አዲስ አበባ፡- 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ የተደረገበት የጌዲዮ- ጉጂ የሰላም ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ፡፡
የጌዲዮ -ጉጂ የሰላም ግንባታ ፕሮጀክት ማኔጀር አቶ እዮብ ይስሀቅ ትናንት በሂልተን ሆቴል የፕሮጀክቱን እቅድ ሲያቀርቡ እንደገለፁት፤ ሁለቱ ህዝቦቹ የሚያስተሳስራቸው ብዙ ነገር ስላለ ሰላም የማስፈን ስራው ቀላል ነው፡፡
ዞኖቹ በአንድ አባገዳ ስር መተዳደራቸው፣ በአንድ ቋንቋ መገልገላቸው እንዲሁም አንድ ባህል መከተላቸው ለስራው ቀናነት እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡
የሰላም ግንባታ የአንድ ቀን ጉዳይ አይደለም ያሉት አቶ እዮብ፤ ለዚህም ግጭቶች ተመልሰው እንዳይመጡ የማድረግና ዘላቂ ሰላምን የማስፈን ስራ ላይ ትኩረት በማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ እዮብ ገለፃ ፤ሰላም ላይ ሁሉም ሰው ተባባሪ ሊሆን ይገባል፤ በመሆኑም ድርጅታቸው በሰላም እጦት ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶችን ተሳታፊ ለማድረግ እንዲሁም ስልጠና ለመስጠት አቅደዋል፡፡
ፕሮጀክቱ አልዘገየም ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ አልዘገየም ፤ የፕሮጀክቱ ዋነኛ ስራም የታረቁትን ደግሞ ማስታረቅ ሳይሆን ዘላቂ ሰላም ላይ ነው ሲሉ ገልጸዋል ፡፡
በወርልድ ቪዢን የፌት ኤንድ ዴቨሎፕመንት ማኔጀር ዶክተር ገለታ ሲሜሶ በበኩላቸው፤ የሰላም ግንባታ ረጅም ጊዜ የሚፈልግ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንደሌላው ፕሮጀክት ባንዴ ተጀምሮ የሚያልቅ ባለመሆኑ የረጅም ጊዜ ልማት የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር ገለታ በሰላም ጉዳይ ላይ ሁሉም ሰው ተባባሪ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ስራቸው እየረዳቸው መሆኑንና ሌሎች ተባባሪ አካላትም ትብብራቸው እንደማይለያቸው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ገለታ የጌዲዮ- ጉጂ የሰላም ግንባታ ፕሮጀክት እየተሰራ ያለው በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ መሪነት ቢሆንም ኬር ኢትዮጵያ እንዲሁም ካቶሊክ ሪሊፍ ሰርቪስ ተሳትፈዋል፤ፕሮጀክቱ ለቀጣይ 18 ወራት የሚቆይ ሲሆን ወጪው ሙሉ በሙሉ የሚሸፈነው በአውሮፓ ህብረት መሆኑንም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 20/2012
ዳግማዊት ግርማ