የሕክምናውን ዘርፍ ከሚገዳደሩት እንቅፋቶች መካከል የባለሙያዎቹ የስነምግባር ችግሮች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሕብረተሰቡም በዘርፉ በሚሰማሩ ባለሙያዎች ላይ በርካታ የስነምግባር ችግሮችን እየነቀሰ ያነሳል፡፡
‹‹እዚህ መምጣት የቻለ በሽተኛ ተመስጌን ማለት አለበት፤ ሀኪሞቹም ውብ ናቸው፤ ጆሮ ሰጥተው ያዳምጡሃል›› በማለት ሐሳባቸውን የጀመሩት ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን መጥተው በየካቲት ሆስፒታል የዓይን ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ያገኘናቸው አቶ ተሻገር ዋሴ ናቸው፡፡
የሰው ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በካርድ ክፍል አካባቢ ያሉ ሠራተኞች መሰላቸት እንደሚታይባቸው የሚናገሩት አቶ ተሻገር፤ ‹‹በአብዛኛው በክልል ጤና ጣቢያዎች ተመድበው የሚሠሩ ባለሙያዎች ምራቅ ዋጥ ያደረጉ ባለመሆናቸው ዓይኔን ገልጬ ለመስጠት ፍርሐት አድሮብኛል፤ ይችን የቀረች እይታዬን ቢነሱኝ ምን ይውጠኛል ብዬ ወደ እዚህ መጣሁ›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡
አቶ ተኮላ ሰይድ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ጃማ ወረዳ የጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት የባለሙያዎች የስነምግባር ችግር በጤናው ዘርፍ መንግሥትን ከሚፈታተኑት እንቅፋቶች በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው፡፡
በየትኛውም የሙያ ዓይነት የተሰማሩ አገልግሎት ሰጪዎች ሙያው የሚፈልገውን ስነምግባር መላበስ እንደሚገባቸው የሚገልጹት አቶ ተኮላ፤ የሕብረተሰቡን ጤና በመጠበቅ ላይ በተሰማሩት ባለሙያዎች ዘንድ መልካም ስነምግባርና ጥሩ ተግባቦታዊ ሂደት ሲኖር ደግሞ የታማሚውን ታክሞ የመዳን ሁኔታ በእጅጉ እንደሚያሳድገው ያስረዳሉ፡፡
በጤና ባለሙያዎች ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል አደንዛዥ እጾች( ጫት) መጠቀም፣በሥራ ቦታ በሰዓቱ አለመገኘት፣አለባበስን አለማስተካከል፣ ታካሚን ማመናጨቅ፣ የባህሪ ብስጩነት፣ ከባልደረቦች ጋር ተግባብቶ አለመሥራት፣ ቀና አለመሆን፣ ታማሚውን ፈጥኖ በመረዳት ባህልና ወጉን ተላብሶ ማገልገል አለመቻል፣ ጥቂቶቹ እንደሆኑ አቶ ተኮላ ያብራራሉ፡፡
የባለሙያዎቹ የስነምግባር ችግሮች ተመድበው አገልግሎት እንደሚሰጡባቸው የሥራ ዓይነቶች ሊለያይ ይችላል የሚሉት ኃላፊው፤ አልፎ አልፎም ታማሚን ከልክሎ መድሃኒት እስከ መሸጥ የሚደርስ የከፋ ችግር ያለበት ባለሙያ ይገጥማል ይላሉ፡፡ በተመሳሳይ ባለሙያው የሚሠራበት የጤና ተቋም ደረጃና የትምህርት ደረጃም በባህሪው ዙሪያ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡
የሥራ አካባቢው ምቹነት፣ ያዳበረው ሙያዊ ልምድ፣ የሚደረግለት ክትትልና ድጋፍ፣ ያደገበት ማህበራዊ ሕይወትና ባህል፣ለሙያው ያለው ፍቅር፣ለሰው ልጅ ያለው አመለካከት እና በሙያው ላይ ያለው ብቃት ጭምር ለባለሙያው የሥነምግባር ቅኝት በአዎንታም ሆነ በአሉታ የየራሳቸው አስተዋጽኦ ያበረክታሉ የሚሉት በደብረብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል ጠቅላላ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ከተማው አሰፋ ናቸው፡፡
ዶክተሩ እንደሚሉት፣ የማህበረሰባችን የአስተሳሰብ ደረጃና የአመለካከት ሁኔታ ከአካባቢ አካባቢ እና ከቦታ ቦታ ሊለያይ ቢችልም ወደ ሕክምና ተቋማት ሲመጡ እንዲያክማቸው ያሰቡትን ዶክተር ማግኘት ካልቻሉ አልድንም ብለው የሚደመድሙ ሰዎች መኖራቸውን አንስተው፣ አባቶቻችን ‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ›› ያሉበትን ፋይዳ በማስታወስ፣ ባለሙያው እነዚህን ሰዎች ማከም የሚጀምረው ለዘመናት አብሯቸው የኖረውን አስተሳሰብ ታሳቢ በማድረግ ጭምር እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
ዶክተር ከተማው፤ በሕክምና ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሙያዎች የሙያዊ ስነምግባር ክፍተት ከሚገባው በላይ ሙያዊ አገልግሎቶችን ይጎዳል፤ ከባለሙያው ግለሰባዊ ጥላቻ አልፎ ተቋማዊ ጥላቻን እስከ ማሳደር ይደርሳል፤ በዚህ የተነሳ ሕብረተሰቡ ዘንድ አመኔታን ያሳጣል ይላሉ፡፡
መጠናቸው ሊለያይ ይችል ይሆናል እንጂ የስነምግባር ችግሮች በየትኛውም የዕድሜ ክልሎች በሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ሊታዩ እንደሚችሉ የሚናገሩት ዶክተር ከተማው፤ ወጣት ጀማሪ ሐኪሞች ማህበረሰባዊ የሕይወት ልምዱን እስኪቀስሙ ድረስ ተጋላጭነታቸው ይጨምራል ይላሉ፡፡ ሆኖም በሥራ ገበታቸው ላይ ተከታታይነት ያለው ድጋፍ ከተደረገላቸው ለመለወጥ ፈጣን መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
በአጠቃላይ ታካሚው ከሕመሙ እንዲፈወስ በመጀመሪያ በሀኪሙና በተቋሙ ላይ ሙሉ እምነት ሊያሳድር ይገባል፡፡ በመሆኑም ለሚከታተለው ሀኪም ሙሉ እምነት ማሳደር ይኖርበታል፡፡ እስከዚህ ድረስ ሕይወቱን አምኖ መስጠት የሚያስችል ስነምግባራዊ ቁመና ማየት ይፈልጋል፡፡ ታካሚዎቻችን በተለያየ መንገድ ዓይተውና መዝነው ሊታከሙ እንደሚወስኑ በመግለጽ ስነምግባርን ማስተካከል ከየትኛውም ነገር መቅደም እንዳለበት ዶክተር ከተማው ይመክራሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 22/2012
ሙሐመድ ሁሴን