አዲስ አበባ፦ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የወንጀል ህጉን ለማስከበርና የወንጀል ፍትህ አስተዳደሩን ውጤታማነት ለማሳደግ ሰፊ ጥረቶችን እንዳደረገ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለጸ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ 2012 በጀት ዓመት የ6 ወር የዕቅድ አፈፃፀሙን ባቀረበበት ወቅት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ እንዳሉት፤ ባለፉት 6 ወራት የወንጀል መከላከል ስራዎችን ውጤታማ እንዲሆኑ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው፤ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ወንጀልና የወንጀልን ስጋት ለመቀነስ የሚያግዙ ትምህርትና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት መሰራቱን አብራርተዋል፡፡
በሁሉም የወንጀል አይነቶች የማጣራት ምጣኔ መቶ በመቶ ለማድረስ ታቅዶ መሰራቱንና በአሁኑ ወቅትም የምርመራ ሂደታቸው የተጠናቀቁ 27 ሺህ 959 መዛግብት ቀርበው 27 ሺህ 684ቱ ውሳኔ ተሰጥቷቸዋል። 275 መዛግብት በሂደት ላይ ያሉ በመሆኑ የማጣራት ምጣኔ በአማካይ 99 በመቶ መድረሱን በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
19 ሺ 238 መዛግብት ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን 8 ሺ 446ቱ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች እንደተዘጉ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች አፈፃፀምን አስመልክቶ ባቀረቡት ሪፖርት በባለፈው ዓመት የተጀመሩና በበጀት ዓመቱም አዲስ የቀረቡ የከባድና የተደራጁ ወንጀሎች፣ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ከባድ የሙስና ወንጀል ጉዳዮችን ትኩረት በመስጠት የምርመራና ክስ አፈፃፀም ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመው፤ ቀደም ሲል የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰትን፣ የሙስና ወንጀልና በኢ ፍትሀዊነት የተነሳ የሚከሰቱ ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት የህግ ድንጋጌዎችን የማሻሻል፣ በልዩ ልዩ ወንጀሎች ተሳታፊ የሆኑ የመንግስት ሃላፊዎች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች ብጥብጥና ሁከትን በማስነሳት ጥቃት ያደረሱ፣ አስገድደው የደፈሩና በመንግስትና በህዝብ ሀብት ላይ ውድመትን ያካሄዱ ህገወጥ ድርጊት የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ የተደረገ ሲሆን፤ በምርመራና በክስ የሚፈለጉ ሶስት ሺ ሰዎች ሲሆኑ አንድ ሺ 404 (46ነጥብ 93) በመቶ በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
በሰኔ 15 ቱ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ በተፈፀመው የወንጀል ድርጊቱ ተካፋይ የሆኑ በባህር ዳር የወንጀል ምርመራ መዝገብ 55 ፣ በአዲስ አበባ የወንጀል ምርመራ ደግሞ 13 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ የተመሰረተ ሲሆን እስከ አሁን 62 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን 6 የሚሆኑት አሁንም እንዳልተያዙ ተገልጿል፡፡
በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በምርመራ ሂደት 357 የተለዩ ግለሰቦችና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በህግ ቁጥጥር ስር እንደዋሉ በሪፖርቱ የተገለፀ ሲሆን 171 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ 185 የሚሆኑት ክሳቸው የተመሰረተ ቢሆንም በቁጥጥር ስር እንዳልዋሉ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
ከምክር ቤቱ አባላት የህግ የበላይነትን ከማስከበርና በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች የሚከሰቱ ግጭቶች የሚመሩና ተሳታፊ የሆኑ አካላትን ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ ላይ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ምላሽ በሰጡት ምላሽ በተለይ ክልሎች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን አጣርቶ ወንጀለኞችን ለመያዝ የሚደረገው ጥረት ወንጀለኞቹ በብሄርና በሃይማኖት ውስጥ በመሸሸጋቸው አዳጋች እንደሆነባቸው ጠቁመው፤ የክልል አስተዳደሮችና ህብረተሰቡ አጋልጦ ለህግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 20/2012
ሐይማኖት ከበደ