ከሰመራ ወደ አሳይታና አፋምቦ ወረዳዎች በሚወስደው አስፓልት መንገድ ግራና ቀኝ ሳይለማ ባክኖ የተቀመጠ ለም አፈር ከአዋሽ ወንዝ ግርማ ሞገስ ጋር ማየት የተለመደ ነው። ይህ ስፍራ ካለመልማቱ ባለፈ ‹‹ፕሮስፒስ ጁሊ ፍሎራ›› በተባለ የአረም ዛፍ ተሸፍኖ ለሰውም ለእንስሳቱም ጉዳትን እንጂ ተጠቃሚነትን ነፍጎ ይታያል።
በብዙ ከሚገለጸው ከዚህ ሁነት መካከል ግን በእነዚህ ሁለት ወረዳዎች ውስጥ ባሉ ዳሌ፣ ሳህሌ እናሁማ ዲይታ ቀበሌዎች የሚከናወነው የስንዴ ልማት ሰርቶ ማሳያ ሥራ የአካባቢውን የሥራ ባህል የቀየረ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም በብዙ ምክንያት ምሳሌ ተደርጎ የሚወሰድ ሆኗል።
አቶ አብዱ ያዩ አንፍሬ እና አቶ ያሲን ሰይድ፣ በዳሌ ቀበሌ በማህበር ተደራጅተው 120 ሄክታር ስንዴ ከሚያለሙ አርብቶ አደሮች መካከል ናቸው። እነርሱ እንደሚሉት፤ አካባቢው ቀደም ሲል በቆሎና ጥጥ የሚመረትበት ቢሆንም ለረዥም ጊዜ በመጤ አረም ተወርሮ ያለ ጥቅም የሚቀመጥ ነበር።
ሆኖም በመንግሥት ድጋፍ በዚህ መልኩ እንዲሆን ሥራው በተጀመረበት ወቅት አካባቢው አረም ለብሶ የነበረ በመሆኑ ከግንዛቤ ክፍተት ጋር ተዳምሮ ለውጤት ይበቃል በሚለው ላይ አለመግባባት ነበር። በሂደት ግን መግባባቱ እየተፈጠረ በጋራ ተቀናጅቶ መስራት ተችሏል። ሥራውም አፋር ላይ ስንዴ እንደሚበቅል በተግባር የታየበት ሆኗል።
እንደ አቶ አብዱ እና አቶ ያሲን ገለጻ፤ አካባቢው ውሃም መሬትም ያለው ቢሆንም፤ አዋሽ ወንዝ ለዘመናት ኅብረተሰቡን እየታዘበው ሲያልፍ ቆይቷል። ይህ ተግባር ግን የማድረግ ይቻላል ልምድ የተገኘበት ብቻ ሳይሆን አዋሽ በትዝብት የሚያልፍ ሳይሆን፤ አፈር እያራሰ የልማት ኃይልና ሲሳይ ሆኗል።
ይኸው ተግባርም ወደሌሎች አካባቢዎች ሊስፋፋ ይገባል። ምክንያቱም በዚህ መልኩ ለስንዴ ልማት ማዋል በመቻላቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም አግኝተውበታል። መስራትና መለወጥ እንደሚቻልም ተገንዝበውበታል፤ የሥራ ዕድል መፍጠሪያም ሆኖላቸዋል።
ከዚህ አኳያ ሥራው የአካባቢውን አፋሮች በእርሻቸውም ሳይጠቀሙ የቆዩበትን ታሪክ ቀያሪና ለቀጣይ ለተሻለ ውጤት እንዲሰሩ ያነሳሳ ሆኗል። ሆኖም አሁንም ሥራውን ዘላቂና የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያስገኝ ለማድረግ ተጨማሪ የባለሙያ ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ የእርሻና መመንጠሪያ ማሽኖች እገዛ ሊደረግ ያስፈልጋል።
በሳህሌ ቀበሌ በማህበር ተደራጅተው ከሚያለሙ ወጣቶች መካከል ዓሊ መሐመድ እንደሚለው ደግሞ፤ ቀደም ሲል በስፍራው ጥጥ እና በቆሎ ነበር የሚለማው። ሆኖም በአካባቢ ጥጥ ያለማ የነበረው ባለሀብት ሥራውን ከተወ በኋላ ስፍራው በአረም ዛፍ ተወረረ።
አሁን መንግሥት ባመቻቸው ዕድል በመጠቀም ወጣቶቹ ተደራጅተው ስንዴ ወደማልማት ገቡ። በዚህ ሂደትም መንግሥት ከአረም ምንጣሮና መሬት ድልደላ ጀምሮ እስከ ዘርና ግብዓት ድረስ ያገዛቸው ሲሆን፤ ሥራውም በአካባቢው ያለውን ውሃም ሆነ መሬት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ከተቻለ ወጣቱ ከራሱ አልፎ ለአገር የሚተርፍ ሥራ መስራት እንደሚችል የታየበት ተግባር ነው።
ይሁን እንጂ ዛሬም የዘመናዊ ማሽነሪና አሠራር ጋር ችግር አለ። ለምሳሌ፣ የመስኖ ቦዮችን በባህላዊ መንገድ በመገደብና በመልቀቅ ነው የሚገለገሉት። በመሆኑም ይህ ዘመናዊ እንዲሆን፤ ሌሎች ሥራውን በዘላቂነት ማከናወን የሚያስችሉ ማሽነሪዎች እንዲኖሯቸው መንግሥት እንዲደግፋቸው መልዕክታቸው ነው።
አቶ አብደላ አደን አብደላ፣ በአፋምቦ ወረዳ የሁማ ዱይታ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በአካባቢው ስንዴ ይመረታል የሚል እምነት ስላልነበራቸው በተወሰነ መልኩ በቆሎና ጥጥ ከማልማት የዘለለ ስፍራው በመጤ አረም የተወረረ ስለነበር አገልግሎት ሳይሰጥ ቆይቷል። በግብርና ባለሙያዎች ታግዘው ወደሥራ ከገቡ በኋላ ግን የእነርሱንም አመለካከት የለወጠ፤ ሌሎችንም እንደ እነርሱ ለመስራት ያነሳሳ ውጤት ማየት ችለዋል።
ይሄን ማየታቸው ደግሞ እነርሱም የበለጠ ለመስራት የተነሳሱ ሲሆን፤ በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ እያፈራረቁ ለመስራት አቅደዋል። ሆኖም ለሥራቸው ቀጣይነት ግን የተጠናከረ የባለሙያና ማሽነሪ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።
በወረር ግብርና ምርምር የመስኖ ልማት ባለሙያ የሆኑት አቶ ገብረማርያም በንቲ እንደሚሉት፤ አካባቢው ቀድሞ ስንዴን በእርዳታ ከሚያገኘው የዘለለ እንደ ሰብል አይቆጥረውም ነበር። የስንዴ ልማት ሰርቶ ማሳያውን ለመተግበር ሲንቀሳቀሱም መሬታችንን ልታበላሹብን ነው የሚል ተቃውሞም ገጥሟቸው ነበር።
ሆኖም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ በመሰራቱ ተባባሪ ሆነው ውጤት ማየት ተችሏል። በታየው ውጤትም ሲቃወሙ የነበሩ ሁሉ ለማልማት መጠየቅ ጀምረዋል። ሆኖም አሁን ባለው ሂደት ሥራው አድካሚና ለመንግሥትም ወጪ የሚያበዛ እንደመሆኑ በቀጣይ ባለሀብቱ በስፋት እንዲሳተፍበት ዕድል ሊፈጠርለት ይገባል። እስከዚያው ግን ኅብረተሰቡን በአግባቡ መደገፍና የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ማገዝ ያስፈልጋል።
የወረር ግብርና ምርምር ተቋም ተመራማሪ እንዲሁም የዱፍቲ፣ አሳይታና ተንዳሆ የስንዴ ማስፋፋት ሥራ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዘርዓይ ዘለቀ እንደሚሉት፤ በአካባቢው ከሰፊ ሰርቶ ማሳያ ሀሳብ ሥራው የተጀመረ ቢሆንም፤ አሁን ያለበት ደረጃ ለማድረስ በርካታ ውጣ ውረድ ታልፎበታል።
ቦታውም የተሻለ ውሃና መሬት ያለ ቢሆንም አካባቢው ከልማት ይልቅ በመጤ አረም ዛፍ ተወሮ ለኅብረተሰቡም ለአካባቢውም ጥቅም ሳይሰጥ ቆይቷል። አሁን የታየው ልማትም በኅብረተሰቡ ተሳትፎና በመንግሥት ድጋፍ ተመንጥሮና መሬቱ ተደልድሎ የተከናወነ ሲሆን፤ በአሳይታ ወረዳ በዳሌ ቀበሌ 212 ሄክታር እንዲሁም በአፋምቦ ወረዳ ሁማ ዱይታ ቀበሌ 62 ያክል ሄክታር መሬት ታርሶ ተዘርቷል።
ይህም ከአካባቢው ኅብረተሰብ ተጠቃሚነት ባለፈ አገራዊ ፋይዳው የጎላ ሲሆን፤ ዓመታዊ የስንዴ ፍጆታን ለማሟላት ከውጭ ሲገባ የነበረውን ምርት ከመተካት አኳያ አበረታች ውጤት የታየበትም ነው። ሆኖም አሁንም ከቴክኖሎጂም ሆነ ማሽነሪ አኳያ ኅብረተሰቡ የበለጠ ሊደገፍና ሥራው ዘላቂነት እንዲኖረው ከማድረግ አኳያ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 22/2012
ወንድወሰን ሽመልስ