዎች ተክለ ሰውነታቸው ስለሚግዝፍ በድጋሚ እየተሠራላቸው መሆኑን አስታውሰዋል።
በአጼ ናኦድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የስነ ዜጋና ሥነ ምግባር መምህር መለሰ አበጀ በትምህርት ቤት ውስጥ ምንም እንኳን ተመሳሳይ ደንብ ልብስ ቢሰጥም ወጥ የሆነ አለባበስ አለመኖሩን በመናገር፤ የተማሪዎች የአለባበስ ሥነ ምግባር እንዳይጓደል የትምህርት ቤት የቁጥጥር ሥርዓትና የወላጆች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ልብስ ማደል ብቻ ሳይሆን ይህንን ጉዳይ ለይቶ ለተማሪዎች ማስገንዘብ እንደሚጠበቅና፤ ዘመናዊነትንና መሰል ዝንባሌዎችን የሚያራምዱ ተማሪዎችን መምከር አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 22/2012 አዲሱ ገረመው