አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በቅርቡ ከታገቱት የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወላጆች ጋር ተወያዩ።
በውይይቱም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚልና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በተጨማሪ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተማሪዎቹ የትውልድ ቦታ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የተማሪ ወላጆች በዚህ ወቅት የልጆቻቸው አድራሻ እስከጠፋበት ዕለት ድረስ የነበራቸው የስልክ ልውውጥ ምን እንደሚመስልም ጉዳዩን በሚመለከት የተቋቋመው ግብረ-ኃይልን ለሚመሩት ኃላፊዎች አብራርተዋል።
አቶ ንጉሱ ጥላሁን ውይይቱን አስመልክተው እንደተናገሩት፥ ወላጆቹ በቅድሚያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጋር በመገኘት ስለሁኔታው ተወያይተዋል።
ግብረ-ኃይሉን የሚመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በነበራቸው ቆይታም መንግሥት የታገቱ ተማሪዎችን ለማስፈታት እያከናወነው ያለውን ተግባር ለወላጆች በዝርዝር እንዳብራሩላቸው ነው የተናገሩት።
በውይይቱም ከወላጆች ለቀጣይ ሥራ የሚሆን መረጃ መገኘቱንም ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በታገቱ ተማሪዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ የሚያሳይ የተረጋገጠ መረጃም ሆነ ማስረጃ አለመኖሩን ለወላጆቻቸው ማስረዳታቸውንም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።
መንግሥት ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ ሲባል በጥንቃቄና አስተውሎት እየሠራ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ችግሩን ለመፍታት ወላጆች በምን መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ጭምር ምክክር መደረጉን ነው አቶ ንጉሱ የገለጹት።
በአጠቃላይ በመድረኩ የጸጥታ መዋቅሩና የፖለቲካ አመራሩ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ ያለምንም ዕረፍት እየሠራ መሆኑ ተገልጾ መተማመን ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።
የታገቱ ተማሪ ወላጆች በበኩላቸው መንግሥት በአካል በማግኘት ስለአወያያቸው ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱን ተገንዝበናል ነው ያሉት።
በውይይታቸውም መንግሥት ጉዳዩን በሚመለከት እስከአሁን ያከናወነውን ተግባር መረዳታቸውን ገልጸዋል።
መንግሥት ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት ልክ ከሠራ ልጆቻቸውን የማግኘት ተስፋቸው ትልቅ እንደሆነም ያላቸውን እምነት መግለጻቸው ኢዜአ ዘግቧል።
መንግሥት በቅርቡ በደምቢዶሎ አካባቢ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር በመሸሽ ላይ ሳሉ የታገቱትን ለማስለቀቅ ሦስት ቡድኖችን አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
አዲስ ዘመን ጥር 22/2012