አዲስ አበባ፡- አዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጤናማ የእናትነት ወርን ደም በማሰባሰብና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብር አስታወቀ፡፡ ህብረተሰቡ ደም በመለገስ ከወሊድ ጋር በተያያዘ በደም መፍሰስ የሚሞቱ እናቶችን እንዲታደግ ጥሪ አቀረበ፡፡
በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የቤተሰብ ጤና ክብካቤ ቡድን መሪ ወይዘሮ ቤተልሄም ታዬ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለጹት ጤናማ የናትነት ወርን ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ እናቶችንና ህፃናትን ለመታደግ ትምህርታዊ ቅስቀሳዎችን በማከናወን ከነገ ከጥር 1 ቀን እስከ 30 ይከበራል፡፡ በተለይ ደግሞ ጥር 8 ቀን 2011ዓ.ም በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ በደም ልገሳ ፕሮግራም ስለሚካሄድ አስፈጻሚ አካላትና ባለድርሻ አካላት በእነርሱ በኩል የሚጠበቀውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የቡድን መሪዋ እንዳሉት በጤና ጣቢያዎችና በሆስፒታሎች እናቶችን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ዝግጅቶች የሚከናወኑ ቢሆንም ህክምና ተቋም የማይሄዱትንም በመገናኛ ብዙሃንና በተለያየ የመረጃ ማስተላለፊያ ዘዴዎች በመጠቀም መረጃዎች ተደራሽ ይሆናሉ፡፡ እናቶች በጤና ተቋማት ቅድመና ድረ ወሊድ ክትትል በማድረግ እራሳቸውም ሆኑ ህጻናት ለከፋ ችግር እንዳይዳረጉ በማድረግ በወሊድ ምክንያት እናትም ልጅም እንዳይሞቱ ለማስቻል ነው፡፡
የቡድን መሪዋ ወደፊት እናት ይሆናሉ ተብለው ከሚታሰቡት ወጣቶች ጀምሮ በሚከናወነው በዚህ ስራ ለውጥ ለማምጣት አምና ከወጣቶች ስነተዋልዶ ጤና ጋር በተያያዘ በተከናወነው የንቅናቄ መድረክ ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር መቻሉንና ግንዛቤ የመፍጠሩ ስራ ቢጠናከርም ለስራው አጋዥ የሆኑ መሰረተ ልማቶችንም አብሮ የማሟላቱ ተግባር ሊታሰብበት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የቡድን መሪዋ እናቶችን ከቤት ወደጤና ተቋም ለማድረስ በከተማዋ ምቹ ያልሆኑ መንገዶች መኖራቸውንና የመንገዶች መጨናነቅ እንዲሁም የህክምና መሳሪያዎች በበቂ አለመኖርና ረጅም አገልግሎት የሰጡ የጤና ተቋማት ሰፊ ቁጥር ያለው ተገልጋይ ካለማስተናገድ ጋር ተያይዞ ተግዳሮቶች መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡
በከተማ የሚኖሩ እናቶች ሁሉም የተሻለ ግንዛቤ አላቸው ለማለት እንደማያስደፍርም ያሉት የቡድን መሪዋ፤ ሩሩህና አክባሪ የሆነ የጤና ባለሙያ ለመፍጠር በንቅናቄው ስራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በዓለም ጤና ድርጅት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አማካሪ ዶክተር አሊ አህመድ እንደገለጹት ከወሊድ ጋር በተያያዘ እናቶችን ለሞት የሚዳርጋቸው፣ በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት ከማህፀን ደም መፍሰስ፣ ኢንፌክሽን፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣የጠና ምጥ ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ ወደ 70 በመቶ የሚሆኑት እናቶች የሚሞቱት ከወሊድ በኃላ በሚያጋጥም መድማት ሲሆን፤ እናቶች በቤታቸውና ህክምና ተቋም ከደረሱ በኋላ በሚፈጠር መዘግየት ለሞት ይዳረጋሉ፡፡
እንደ ዶክተር አሊ ማብራሪያ፤ እናቶች 67በመቶ በቤት ወስጥ፣49 በመቶ በህክምና ተቋማት38በመቶ በትራንስፖርት ላይ ይዘገያሉ፡፡ከ2006ዓ.ም እስከ 2010ዓ.ም ባሉት መረጃዎች እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት እናቶች ለሞት የተዳረጉት በመዘግየት ነው፡፡
ባለፉት ጊዜያት ከወሊድ ጋር በተያያዘ ከአንድ ሺ እናቶች ስድስት መቶዎቹ ይሞቱ እንደነበር ዶክተር አሊ አስታውሰው፣ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በተሰሩት ስራዎች ወደ 410 ዝቅ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የበለጠ መሰራት እንዳለበትና አብዛኞቹም ግንዛቤ በመፍጠር የሚፈቱ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
ጤናማ የናትነት ወር ‹‹በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን በጋራ እንታደግ››በሚል መሪቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ደግሞ ለአምስተኛ ጊዜ የሚከበር ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2011
በለምለም መንግስቱ