- ስነተዋልዶ ላይ ያተኮረ የሞባይል መተግበሪያ ተሠርቷል
የሥነ ተዋልዶ ጤና የአቻ ለአቻ ትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ። በወጣቶች የተሠራ የሞባይል መተግበሪያ በሙከራ ትግበራ ላይ ይገኛል።
የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሕይወት ኃይሉ የወጣቶች ስነ ተዋልዶ ጤና ውይይት በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደበት ወቅት እንደገለጹት፤ ወጣቶች በአቻ ለአቻ የመማማሪያ መድረኮቻቸው በሥነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ሲሆን በቴክኖሎጂ ሲታገዝ ደግሞ የበለጠ ውጤታማ ሊያደርግ ይችላል።
የሥነ ተዋልዶ ጤና ትምህርትንም ዘመኑ በፈቀደው መንገድ በሞባይል ቴክኖሎጂ ተደራሽ ለማድረግ የተሠራው የፈጠራ ሥራ ሊበረታታ የሚገባው ነው ያሉት ወይዘሮ ሕይወት፤ ወጣቶች የሚገጥሟቸውን የሥነ ተዋልዶ ጤናዊ እክሎች ፈጠራዊ ክህሎትን በመጠቀም ምላሽ ለመስጠትና መፍትሔ ለማበጀት የተሄደበትን እርቀትም አወድሰዋል።
በቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ማከናወን መቻላቸው ውጤታማነታቸውን በእጅጉ ይጨምራል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ሁኔታዎችን ቀላል፣ ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግ ወጣቶቹ ባሉባቸው ቦታዎች ሆነው የአቻለአቻ መልዕክቶቻውንም መለዋወጥ የሚያስችላቸው በመሆኑ መልዕክቶቹ ፈጥነው ይደርሳሉ፤ ጊዜያቸውን ይቆጥባል፤ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ደወል ይሆናል፤ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በከንቱ የሚያጠፉትን ጊዜ ይቆጥባል፤ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ የሚያስገኝ በመሆኑ ጤናማነታቸው ተጠብቆ ምርታማነታቸው እንደሚጨምርም አስረድተዋል።
በስነተዋልዶ ጤና የአቻ ለአቻ ትምህርትች የሞባይል መተግበሪያ ቴክኖሎጂ የሠራው የአሰላ 10ኛ ክፍል ተማሪ ተካልኝ ገነነው እንደገለጸው፤ በአሰላ ‹‹ሰርቅ የስነተዋልዶና ጤና ማህበር›› ታቅፎ የአቻ ለአቻ ትምህርትን ለወጣቶች በማስተማር እንደሚሳተፍ ተናግሯል።
ተማሪ ተካልኝ እንደተናገረው፤ ወጣቶች ለበርካታ ሰነተዋልዷዊ ችግሮች የተጋለጡ ናቸው፤ ምክንያቱ ደግሞ በአብዛኛው የግንዛቤ እጥረቶች እንደሆኑ አንስቷል። እነዚህን የግንዛቤ ክፍተቶች መሙላት የሚያስችል የወጣቶች ስነተዋልዶ መረጃ በቀላሉና በሰፊው ማግኘት እንዲችሉ ቢደረግ ችግሩን መቀነስና ብሎም መፍታት እንደሚቻል ሁሌም ያሳስበው እንደነበር አብራርቷል።
በዚህ የተነሳም በሞባይል ቴክኖሎጂ የስነተዋልዶ መረጃዎችን ለአቻ ወጣቶች ተደራሽ ለማድረግ መፍጨርጨር እንደጀመረ የሚናገረው ተማሪው፤ አሁን ላይ መተግበሪያውን በመሥራት በሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ የተለያዩ መልዕክቶችን ለወጣቶች በሰፊው ማድረስ የሚያስችል የሞባይል መተግበሪያ እውን አድርጓል። መተግበሪያው አሁን በሙከራ ደረጃ መረጃዎችን ለወጣቶች በማስተላለፍ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይ ወደሙሉ ትግበራው መሸጋገር የሚያስችል አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን ተናግሯል።
የ‹‹ዲ ኤስ ደብሊው›› ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ዳይሬክተር ፈየራ አሰፋ በበኩላቸው ፤ በወጣቶች ስነ ተዋልዶ ጤና፣ በወጣቶች ስብዕና ግንባታ እና በወጣቶች አቅም ግንባታ ላይ በሰፊው የሚከናወኑ የመንግሥት ጥረቶችን መደገፍና ለውጤት ማብቃት የፕሮግራሙ ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ወጣት ተኮር መረጃዎችን ማዳረስና ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችለው ችግር ፈቺ መተግበሪያ እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ አድርገዋል። ምክንያቱም ወጣቶች በመረጃ የጎለበቱና ጤናቸው የተጠበቀ መሆን አለባቸው። ይህ ሲሆን ለራሳቸው፣ለቤተሰቦቻቸው እና ለአገራቸው የሚፈለግባቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችሉ አስረድተዋል።
ይህ የሥነተዋልዶ ጤና የሞባይል መተግበሪያ የቴክኖሎጂ ፈጠራ የመጀመሪያው ያልሆነው ተማሪ ተካልኝ፤ ከዚህ በፊት በተካሄዱ የወጣቶች የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድሮች በአፋሪካ ደረጃ ለሦስት ጊዜያት በመሳተፍ በሁሉም ውድድሮች 3ኛ ደረጃን በመያዝ ያሸነፈ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እጅ ሽልማት መቀበሉም ተወስቷል።
አዲስ ዘመን ጥር 22/2012
ሙሐመድ ሁሴን