አዲስ አበባ፡- የግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት በተማሪዎች ላይ ያደርሳል በተባለው የተመሳሳይ ፆታ ወሲባዊ ትንኮሳና ቀለምን መሠረት ያደረገ የትውልድ አምካኝ ተግባር ላይ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ነሐሴ 1 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲሁም ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም በተከታታይ በተሠራው ዘገባ የተካተተው መምህር ኃይሉ ፍቃዱ ትምህርት ቤቱ ያሳረፈባቸው ቅጣት እንዲነሳላቸው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወሰነ።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሥራ ክርክር ችሎት በቀን 08/05/2012 ዓ.ም በቁጥር የይ/መ/ቁ. 191477 ወጪ ባደረገው መዝገብ ግልባጭ ላይ እንደገለፀው፤ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 43 ንዑስ ቁጥር አንድ እና አምስት መሠረት መምህሩ የአንድ ዓመት ያልተከፈለ ውዝፍ ደመወዛቸው እንዲሰጣቸውና ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ አዟል።
ጉዳዩ ለችሎቱ ሊቀርብ የቻለው የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ መሠረት የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተዘጋውን መዝገብ አንቀሳቅሶ በትምህርት ቤቱ በትክክል የዘር መድልዖ መኖሩንና አለመኖሩን በተገቢው መንገድ ተጣርቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት በማዘዙ ነው።
ፍርድ ቤቱም ትዕዛዙን ተቀብሎ አስፈላጊ ማስረጃዎችን ከመረመረ፣ ምስክሮችንና የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ የዘር መድልዖ መኖሩንና አለመኖሩን አጣርቶ ውሳኔ መስጠቱን መዝገብ ግልባጩ አስፍሯል። መምህሩ በገለጹት መልኩ በትምህርት ቤቱ ውስጥ በኢትዮጵያውያንና ከአገር ውጪ በመጡ ሠራኞች መካከል ልዩነት መፈጠሩን መልስ ሰጪ ሆኖ የቀረበው የትምህርት ቤቱ ምስክሮችም በማመላከታቸው የነበረው ልዩነት እንዳለ የሚያረጋግጥ መሆኑን አብራርቷል።
የተፈፀመውን ድርጊት መምህሩ መናገራቸውን ሥም ማጥፋት ሊሆን ስለማይችል የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 14 ንዑስ ቁጥር አንድ (ረ) የሚደነግገው ከአሠሪ ሕገወጥ ድርጊት ውስጥ በብሔረሰብ፣ በፆታ፣ በሐይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከትና በሌላም ሁኔታ በሠራተኞች መካከል ልዩነት ማድረግ ነው የሚል በመሆኑ መልስ ሰጪ ይግባኝ ባይ የሥም መጥፋት ድርጊት ፈጽሟል በማለት የፈፀመው የሥራ ውል መቋረጥ ሕገወጥ ስንብት መሆኑንም በመዝገብ ግልባጩ አስቀምጧል። በመሆኑም መምህር ኃይሉ ወደ ቀድሞ ሥራቸውና ያልተከፈላቸው ደመወዛቸው እንዲሰጣቸው ተወስኖላቸዋል።
ግሪክ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ‹‹ዜጎች በአገራቸው መማርም ሆነ መሥራት እንዳይችሉ በሚያደርግ ትምህርት አሰጣጥና በግብረሰዶም ተግባር ላይ ተሰማርቶ ትውልድ እያመከነ ነው›› በሚል ቅሬታ እንደቀረበበትና ነሐሴ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ‹‹ትምህርት ቤቱ ትውልድ ገንቢ ወይስ አምካኝ?›› በሚል ርዕስና ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር መፍትሔ እንደሚሰጥ የገባው ቃል ከምን ደረሰ? በሚል መስተናገዱ ይታወሳል። በወቅቱ የቀረበበትን ቅሬታና አራት የተለያዩ ማህተሞች የመጠቀሙን እንቆቅልሽ በተመለከተ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ያስተባበለ ሲሆን፤ ትምህርት ሚኒስቴር ግን በትምህርት ቤቱ ተገኝቶ እንዳረጋገጠና የቅሬታውን ተገቢነት አምኖ መፍትሄ እንደሚሰጥ ገልፆ ነበር።
አዲስ ዘመን ጥር 20/2012
ፍዮሪ ተወልደ