- አራት የተጠረጠሩ ሰዎች በለይቶ ማከሚያ ማእከል ክትትል እየተደረገላቸው ነው
አዲስ አበባ፡- የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የተጠናከረ ዝግጅት መደረጉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ከቻይና የመጡ ናቸው የተባሉና አራት የተጠረጠሩ ሰዎች በለይቶ ማከሚያ ማእከል ክትትል እየተደረገላቸው ነው።
ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን በጋራ በሰጡት መግለጫ እንደተገለጸው፤ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከቻይና እና አጎራባች አገሮች ለሚመጡ መንገደኞች የሙቀት ልየታ (thermal screening) እና ፎርም የማስሞላት ስራ ተጀምሯል። የልየታ ስራውን ለማጠናከር በቂ የሰው ኃይል ተመድቧል።
የከፋ ሁኔታ ላልታየባቸውና 30 ለሚሆኑ በበሽታው የሚጠረጠሩ ታካሚዎችን መያዝ የሚችል የለይቶ ማከሚያ የህክምና ማእከል በቦሌ ጨፋ ተዘጋጅቶ አስፈላጊው የህክምና እና ልዩ ልዩ ግብዓቶች እየተሟሉ ይገኛሉ። በዚህ ማእከል በሽታዉ የተረጋገጠባቸው፣ የተጠረጠሩ እና ተለይቶ ክትትል ለሚደረግላቸው ሰዎች ክፍሎች ተለይተው መዘጋጀቱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን ለኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቅድመ ዝግጅት የአደጋ ማስተባበሪያ ማእከል (Emergency Operation Center) ወደ ተግባር በማስገባት ጭምጭምታዎችን የማረጋገጥ እና ለተጠርጣሪዎችም ጥልቅ ምርመራ እየተከናወነ መሆኑም ነው የተገለጸው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከቻይና የመጡ ናቸው የተባሉና አራት የተጠረጠሩ ሰዎች በለይቶ ማከሚያ ማእከል ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ተገልጿል።
ከተለዩት ተጠርጣሪዎች ሁለቱ የሳል እና የሙቀት ምልክት ያሳዩ ቢሆኑም፤ በአሁኑ ወቅት ግን አልፎ አልፎ ሳል ከማሳየታቸው ውጭ ሌላ የበሽታ ምልክት የላቸውም። ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ምንም አይነት የህመም ምልክት ባያሳዩም ከቻይና ወረርሽኙ ካለበት ቦታ የመጡ መሆናቸው እና ምልክቱን ካሳየው ተጠርጣሪ ጋር ቅርብ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው ነው ተብሏል።
ከአራቱ ተጠርጣሪዎች የላብራቶሪ ናሙና ተወስዶ ለምርመራ በዛሬው ዕለት ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኳል። ከተወሰደው ናሙና በኢትዮጵያ በተደገላቸው ምርመራ ከ 5 አይነት ኮሮና ቫይረሶች ነጻ መሆናቸውን መረጋገጣቸው ተገልጿል።
ከቻይና ለመጡ 280 መንገደኞች በየዕለተቱ ባረፉበት ቦታ ክትትል እየተደረገላቸው ነው ያለው መግለጫው፤ ይሄ ክትትል ለ14 ቀናት የሚቆይ ይሆናል ተብሏል።
አዲስ ዘመን ጥር 20/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር