አዲስ አበባ:- 60 በመቶ የሚሆኑ ህጻናት ስለማንነታቸው የሚገልጽ ህጋዊ መታወቂያ (legal identity) እንደሌላቸው የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ገለጸ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጅብ ጀማል የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በትናንትናው ዕለት በኤጀንሲው ድንገተኛ ምልከታ ባደረጉበት ወቅት የመጀመሪያው መንፈቅ አመት ያከናወናቸውን ተግባራት ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል።
በዚህ መድረክ ህገ መንግስቱ አንድ ህጻን ከተወለደ በኋላ ስም የማግኘት፣ ወላጆቹን የማወቅ፣ ዜግነት የማግኘት እንዲሁም የተወለደበት ቦታና ቀን መታወቅ እንዳለበት የሚደነግግ ቢሆንም፤ በአገሪቱ 60 በመቶ የሚሆኑ ህጻናት በህግ ከተቋቋመ ተቋም ስለማንነታቸው የሚገልጽ ህጋዊ መታወቂያ (legal identity) የላቸውም።
ኤጀንሲው ከሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መጀመሩን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ማዕከላዊ እስታቲክስ ኤጀንሲ ያወጣውን ግምታዊ ስሌት መነሻ በማድረግ ባለፉት አምስት አመታት ኤጀንሲው በአገሪቱ ይህን ዓለም ለሚቀላቀሉ ለ12 ሚሊዮን ህጻናት የልደት የምስክር ወረቀት እሰጣለሁ ብሎ አቅዶ፤ ነገር ግን በተለያዩ ችግሮች ሁለት ሚሊዮን ለሚሆኑ ህጻናት ነው የልደት የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ ማድረግ የቻለው።
ስለዚህ ከእቅዱ አንጻር 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት በወሳኝ ኩነት መረጃቸው አልተመዘገበም ማለት ነው። ይህ መረጃ እንደሚያሳየው በአገሪቱ 60 በመቶ የሚሆኑት ልጆች ህጋዊ መታወቂያ እንደሌላቸው ያሳያል ብለዋል።
ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን እስከ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ዓለም ላይ ህጋዊ መታወቂያ የሌለው ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ በአፍሪካ በተለይ ከሳህራ በታች ያሉት አገሮች 700 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ህጋዊ መታወቂያ (legal identity) እንደሌላቸው አቶ ሙጅብ ገልጸው፤ ከሳህራ በታች ካሉ አገሮች መካከል አብዛኛውን ከ18 ዓመት እድሜ በታች የሆኑ ዜጎች ህጋዊ መታወቂያ ከሌላቸው አገሮች ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። ስለዚህ ተቋሙ የወሳኝ ኩነት ምዝገባን እንደ አገር ለማሳደግና ለማሻሻል አንድ አገር አቀፍ ጥናት በቅርቡ እንደሚያስጠና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ የአንድ ሰው የማንነቱ መታወቂያ ዜግነቱ፣ የትውልድ ቦታው፣ ስሙ፣ ጾታው፣ የተወለደበት ጊዜ፣ ቦታ እንዲሁም ወላጆቹ ናቸው። ስለዚህ እንደተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትርጓሜ አንድ በህግ የተቋቋመ ተቋም እነዚህን አንድን ሰው የሚገልጹ መረጃዎችን መዝግቦ ለግለሰቡ ህጋዊ መታወቂያ ሲሰጥ፤ ያሰው ህጋዊ መታወቂያ (legal identity) አለው ይባላል ብለዋል።
ስለዚህ ኤጀንሲው ከውልደት እስከ ሞት ያለን የአንድን ግለሰብ ህጋዊ መታወቂያ የሚሰጥ እና የሚሰርዝ ተቋም መሆኑን አውስተው፤ በኢትዮጵያ አንድ ዜጋ 18 ዓመት ካልሞላው የቀበሌ መታወቂያ አያገኝም። በመሆኑም አንድ እድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ህጋዊ መታወቂያው የልደት የምስክር ወረቀቱ እንደሆነ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2012
ሰለሞን በየነ