አዲስ አበባ፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅንጅትና ግንዛቤ አናሳ መሆን የትምባሆ ቁጥጥር ስራውን እየፈተነው እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ መድሃኒት፣ ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ጠቆመ፡፡
ባለስልጣኑ የግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸሙን ትናንት ከባለድርሻ አካላት ጋር ሲገመግም በትምባሆ ቁጥጥር የተሰሩ ስራዎችን በማስመልከት የባለስልጣኑ የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያ አቶ አሸናፊ ደመቀ፤ ምክር ቤቱ በውበት መጠበቂያ ምርቶች 100 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጨመር ሃሳብ ሲያቀርብ፤ የትምባሆ ምርት ላይ 20 እና 30 በመቶ ብቻ እሴት ታክስ እንዲጨመር ሃሳብ መቅረቡ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ሲጋራ ለጤና ጠንቅ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ የጤና፣ የኢኮኖሚ፣ የስነልቦና፣ የፖለቲካ ቀውሶችን የሚያስከትል፣ አካባቢን የሚበክል መሆኑን ተናግረው ፤ በአደጉት አገራት 10 በመቶ የሲጋራ ተጠቃሚነት ሲያድግ፤ በአንጻሩ በማደግ ላይ ባሉ አገራት 60 በመቶ በማሻቀቡ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
የአጫሾችን ቁጥር ለመቀነስና አዳዲስ አጫሾች እንዳይገቡ ለመከላከል ከሚያስችሉ ተግባራት መካከል ኤክሳይዝ ታክሱን ከፍ ማድረግ በመሆኑ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ አቶ አሸናፊ አመልክተዋል፡፡
ሕግን ተላልፈው የሚገኙ አካላትን ተጠያቂ በማድረግ ረገድ የፍትሕ አካላት ተባባሪ አይደሉም ያሉት አቶ አሸናፊ፤ ግንዛቤ ኖሯቸው በቅልጥፍና ያለማስኬድ ችግር ለስራው ተግዳሮት ሆኗል ብለዋል፡፡ የጸጥታ አካላት በማታ ቁጥጥር ስራው ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ለትግበራ ፍቃደኛ አለመሆናቸው እንቅፋት መሆኑንም አክለዋል፡፡
በቀጣይነትም የቁጥጥር ስራውን በቀንና በሌሊት ፈረቃ እንደሚያጠናክር፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የብዙ ወንጀሎች መፈጠሪያ እንዳይሆኑ ሕብረተሰቡን በማስተባበር ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል፡፡ አንዳንድ የታክሲ አሽከርካሪዎች መኪና ውስጥ የሚያጨሱ መኖራቸውን በመጠቆም፤ የተሳፋሪዎች መብት መከበር ስላለበት ከትራንስፖርት ተራ አስከባሪዎችና ከስምሪት ሰራተኞች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ድንገተኛ የምሽት ትምባሆ ቁጥጥር በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ ለመተግበር መታቀዱንም አክለዋል፡፡
በምግብና መድሃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 ዙሪያ ለተለያዩ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸው፤ በማታና በቀን ፈረቃ ሆቴሎች፣ ካፌና ሬስቶራንቶች፣ ባርና ሬስቶራንቶች እንዲሁም ግሮሰሪዎች ላይ በድምሩ በሶስት ሺ 543 ድርጅቶች በአዋጁ መሰረት ከትምባሆ ነጻ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የቁጥጥር ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡ ትምባሆ በነጠላ የሚሸጡ መደብሮችን ለመቆጣጠርም 167 ሱቆች ላይ ቁጥጥር መደረጉንም አንስተዋል፡፡
በትግበራውም 36 ድርጅቶች ላይ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መጻፉን፣ 13 ድርጅቶች መታሸጋቸውን አብራርተዋል፡፡ ሲጋራና ሺሻ ያስጨሱ ከተገኙ ድርጅቶችም 88 ሺ 500 ብር በቅጣት መሰብሰቡን ተናግረው 267 የሺሻ ዕቃዎችም ተወግደዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የሐሺሽ ቅጠል በቅሎ በመገኘቱ ከፍትሕ አካላት ጋር በመቀናጀት የማስወገድ ስራ ቢሰራም ፤ ሰዎቹንም ለመቅጣት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸው፤ በአንጻሩ ግን የተሻለ አዋጅና የሕብረተሰቡ ግንዛቤ እየጨመረ መምጣቱን እንደ ጥሩ አጋጣሚ አንስተዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የዓለም አንድ ሶስተኛው ሕዝብ ትምባሆ ያጨሳል፣ ትምባሆ በማምረትና በማጨስ በዓለም ቀዳሚ የሆነችው ቻይና ስትሆን ከአፍሪካ ሞሮኮ ከፍተኛ የአጫሾች ቁጥር በመያዝ ትጠቀሳለች፡፡ ኢትዮጵያ አምስት በመቶ (3ነጥብ 4 ሚሊዮን) አጫሾችን በመያዝ የመጨረሻ ደረጃ ይዛለች፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 20/2012
ዘላለም ግዛው