አዲስ አበባ፡- ከመደበኛዎቹ የትምህርት ዓይነቶች በተጨማሪ ግዕዝንና ግብረገብነትን ያካተተ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በደብረብርሃን ከተማ ሊከፈት እንደሆነ መሥራቾች አስታወቁ።
የትምህርት ቤቱ መሥራች ወይዘሮ አዳነች ኃይሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የዕውቀትን ገበታ ለመቋደስ ‹‹ሀ›› ብለው ወደ ቅድመ መደበኛ ትምህርት የሚላኩ ሕጻናት እየተኮተኮቱ ማደግ እንዳለባቸው ዕሙን ነው። በመሆኑም ፈለገ ብርሃን የተሰኘው አፀደ ሕፃናት በአገሪቱ በትውልድ ቀረጻ ላይ የሚስተዋለውን ከፍተኛ ክፍተት ለመሙላት ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፤ በሴቶች ብቻ የተቋቋመ ነው። በ2013 ዓ.ም ሥራውን ለመጀመር የሚያስችለው የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛል።
እንደ ወይዘሮ አዳነች ገለጻ፤ ከመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን በውል ባገኘው 11 ሺህ 400 ሜትር ካሬ ስፋት ቦታ የሚያርፈው ትምህርት ቤት የአጭር ጊዜ ዕቅዱ መሠረታዊ ለመማር ማስተማር የሚረዱ ግብዓቶች ማሟላት ሲሆን፤ ሀገራቸውን የሚወዱ፣ ሃይማኖታቸውን የሚያከብሩና ለሠው ልጆች ሁሉ ፍቅር ያላቸው ዜጎችን በሥነምግባር ማነጽ ዋነኛ ትኩረቱ ነው።
በዚህም ትውልድን በዕውቀት፣ በሥነምግባርና ብዙም ትኩረት ተሰጥቶት የማይታየውን የግዕዝ ቋንቋ በተለየ ሁኔታ ያስተምራል። ሥራውን ሲጀምርም በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን የነጻ የትምህርት ዕድል ለመስጠት አቅዷል።
በከተማው ልዩ ሥሙ ‘ስፖንጅ ሜዳ’ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚከፈተው ትምህርት ቤቱ ከመደበኛ መማር ማስተማር ተግባሩ ባሻገር በአገሪቱ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህል፣ ትውፊት፣ ሃይማኖት ብሎም አጠቃላይ አኗኗር ሊያሳዩ የሚችሉ ቁሶች ማዕከል ይኖረዋል።
ይህም ሕፃናቱ ‹‹በአገሪቱ የሚገኙ ሕዝቦች ታሪክ የእኔ ታሪክ ነው፣ እኔ ሌሎችን ሳከብር በምላሹ እከበራለሁ›› ብለው እንዲቀበሉ በማድረግ በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለውን የአክራሪ ብሔርተኝነት እንዲሁም ይህንን ተከትሎ የሚከሰቱ የአገር አለመረጋጋት ችግሮችን ለማቃለል አሻራ ያሳርፋል ተብሎ ይጠበቃል።
በተያያዘ የአገሪቱ የኋላ ታሪክ ምን እንደነበር አውቀው ወደፊትስ ምን ይሆናል? የሚለውን ማለም የሚችሉ ዜጎችን በመፍጠር ለሠላምና ለዕድገት የሚኖረው ድርሻ የላቀ እንደሚሆን ወይዘሮ አዳነች ጠቁመዋል።
አዲስቨ ዘመን ጥር 20/2012
ፍዮሪ ተወልደ