አዲስ አበባ፡- የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትየጵያ እንዳይገባ አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ። በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መንገደኞች የሙቀት መጠናቸውን እየተለኩ እንዲገቡና ምልክቱ የታየባቸው ደግሞ የህክምና መስጫ ቦታዎች ዝግጅት መደረጉን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ ሰሞኑን ለተለያዩ መገኛኛ ብዙሃን በሰጡት ገለጻ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከቻይና እና አጎራባች አገሮች ለሚመጡ መንገደኞች የሙቀት መጠናቸውን እየተለኩ እንዲገቡ እየተደረጉ ሲሆን በበሽታው የተያዙ ከአጋጠሙና የሚጠረጠሩ ካሉ መታካሚያ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል። የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ካለባቸው ሀገራት የመጡ መንገደኞች አድራሻቸው ታውቆ ክትትል እየተደረገባቸው ነው። ህክምናውን ለሚሰጡ የጤና ባለሙያዎችም ስልጠና መስጠት ተጀምሯል።
እስከአሁንም ከቻይና የመጡ አራት የተጠረጠሩ ሰዎች በተለየ ማከሚያ ማዕከል ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸው ከተለዩት ተጠርጣሪዎች ሁለቱ የሳል እና የሙቀት ምልክት ያሳዩ ቢሆኑም በአሁኑ ጊዜ አራቱ ተጠርጣሪዎች ከበሽታው ነፃ መሆናቸው በተደረገው ምርመራ መረጋገጡን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሊያ ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ በበሽታው የሚጠረጠሩ ታካሚዎችን የሚይዝ የለይቶ ማከሚያ የህክምና መዕከል በቦሌ ጨፋ ተዘጋጅቶ አስፈላጊው የህክምና እና ልዩ ልዩ ግብአቶች እየተሟሉ ይገኛሉ። በጽኑ ለታመሙና ከፍተኛ የህክምና ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የተለየ ክፍል ተዘጋጅቷል።
በጤና ሚኒስቴር የሚመራ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ የወረርሽ ቅድመ ዝግጅት ብሄራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የመጀመሪያ ውይይቱን ያደረገ ሲሆን በግብረ ኃይሉ ከተካተቱት ተቋማት መካከል፤ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ቀይ መስቀል፣ ባህል እና ቱሪዝምና ኢሚግሬሽን ይገኙበታል። እንዲሁም በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚመራ የቴክኒካል ቡድን ተቋቁሞ ሥራውን የጀመረ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር በድረ ገጹ አስፋሯል።
በሽታው በጉንፋን መልክ ጀምሮ የመተፈንሻ አካላትን የሚያጠቃ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ በሽታው እንዳይተላለፍ ለመከላከል እጅ መታጠብ አስፈላጊ መሆኑንና ከቻይና መጥተው ይህ ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች ካሉ ህብረተሰቡ ጥቆማ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
በዓለም የጤና ድርጅት ዕለታዊ ሪፖርት መሰረት በሽታው በወረርሽኝ መልክ ሪፖርት መደረግ የጀመረው ከታኅሣሥ 24/ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቻይና አንድ ግዛት ውስጥ የተቀሰቀሰው የኮሮና ቫይረስ መላ ቻይናን ማዳረሱና በበሽታው የሞቱ ሰዎች ቁጥርም 170 መድረሱ ተነግሯል። የቻይና የጤና ባለስልጣናት እንዳስታወቁት በአገሪቱ እስከ ትናንት ድረስ 7 ሺህ 711 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል።
አዲስ ዘመን ጥር 22/2012