ወይዘሮ ለምለም ቢያድግልኝ የካቲት 12 ሆስፒታል በሪፈር የተላኩ ታካሚ ናቸው። ለአገልግሎት በገቡባቸው ክፍሎች የነበረውን የሕክምና እንክብካቤ ያመሰግናሉ። ተመርምረው ጨርሰው መድሐኒት እንዲገዙ ማዘዣ ተጽፎላቸዋል። መድሐኒቱን በግቢው መድሐኒት መሸጫ ማግኘት ባለመቻላቸው ከግል መድሐኒት ሱቆች ለመግዛት በመሄድ ላይ መሆናቸውን ነግረውናል።
‹‹ ቅድም መጥቼ እኮ ያላዳረስኩት ‹ፋርማሲ› የለም። ወረቀቱን በግድ አይተው አይተው የለም ይሉኛል። መጨረሻ ላይ ለካ እንደ እኔው መድሐኒት ሻጭዎቹም አልነበባቸው ብሎ ኖሯል። ተመልሼ አስቀይሬ መምጣቴ እኮ ነው።›› ሲሉ የሕክምና በተለይም የመድሐኒት ማዘዣ ወረቀቶች ለማንበብ አዳጋች መሆናቸውን ነግረውናል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ትምህርት ቤት ‹‹የፋርማሲ›› ትምህርት ክፍል መምህሩ ከበደ ወንዱ እንዳሉት፤ የመድሃኒት ማዘዣ ወረቀቶች ሙሉ መረጃ መያዝ አለባቸው። የጤና ተቋሙን ስም፣አድራሻ(መገኛ አካባቢ፣ ስልክ ቁጥር ሌሎችም) እና ‹‹ሎጎ›› ማካተት አለባቸው።
በተጨማሪም የታካሚውን ሙሉ መረጃ ማለትም፡- ሙሉ ስም፣ ዕድሜ፣ ጾታ፣ ቁመት፣ ክብደት፣ ስልክ ቁጥር በተገቢው መስፈር(መጻፍ) አለባቸው። የሚገዛው መድሐኒት ዝርዝር ይሰፍራል(ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ)፤ የመድሐኒቱ ስም፣ መጠን(በሚሊ ግራም/በግራም)፣ የሚሰጥበት መንገድ(በአፍ፣ በፊንጢጣ፣ በደም ስር…ሌላም)፣ የሚሰጥበት ቆይታ፣ መጠን /ምን ያህል ነው ?(የታብሌቱ ቁጥር) እና በሌሎች መለኪያዎችም ተመጥኖ በትክክል በማዘዣ ወረቀቱ ላይ መስፈር እንዳለባቸው አብራርተዋል።
መድሃቱን የሚያዘው ባለሙያም ስሙን እስከ አባቱ እና ፊርማውን መጻፍ አለበት። በኢትዮጵያ የተለመደ ባለመሆኑ እንጂ የሙያ ፈቃድ የምዝገባ ቁጥሩን ጭምር መጻፍ ግዴታው ነው። የተቋሙ ማህተም ሊያርፍበት ይገባል። በመጨረሻም መድሐኒቱን የሚያድለው ‹‹ፋርማሲ›› ባለሙያ ስም መስፈር አለበት። አንድ የመድሐኒት ማዘዣ ወረቀት እነዚህን ነገሮች ማሟላት እንዳለበት አቶ ከበደ ተናግረዋል።
አቶ ከበደ በማብራሪያቸው እንዳነሱት፤ እንደ መልክ ሁሉ የእጅ ጽሑፍም የሚለያይ በመሆኑ እንጂ እንዳይነበብ የሚያደርግ አሠራር በሕክምና ትምህርት ውስጥ ፈጽሞ የለም። የመድሐኒቶች ስም በአህጽሮት ሊጻፍ ይችላል። ከዚያ ባለፈ ግን ሆን ተብሎ እንዳይነበብ ማድረግ አይቻልም፤ ሊያስጠይቅም ይችላል።
የታካሚው ቁጥር ብዙ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በፍጥነት ሲጻፍ ለመነበብ የሚያዳግቱ ችግሮች ይፈጠራሉ። በሰፊውም የሚስተዋል ችግር ነው። በዚህ ምክንያት መድሐኒቶች ሲታዘዙ የሚፈጠር ትንሽ ስህተት ከባድ መከራን ያስከትላል።
በሕክምና ትምህርት ውስጥ በመሰለኝ አይሰጥም። የስህተትም ትንሽ የለውም። በመሆኑም አዳጋች ሁኔታዎች ሲገጥሙ ማዘዣውን ከሰጣቸው ባለሙያ እንዲያስቀይሩ መደረግ ይኖርበታል፤ይደረጋልም ነው ያሉት አቶ ከበደ።
በሙያ ደረጃ ታካሚው እንዳያነበው ማድረግ አይፈቀድም። እንደውም ታካሚው እያንዳንዱን መረጃ በግልጽ እንዲያውቀውና ግልጽ እንዲሆንለት ባለሙያው አብራርቶ ማስረዳት እንደሚኖርበት መምህሩ አብራርተዋል።
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ክፍል መምህሩ ዶክተር መልካሙ በድሞ በበኩላቸው፣በሕክምና ትምህርት የስነምግባር ጉዳይ ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ ይገልጻሉ። ታካሚው የማዘዣ ወረቀቱን ይዞ ከተለያዩ መድሐኒት መሸጫዎች ሞክሮ ሊነበብ ካልቻለ አስቸጋሪ ነው። ቢያንስ በእጅ ጽሑፍ አንዱ ከሌላው የሚለያይ ቢሆንም ሁሉም ሊያነበው አዳጋች እና አጠራጣሪ ከሆነ ተመልሶ ማዘዣው እንዲስተካከል መድሐኒት ሻጮች ታካሚውን መምከር እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ዶክተር መልካ እንደለገለጹት፤ አሁን በሚታየው የአሠራር ሂደት የተጠያቂነት አሠራሩ ደካማ በመሆኑ እና ታካሚውም መብቱን የመጠየቁ ልምድ የጎለበተ ባለመሆኑ እንጂ ጊዜውን እና ድካሙን አስልቶ ባለሙያውን ተጠያቂ ማድረግ ይችላል።
ምክንያቱም ታካሚው የመድሐኒት ማዘዣውን ይዞ ከመረጠው ቦታና አገር ለመግዛት ከሄደ በኋላ ችግሩ ቢፈጠር እንግልቱና ድካሙ የበረታ ይሆናል። ስለዚህ በሕክምና ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከሚያስተውሉት ስህተት ፈጥነው መማርና በሌሎች ላይ እንዳይደገም ለሙያቸው የገቡትን ቃል ማስታወስ ይገባቸዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 22/2012
ሙሐመድ ሁሴን