አዲስ አበባ:- የጉምሩክ ኮሚሽን በስድስት ወራት ውስጥ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚገመቱ የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎችና ገንዘብ መያዙን አስታወቀ። 224 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያለው አደንዛዠ እፅ መያዙም ተጠቁሟል።
በጉምሩክ ኮሚሽን የጉምሩክ ህግ ተገዥነት ዘርፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሸናፊ ባሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ መሪ እቅድ አዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በህገወጥ መልኩ ከአገር በሚገቡና በሚወጡ እቃዎች ላይ ባደረገው ቁጥጥር፤ በስድስት ወራት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚገመቱ የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎችና ገንዘብ በቁጥጥር ስር አውሏል።
እንደ ጽህፈት ቤት ኃላፊው ማብራሪያ፤ ኮሚሽኑ በመንፈቅ ዓመቱ በህገወጥ መንገድ ወደ አገር የሚገቡ ኮንትሮባንድ እቃዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረጉ ከአንድ ቢሊዮን 39 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው አደንዛዥ እፆች፣ የጦር መሣሪያዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ ምግብ ነክ ሸቀጣ ሸቀጦች፣ ተሽርካሪዎች መያዙን ገልጸዋል።
በሌላ በኩልም በስድስት ወራቱ በህገወጥ መንገድ ከአገር ወደ ውጪ በሚወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች ላይ በተደረገ ቁጥጥር ወደ 161 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው እቃዎችን በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ የቁም እንስሳትና ገንዘብ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎችን ኮሚሽኑ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የተናገሩት አቶ አሸናፊ፤ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለውም ጠቁመዋል።
በአንጻሩ አምና በተመሳሳይ ወቅት በወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች 200 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ዕቃዎች የተያዙ ሲሆን፤ ዘንድሮ 161 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ዕቃዎች ከአገር ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ይህም የዘንድሮው የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች ዋጋ በ39 ሚሊዮን ብር እንደሚያንስ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ከተያዙት የገቢና የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል ከፍተኛው ገቢ ካስገኘው አደንዛዥ እጽ 224 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ተይዟል። ከገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ አደንዛዥ ዕጽ በመጀመሪያ ደረጃ የሚገኝ ሲሆን አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ ምግብና መጠጥ ነክ ነገሮች እንዲሁም ተሽከርካሪዎች በሁለተኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ በቅደም ተከተል ይዘዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 20/2012
ሶሎሞን በየነ