- l ከ 400 በላይ ያገለገሉ አውቶብሶች ለሸገር ዳቦ ማከፋፈያነት ሊውሉ ነው
አዲስ አበባ:- የሸገር ዳቦና የዳቦ ዱቄት ፋብሪካ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ ከዳቦ ማምረት እስከ ማከፋፈል ድረስ ባለው ሰንሰለት ለ20 ሺ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ገለጸ። ከ400 በላይ ያገለገሉ የአንበሳ የከተማ አውቶብሶች ለዳቦ ማከፋፈያነት ሊውሉ ነው።
የጽህፈት ቤቱ የፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊ ወይዘሪት ፌቨን ተሾመ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል በሆነው ሆራይዘን ፕላንቴሽን ኩባንያ አማካኝነት እየተገነባ ያለው የሸገር ዳቦና የዳቦ ዱቄት ፋብሪካ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ፤ በመዲናዋ የሚስተዋለውን የዳቦና የዱቄት አቅርቦት ችግር መቅረፍ ከማስቻሉ በላይ ከዳቦ ማምረት እስከ ማከፋፈል ድረስ ባለው ሰንሰለት ለ20 ሺ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል።
እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ፤ በመዲናዋ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋትና ማህበረሰቡ ዳቦ፣ ዘይት፣ ስኳርና ዱቄት የመሳሰሉ ለእለት ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን ለመግዛት በረጃጅም ሰልፎች ጊዜውን ከማባከኑም በላይ ብዙ ወጪ ያወጣል ፡፡ የከተማ አስተዳደሩም ቢያንስ በዳቦ እና ዱቄት ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረትና ረጃጅም ሰልፎችን ለመቅረፍ የተለያዩ ባለሀብቶችን ወደ ኢንቨስትመንቱ እንዲገቡ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።
በዚህ ድጋፍም ከወራት በፊት በሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል በሆነው ሆራይዘን ፕላንቴሽን ኩባንያ አማካይነት ወደ ግንባታ የገባው የሸገር ዳቦና የዳቦ ዱቄት ፋብሪካ ግንባታ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ፋብሪካው ወደ ስራ ሲገባ በሰዓት 80 ሺ ዳቦ የሚያመርት ሲሆን፤ ምርቱም ዝቅተኛውን የማህበረሰብ ክፍል ባገናዘበ ዋጋ የሚያከፋፍል ይሆናል። ይህም በከተማው የሚስተዋለውን የዳቦ አቅርቦት ማነስና የዋጋ ንረት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከመቅረፉ በላይ፤ ከዳቦ ማምረት እስከ ማከፋፈል ድረስ ባለው ሰንሰለት ለ20 ሺ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ለረጅም ጊዜ ከስራ ውጭ የነበሩ 420 ያገለገሉ አንበሳ የከተማ አውቶብሶችም ለሸገር ዳቦ ማከፋፈያነት ለማዋል የተለያዩ የማስዋብና የማስጌጥ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሪት ፌቨን፤ በአደጉ አገሮች ተንቀሳቃሽ ሱቆች የተለመዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአውቶቡሶቹ ላይ ወጣቶች ተደራጅተው ዳቦ በማከፋፈል የስራ እድል የሚፈጠርላቸው ሲሆን፤ በ 116 ወረዳዎች የዳቦ ማከፋፋያ ማዕከል ሆነው ስለሚያገለግሉ ማህበረሰቡ በአቅራቢያው ዳቦን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመት እንደሚያስችሉ አስገንዝበዋል።
የሆራይዘን ፕላንቴሽን ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፤ የፋብሪካው የግንባታ ስራ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ማሽኖች ከጣሊያን አገር ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ሲሆን የተወሰኑት ወደ ፕሮጀክቱ ሄደዋል ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ሞጆ ደረቅ ወደብና ጅቡቲ ወደብ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
የመዲናዋን ማህበረሰብ የዳቦ ጥያቄ ለመመለስ ሼህ ሙሀመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ የፕሮጀክቱን ሙሉ ወጪ በመሸፈን እንዲገነባ ማድረጋቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ በሚቀጥለው ወር የማሽን ተከላ ስራው ተጠናቆ ወደ ምርት ይገባል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በ40 ሺ ካሬ ሜትር ወይም አራት ሄክታር ላይ ያረፈው የሸገር ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ እስከ አሁን ለግንባታው ከ 900 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በፕሮጀክቱ ስራ 450 ሰዎች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፤ በመጪው ወር ፋብሪካው ሲጠናቀቅም በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጠርላቸው ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 20/2012
ሶሎሞን በየነ