ህብረተሰቡ በአዝማሪ ሙዚቃ ሰርጉን አድምቆበታል፤ መንፈሱን አድሶበታል፤ ማህበራዊ ሥርዓቱን ጭምር አርቆበታል።በተለይ አዝማሪነት በትምህርት የተደገፈ ሲሆን ምን ያህል ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው።ያልተዘመረለት አዝማሪው በሙያ ሁለተኛ ዲግሪውን ያገኘ ነው።ቆንጆ ክራር ደርዳሪም ነው፤ የዜማና ግጥም እንዲሁም ተውኔት ደራሲም ነው።
ብዙ ጊዜ አዝማሪ ሆኖ ሁለተኛ ዲግሪ ያለው አይተን የማናውቀውን የሰበረ፤ ከስድስት በላይ አልበሞች የሰራ፤ ከሌሎች ድምጻውያን ጋርም እንዲሁ ከስድስት በላይ አልበሞችን ሰርቶ ለባህል ወዳዱ ህዝብ ያደረሰ ነው።የባህል አንባሳደሩ አርቲስት አበባው አስራት።እኛም ይህ እንቁ እና ብዙ የህይወት ተሞክሮ ባለቤት ልምዱን ያወጋን ዘንድ የዛሬው የህይወት እንዲህ ናት እንግዳችን አደረግነው።
አበባው
ወርሃ መስከረም አንድ ሲባልና አደይ አበባ ሲፈነዳ ነው የተወለደው።ውልደቱን ከወሩ ጋር በማስተሳሰር ታላቅ እህቱ አበባው ስትል አወጣችለት።ያው በመስከረም ወር አበቦች ከያሉበት ብቅ የሚሉበት አይደል።ልምላሜ በምድሪቱ ላይ በመታየቱ አፈራ፣ ለመለመ ለማለት ያወጣችውን ስምም በመሆኑ ቤተሰቡ ተቀበለው።ከዚያም አልፎ የአካባቢው ሰው ይጠራበት ጀመር።እናም አበባው አስራት መባሉ ቀጠለ።
አበባው ትውልዱ ጎጃም ውስጥ ደምበጫ ሸለል ገብረኤል ነው።የመጨረሻ ልጅ ስለሆነ የሁሉንም ቤተሰብ እንክብካቤ እያገኘ ነው ያደገው።በተለይ እናትና ታላቅ ወንድሙ መቼም ቢሆን ከአዕምሮው አይጠፉም።ያደረጉለት ነገር ዘወትር የማይረሳውም ነው።አበባው በልጅነቱ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መካከል ጅምናስቲክ መስራት ይወዳል፤ ስፖርቱም በአጎናጸፈው ክህሎትም ለማንኛውም ነገር ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ልጅ አድርጎታል።
በትምህርት ቤት ውስጥ ቲያትር በመስራት የሚታወቀው እንግዳችን፤ በደርግ ጊዜ ኪነት ቡድን ውስጥ ይሳተፍ ነበር።አበባው ድምጻዊ መሆኑን የተረዳው በአደባባይ በሚያቀርቧቸው የተለያዩ ሥራዎች መሆኑን ይናገራል።በተለይ በትምህርት ቤት የወላጆች ቀን ሲያከብሩ የሚሰራቸው ሥራዎች መቼውንም የማይረሳቸው እንደነበሩ ይናገራል።
በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታዘዝ ልጅ አለመሆን ራስን ብቻ ሳይሆን ቤተሰብንም ያሰድባል።በዚህም ከጎረቤት ትዕዛዝ ሥር ወጥተው እንደማያውቁ የሚናገረው ባለታሪኩ፤ ጎረቤት ቆንጥጦ ያሳደገን በመሆናችንና መታዘዝ ግዴታችን እንደሆነ በማሰባችን ዛሬ ላይ ስነምግባር ያለው ልጅ ሆነናል።መመረቅን ያህል ሀብት የለም ብለን ማመናችንም ለታላቅ ክብር አብቅቶናል ይላል።
በገጠር አካባቢ በማደጉ ብዙ ጊዜ እንጨት እየለቀመ ቤተሰቡን ሲያገለግል የቆየው የትናንቱ ልጅ የዛሬው ጎልማሳ አርቲስት አበባው፤ እስክሪብቶና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስ ግዙልኝ ላለማለትም ያልሞከረው የንግድ አይነት እንዳልነበረ ያነሳል።ለአብነትም ጋዝ፣ እንቁላል፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ሎተሪ በማዞርና መሰል ነገሮችን በመሸጥ ከራሱ አልፎ ቤተሰቡን ያግዝ እንደነበር አጫውቶናል።በተለይ ነግዶ ከሚያገኘው ገንዘብ ለእናቱ ዘይትና ሌሎች ለምግብ የሚውሉ ነገሮች ሲገዛ ደስታው እጥፍ እንደነበር ያስታውሳል።
ቤት ውስጥ እርሱ ካለው ውጪ አንዳች ነገር እንደማይደረግ፤ ለምርጫና ሀሳብ ለመስጠትም ብዙ ጊዜ እንዲናገርና እንዲመርጥ ቅድሚያ የሚሰጠው እርሱ ብቻ እንደነበር ያጫወተን አበባው፤ በልጅነቱ መሆን የሚፈልገው ነገር የወሰነውም ራሱ ነው።እናም የመጀመሪያ ምኞቱ በቅርብ የሚያያቸውንና የሚወዳቸውን መምህራንን መሆን ነበር።ካደገ በኋላ ደግሞ ሙዚቃው ማረከውና ፍላጎቱን ቀየረ።አዝማሪ ወይም ሙዚቀኛ መሆንንም ተመኘ።
አበባው በደርግ ጊዜ በህብረት ሥራ ዘመቻ ወቅት ገና ልጅ እያለ አዛውንቱን በአጨዳ፣ በአረም ነቀላና መሰል ነገሮች ይደግፍ እንደነበርም አይረሳውም።ከትምህርት ቤት ሲመለስ ደግሞ ተማሪዎች ይህንን በጎ ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ በትዕይንት መልክ በግጥም በሰልፍ ላይ ያቀርብላቸዋል።
በተምጫ ወንዝ ላይ ሲዋኝ ያደገው እንግዳችን፤ እግር ኳስ በጣሙን ይወዳል።እንደውም ሱሰኛ ነኝም ይላል።ከዚያ ባሻገር ከሁሉም ሰው ጋር ጊዜውን በጨዋታ ቢያሳልፍ ያስደስተዋል።
ትምህርት
ፊደል መቁጠርን የጀመረው በታላቅ ወንድሙ አማካኝነት በቤት ውስጥ ነው።ከዚያ በቀጥታ ዘመናዊ ትምህርትን ለመቅሰም በአቅራቢያው ወደሚገኘው ‹‹ሸለል ገብረኤል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት›› ሄደ።እስከ ስድስተኛ ክፍልም በትምህርት ቤቱ ተማረ።ቀጣዩን ትምህርት ለመከታተል ደግሞ ማቻከል ተብሎ ወደሚጠራው ወረዳ አማኑኤል ከተማ ነበር የተጓዘው።በዚያም አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባ።
ይህ ትምህርት ቤት ከቤተሰቦቹ ራቅ ያለ በመሆኑ ገንዘብ እየተከፈለለት ቀላቢ ቤት ገብቶ ነው የተማረው።ስለዚህም ጥንቁቅ ተማሪ በመሆን ሰባትና ስምንተኛ ክፍልን አጠናቀቀ።ብዙ ጊዜውን ለንባብ ስለሚያውለው ደግሞ በወቅቱ ከማቻከል ወረዳ ከፍተኛ ውጤት ከአመጡ ተማሪዎች መካከል አንዱ ሆኖ እንዲያልፍ አድርጎታል።ዘጠነኛ ክፍልን ደግሞ የተማረው ደምበጫ በመሄድ ነው።አሁንም በአቅራቢያው ትምህርት ቤት ስላልነበር የተወሰነ ጊዜ ሆቴል ላይ ወንድሙ ተከራይቶለት ተማረ።ሆኖም የማይገባ ጥፋት በመስራቱ በእግሩ እየተመላለሰ እንዲማር ተፈረደበት።
ድሎት የበዛበት የያኔው ጊዜው ወጣት አበባው፤ ለትምህርቱ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ምሽት ቤቶች ላይ መቆየቱን ተያያዘው።ዳንስና ጭፈራ እንዲሁም ሙዚቃው ውስጡን ነሽጦት ኖሮ በዚያው አስቀረው።በዚህም የዘጠነኛ ክፍል ውጤቱ ያልተጠበቀ ሆነ።ዝቅተኛ የሚባል ውጤት አመጣ።ይህ ያበሳጨው ወንድሙም ክፍያውን አቆመና ተመላልሶ እንዲማር አደረገው።በዚህ ደግሞ ዛሬ ድረስ የሚያመሰግነውን ለውጥ እንዲያሳይ አድርጎታል።
‹‹መንደላቀቅ ብዙ ነገርን ይቀማል።በእግር ተመላልሶ መማር ግን ጊዜን ከመቆጠቡ ባለፈ ችግርን እያዩ የወደፊት አቅጣጫን ለማስተካከል መድሃኒት ይሆናል።ምክንያቱም ራሴን አይቼ እንድመለስና ትክክለኛ መስመር ላይ እንድቆም ያደረገኝ በእግሬ ተመላልሼ መማሬ ነው።ስሄድ ብቻ ከስምንት በላይ ኪሎ ሜትር መጓዜ ብዙ ነገር አስጨብጦኛል›› ይላል።በደምበጫ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 12ኛ ክፍልን በጥሩ ውጤት ያጠናቀቀው አበባው፤ ወቅቱ ፈታኝና ከፍተኛ ውጤት ማምጣትን የሚጠይቅ በመሆኑ ጊዜው የሚፈልገውን የመግቢያ ውጤት አላገኘም ነበር።ይሁንና ‹‹ሳይደግስ አይጣላም›› እንዲሉ ሆነና ነገሩ በኮታ ዩኒቨርሲቲ የሚገባበት አማራጭ ተስተካከለለት።
በእነርሱ ጊዜ ዲግሪ ለመግባት 3ነጥብ 2 ይጠይቃል።እርሱ ደግሞ ያመጣው 3 ነጥብ ብቻ ነው።በዚህም ቀደም ሲል በነበረው ጉብዝናና በባህሪ እንዲሁም ሌሎች መስፈርቶች ተካተውበት ነበር በኮታ የሚወሰድበት ፈተና ላይ እንዲሳተፍ የሆነው።ከዚያም ፈተናውን በጥሩ ውጤት አለፈና ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አደረገ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ገብቶ ቢሆን ሌላ ፈተና እንደነበረበት ያጫወተን ባለታሪኩ፤ የፈለጉትን የትምህርት መስክ ለማግኘት የመጀመሪያ ዓመት ትምህርቱ ላይ ከ2 ነጥብ 7 ባሌ ውጤት ማምጣት ያስፈልጋል።ይሁንና እርሱ ግን ይህንን ውጤት ማምጣት አልቻለም ነበር።በዚህም አማርኛ ትምህርት ክፍል ውስጥ ተመደበ።እርሱ መማር የሚፈልገው ቴአትሪካል አርት እንጂ አማርኛ ባለመሆኑም ትምህርቱን አቋረጠ።
የሚፈልገውን ሙያ ለማጥናት ሲል ከ14 ዓመት በላይ በዚያው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል ውስጥ ነጻ አገልግሎት እየሰጠ የቆየው እንግዳችን፤ የማታ ትምህርት እስኪጀመር ድረስ ትምህርቱን ለመጀመር አልቻለም ነበር።ስለዚህም ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2 ሺህ ድረስ ከትምህርት ገበታው ርቆ ቆይቷል።ሆኖም የትምህርት ፍቅሩ አልጠፋምና 2001 ላይ የቴአትር ትምህርቱ በማታ ተጀመረ።ደስታው እጥፍ ድርብ ሆነና የመጀመሪያው ተመዝጋቢ ሆኖ ትምህርቱን እንዲከታተል ሆነ።
‹‹ረጅም ዓመታትን ከትምህርት ብርቅም ፍቅሩ ነበረኝና የተሻልኩ ተማሪ ከመሆን አላገደኝም›› የሚለው ባለታሪኩ፤ ፈልጎና ናፍቆ የሚደረግ ነገር ይጣፍጣል።በዚህም ድግሪዬን በ2001 ጀምሬ በ2004 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ችያለሁ።እንደውም የማዕረግ ተመራቂም ነበርኩም ብሎናል።ይህ ሳይበቃው ደግሞ በመካከሉ በአዝማሪነትና በማዕከሉ ውስጥ በባለሙያነት እየሰራ የመማር ፍቅሩ ከውስጡ ሳይጠፋ ዓመት ቆይቶ ማስተሩን ያዘ።እናም ብቸኛው አዝማሪ ሁለተኛ ዲግሪ ያለው ሆነ።በዚህም ጊዜ ቢሆን የማዕረግ ተመራቂ እንደነበር ይናገራል።
‹‹ማስተርስ ያለው የባህል ዘፋኝ በአገር ደረጃ አላውቅም።በዚህም ብቸኛ ነኝ ብዬ አስባለሁ።ስለዚህም አዝማሪው ባለ “ማስተር” ስባል ያስደስተኛል›› የሚለው አበባው፤ ‹‹የባህል ድምጻዊ ሁሉ ሰነፍ አይደለም።ዲግሪም ሆነ ማስተር ማግኘት የማይችልም አይደለም።እድሉን ካገኘ ማንም ሰው ዲግሪ እና ከዚያ በላይ ሊይዝ ይችላል።ስለዚህም በባህል ዘፋኝነት ማስተር የያዘ ብቸኛ የሆንኩበት ምክንያት እድል ስለተሰጠኝ ነው።›› ይላል።
ሁለተኛ ዲግሪ ለመያዝ ብዙ ፈተናዎችን ያለፈው እንግዳችን፤ ማንኛውንም የተሻለ ነገር ለማግኘት ጥረት ወሳኝ ነገር ነው።ምክንያቱም እኔ ሁለተኛ ዲግሪዬን ስማር እስኪነጋ ድረስ እየሰራሁና ቀን እንቅልፍ እያዳፋኝ ጭምር እየተማርኩ ነው።በመሆኑም ትክክለኛ የሙያ ባለቤት ለመሆን የሚጠይቀውን መስዋዕትነት መክፈል ያስፈልጋል ይላል።አበባው ሁሌም መማርን ገንዘብ አድርጎ የሚወስድ በመሆኑ አሁንም ትምህርቱን መቀጠል እንደሚፈልግ አጫውቶናል።ትምህርት ማቆሚያ ሊኖረው አይገባምም ባይ ነው።
የሙዚቃ ህይወት
‹‹ሬዲዮና ቴሌቪዥን በሌለበት አካባቢ ተወልዶ ድምጻዊ መሆን የማይታሰብ ነገር ነው።ተሰጥኦ ካለ ግን በተገኘ አጋጣሚ ማዳበር ይቻላልና ጸጋን ለይቶ መትጋት ያስፈልጋል።ምክንያቱም ለማስመሰል እንኳን እድል የሌለበት፣ በስም ጠርቶ የእገሌ ዘፈን ይመስጠኛል ብሎ መለማመድ በማይቻልበት ውስጥ ልዩ ጸጋ ከሌለ አንድ እርምጃ መራመድ አዳጋች ነው።እናም የዛሬ ሙያዬ የተፈጥሮ ስጦታን ይዞ ብዙ በመልፋት የተገኘ ነው ›› ሲል የድምጻዊነት ጅማሮውን ያስታውሳል።
ሌላው የአዝማሪነት ወይም የድምጻዊነት ጅማሮው የክራሩ መምጣትና ክራር መጫወት የመቻሉ ምስጢር ነው።የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተሩ ደግሞ የክራር ጨዋታን ያስተማረው ነው።ዘወትር ከጓደኛው ጋር ወደቤታቸው ሲሄዱ ጓደኛው ክራር ይጫወታል።እናም አበባውም እንዲሞክር ይጠይቀውና ያለማምደዋል።አልፎ አልፎ ጓደኛው ለሻይ ቡና ሲወጣ አንስቶ በቻለው መጠን ይጫወታል።ይህ ደግሞ ክራር ወዳድነቱን ከእለት እለት ጨመረለት።በዚህም ዘፋኝ፣ ክራር ደርዳሪ ለመሆን ቻለ።ይሁንና በደንብ እንደቻለ የተረዳው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት በገባበት ወቅት ነው።ምክንያቱም የቴአትር ተማሪዎችን በተለያየ ቅኝት የማጀብ ሥራ ሲሰሩ ይመለከታል።እንዲያሳዩትም ይጠይቃል።ከዚያ ጥሩ ክራር ተጫዋች ለመሆን በቅቷል።
‹‹ሙዚቃን ተለክፌበታለሁ፤ አዝማሪነት አልኖረውም ብል እንኳ በቀላሉ የምወጣበት አይደለም፤ ካለሙዚቃ መኖር ይሳነኛል።ምክንያቱም ከማንጎራጎሩ ባሻገር ብዙ የሚናፈቁ ነገሮችን በውስጡ ስለያዘ ይስበኛል።›› የሚለው እንግዳችን፤ ለእኔ ደስታም ሆነ ሀዘን መግለጫዬ ግጥሜና ዜማዬ ናቸው።ክራሬ ደግሞ ሰላሜን ትሰጠኛለች።ብዙ ጊዜ አጠር ያለ ስንኝ መጻፍ ይመቸኛል፤ ጠንካራ ብሶቴን በጠንካራ ስንኞቼ ውስጥ በመሸጎጥ ሰፊ የሆነውን ሀሳቤን በአጭሩ አስተላልፍበታለው።
‹‹አዝማሪነት የእውቀት ጥግ ያለበት፣ የጉልበትና መሰል ነገሮች ብዝበዛ የሚደረግበት ግን ፍቅር የሞላበት ነው።በዚህም አብዝቼ እወደዋለሁ።እንደውም አቅሜን መለኪያና አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶቼን የማይበት መድረክ አድርጌም ነው የምወስደው። ዛሬ ሙዚቀኛ ነኝ ብዬ አፌን ሞልቼ መናገር የቻልኩትም በእርሱ በሰጠኝ የእውቀት ልኬት ነው።እናም ሁሌም አዝማሪነቴን ወይም ድምጻዊነቴን እወደዋለሁ›› ይህ የአበባው የዘወትር ንግግሩ ነው።
ቆይታ በባህል ማዕከል
ለአራት ዓመት ያህል ያለክፍያ ከሰራ በኋላ የባህል ክፍሉ አሰልጣኝ ሆኖ በቋሚነት ተቀጠረ።በዚህም ዜማና ግጥም ከመድረስ ባሻገር ክራር እየተጫወቱ ባህል ክፍሉን ማጀብ ሥራው ሆነ። የባህል ድምጻዊዎች እድሉን ባለማግኘት በትምህርታቸው ብዙም የገፉ አይደሉም።በዚህም ቀደምት አዝማሪዎች ማንበብ ባለመቻላቸው ግጥም የሚነገራቸው በጆሯቸው ነበር።አበባው ግን ይህንን ሁሉ ሰብሮ ያለፈና በትምህርቱ የገፋ በመሆኑ በዚህ ማዕከል የተሻሉ የሥራ ደረጃዎችን በመያዝ መስራቱን ቀጥሏል።
ክራር እየደረደረ ሰውን በመረዋ ድምጹ ለአመታት በየውስኪ ቤቱ እየተዘዋወረ ህብረተሰቡን አዝናንቷል።ከዘጠኝ ሰዓት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስም ከትምህርት ጎን ለጎን በመስራት የሥራ ጥንካሬውን ያሳየ ነው።አበባው ለሰርግ፣ ለልደት፣ ለክርስትና እና የተለያዩ ግብዢያዎችም በክራሩ እያጀበና በመረዋ ድምጹ እያንጎራጎረ ሥራዎችን ከመስራት ያልቦዘነ ነው።ይሁንና ማንኛውንም ዘፈን ያለ ስሜቱ አይጫወትም።ሰዎችን የሚያጋጭ፣ ወገንተኛ ሁንልን የሚል ነገር አይሰማም።መቃወም ያለበትን በመቃወም፤ ማመስገን ያለበትን ምስጋና በመቸር ነው ትክክለኛውን የአዝማሪነት ሙያ የሚተገብረው።
‹‹ከጥበብ ጋር የተጋባ መቼም ቢሆን ከዚያ ሊርቅ አይችልም።ለዚህም ማሳያው እየተገፋሁ እንኳን ሙያውን መልቀቅና የተሻለ የሚባለው ሥራ ላይ ልገባ አልቻልኩም›› የሚለው ባለታሪኩ፤ ዲግሪውንም ሆነ ማስተሩን ይዞ ሌላ ሙያ ውስጥ ቢገባ የተሻለ ተከፋይና የተሻለ ኑሮ የሚኖር ይሆን ነበር።ነገር ግን እርሱ ይህንን አልመረጠም።ይልቁንም ሙያተኛ ነኝ ለማለት መከፈል ያለበት መስዋዕትነት መከፈል አለበት ብሎ የሚያምን ነው።እናም ሙያውን ትቶ መሄድ አይፈልግምና ቢገፋም እንኳን ከዚያ መውጣት እንዳልወደደ ያስረዳል።እንደውም ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ጊዜ ምርር ሲለው የጻፈውን ግጥም እንዲህ ሲል አንብቦልናል።
የጥበብን ልክፍት ምን አደርገዋለሁ
እየው አሁን እንኳን ቆብ ጭኜ እዘፍናለሁ።ስለዚህ ሙያው ማርኮ ከቤቱ ያስቀራልና ለሙያችሁ ተሟገቱ ይላልም።
የአዝማሪነት ሙያ የተጣላን ማስታረቂያ ነው።አንድ ጊዜ በቡድን ሆነው የሚጠጡ የጎጃምና የጎንደር ልጆች ገጠሙኝ።ብዙ ግጥም የሚሰጠው የጎጃም ቡድኑ ሆነ የጎንደር ቡድኑ ቅሬታ አነሳብኝ።ጎንደርኛ ለምን አትዘፍንም ብሎም በቁጣ ተነሳ።ከዚያኛው ወገን ደግሞ ምናገባህ የሚል ውዝግብ ድንገት አስተጋባ።በዚህ መካከል ገንዘብ ፈላጊው ድሃ ሊደበደብ ሆነ።እናም ወዲያው መልስ ከመስጠት ተቆጠብኩና ዝም የሚያሰኛቸውን ግጥም በክራሬ መደርደር ጀመርኩ።ግጥሙም እንዲህ የሚል ነበር።
አሁን አይበል እንጂ
አያድርገው እንጂ፤
አምላክ በጥበቡ ጣናን ባይሰራው
ጎንደርና ጎጃም ምን መለያ አለው።ወዲያውም እርቀሰላም ወረደና ውስኪ ለጠጪው ሁሉ ታዘዘ።ስለዚህም እንደሙዚቃ አስታራቂ ነገር የለምና በሥራ ፈጣሪና አስታራቂ ሆኜ እንድቀጥል አድርጎኛል ይላል።
አበባው አብዛኛው ዘፈኖቹ ባህላዊ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ፤ የመጀመሪያ ሥራው ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ በ1989 ዓ.ም ያወጣው ነው።ይህም ‹‹ አበባው ደጎል አበባው›› ይባላል።በመቀጠል ብቻውን ሙሉ አልበም የሰራ ሲሆን፤ በ1992 ዓ.ም የሰራው ‹‹ድምድም›› ፣በ1997 ዓ.ም ደግሞ ‹‹የጎጃም ወለላና ሀዬ በል››፣ 1999 ዓ.ም ደግሞ ‹‹ፈገግታ›› የሚልና በመጨረሻ ደግሞ በ2000 ዓ.ም ‹‹ አካልቤ›› በሚል አልበሙን ሰርቷል።
የኮሌክሽን ሥራውን በ1994 ዓ.ም ከሥራ አጋሮቹ ጋር በመሆን የለቀቀው አበባው፤ እነዚህን አልበሞች ከሰራ በኋላ ወደ ክሊፕ ሥራ እንደገባ ይናገራል።ቀደምት ሥራዎቹ ላይ የነበሩትን ዘፈኖች በመምረጥም 2002 ዓ.ም ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆን አድርጓል።ከዚያ ባሻገር ደግሞ እንግዳችን በተለያየ ጊዜ ለተለያዩ ሙዚቀኞች የዘፈን ግጥምና ዜማ የሰጠ ነው።ለአብነት የአቢ ላቀውን የመጀመሪያ አልበሟ ስድስተኛው ትራክ ያለውን ‹‹ሄሎ ኢትዮጵያ›› ማንሳት እንችላለን።ስለዚህም በአጠቃላይ በዜማ ከ60 በላይና በግጥም ከ60 በላይ ዘፈኖችን ለመድረክ እንዲያበቁ ያደረገ ነው።ከዚያ አለፍ ሲባል ደግሞ ግጥም ጽፎ ማህበረሰቡ መንፈሱን እንዲያድስበት በመድብል መልክ የደረሰም ነው።
አዝማሪነትን ጎጃም በረንዳ ውስኪ ቤት እንደጀመረ የሚናገረው ባለታሪኩ፤ ለአዝማሪነት ማህበረሰቡ የወረደ ምልከታ ስላለው እየፈራ እየተባ እንደጀመረው ያስታውሳል።የክራር ፍቅሩን እንደውም አዝማሪው ለሽንት ሲወጣ እያነሳ እንዳሟሟቀው አይረሳውም።ብዙ ልምድ ያካበተና ብዙ ሰውም የሚወደው በመሆኑ ክራር አጨዋወቱንም ያደንቅለት ነበር።እናም አንዳንድ ጊዜ ወጣ ሲል እንዲጫወትበት ይፈቅድለታል።
‹‹ከቀናት በኋላ ልክ እንደእርሱ እኔን ፈልጎ የሚመጣም በረከተ።እንድዘፍንም የሚጋብዘኝ ብዙ ሆነ›› የሚለው ባለታሪኩ፤ ይህ በመሆኑ አንድ የዘወትር አድማጩ በወቅቱ 40 ብር ውድ ቢሆንም የእርሱን ድምጽ በነጻነት ማድመጥ ይፈልጋልና ክራር ገዛለት።ከዚያማ ማንንም ሳይለምን በፈለገው ቦታ እየሄደ መጫወትና ገንዘብ ማግኘቱን ተያያዘው።ክራሩን ይዞም ዳትሰን ሰፈር፣ ገዳም ሰፈር፣ ራስ ደስታ፣ ካሳንችስ እያለ የአዝማሪነት ስራውን አጧጧፈው።
አበባው በባህሪው ያለውን መጋራት የሚወድ ነው።በዚህም ገንዘብ አይበረክትለትም ነበር።ምክንያቱም ካሳንቺስ ያገኘውን ገዳም ሰፈር ግጥምና ዜማቸውን ለሚደረድሩ አዝማሪ ጓደኞቹ ይሸልመዋል።እናም እንዲህ እንዲህ እያለ ነው ለአመታት የአዝማሪነት ህይወትን ያሳለፈው።
ከእነ አልማዝ እንዳለ እና አስቴር እንዳለ እዲሁም ማርሸት ጋር በእጅጉ የሚጫወተው አበባው፤ ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል ውስጥ በነጻ አገልግሎት እየሰጠ ነበር ይህንን ሥራ ሲሰራ የቆየው።ከዚያ እስከ ዳይሬክተርነት የሰራው እንግዳችን፤ በባህል ማዕከሉ የባህል ክፍሉ አሰልጣኝ ነበረ።ከዚያ ወደ የቴአትርና የሙዚቃ ባለሙያነት በደሞዝ ከፍ ብሎ መስራቱን ሲጀምር በትንሹም ቢሆን ሰዓቱን ቀንሶ ይሰራ ነበር።
ዛሬ ላይ እየሰራ ያለበትን ቦታ ሲያገኝ ማለትም አርቲስቲክ ዳይሬክተር ሲሆን ግን የትምህርቱ ጫናም ነበረበትና አቆመው።በባህል ማዕከሉም ቀጥ ብሎ መስራቱን ጀመረ።በዚህ ቤት ከዩኒቨርሲቲው ሳይወጣ ለ30 ዓመት ያህል ከሚወደው ሙያ ጋር እንዲኖር ሆኗል።ከዚያ በተጨማሪ አገራዊ የሆኑ በዓላት ላይም ባለው እውቀት ሁሉ ይሳተፋል።
ፈተና
‹‹የእኔ ፈተና ብዙ ነው።በአንደኝነት የሚጠቀሰው ግን የእድል አለመኖሬ ነው። ምክንያቱም የግጥም፣ የዜማ ደራሲ ነኝ።የሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋችና አቀናባሪም ነኝ። በዚያ ላይ ተውኔቶችን ከመጻፍ አልፌ እተውናለሁ። ይሁንና አንዳች ታዋቂነት የለኝም።በዚህም ባለኝ እውቀት ልክ ተጠቃሚ እየሆንኩ አይደለም›› የሚለው አበባው፤ ለአብነት ‹‹ የባላገር ፍቅር›› የተሰኘ በኢትዮጵያ አንቱታን ያተረፈ ቴአትር ጽፌ በብሔራዊ ቴአትር ቀርቦ ብዙዎች እንዲማሩበት ቢሆንም የአቅም ችግር ሳይኖር የፈላጊ ችግር ግን ገጥሞኛል።ሁሉ ነገር በእድል ምክንያት ተዘጋ።ስለሆነም የእኔ ፈተና በእድሌ ምክንያት አለመታወቄ ነው ብሎናል።
ገጠመኝ
በአዝማሪነት ካሳንቺስ እየሰራ ሳለ ነበር ይህ የሆነው።ሁልጊዜ ሸላሚዎቹ ሀበሾች ብቻ ናቸው።ግን ነጮችም ለመዝናናት ገብተው ይታያሉ።እናም ለምን ለእነሱስ አይዘፈንላቸውም በማለት በእንግሊዚኛ እንዲህ ሲል አሞገሰ።ስሙ ኒኮላስ ይባላል።እናም ሌት ቱጌዘር ፕሌይ ሌት ቱጌዘር ዳንስ
ሚስተር ኒኮላሴ ውልካም ቱ ዚስ ሀውስ።አለለት።እርሱም በሚያምር ፈገግታው ፈገግ ብሎ እነርሱ የሸለሙትን እጥፍ አድርጎ ሸለመው።በዚህም መቼም የማነሳው ገጠመኝ ሆነብኝ ይላል።ቀጥሎም አልችልም የሚባል ነገር ሳይኖር ወደ ተግባር ከተገባ ሁሉንም የማስደሰት ሥራ መስራት ይቻላል።በመሆኑም ሰዎች ቢጠቀሙበት የምለው ልዩ ተሰጥኦዋቸውን በልዩ ፈጠራ አጅበው አዲስ ሆነው መታየትን ነው ይላል።
ቤተሰብ
አበባው ባለቤቱን እመቤትን ያገኛት ዩኒቨርሲቲ እየሰራ ባለበት ጊዜ ሲሆን፤ እዚያው ዩኒቨርሲቲው ውስጥ በጸሐፊነት በምትሰራ ጊዜ ነው።በዚህም ለመተዋወቅም ሆነ ትዳር ለመመስረት ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም።አሁን የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነው።ልጁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሲሆን፤ ኢንጂነሪንግ ያጠናል።የአባቱን ሙያም በጣም ይወዳል።ሆኖም የዘመኑ ልጅ በመሆኑ ራፕ ነገር እንጂ ባህላዊ ዘፈን አይመቸውም።የተለያዩ ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችንም ይጫወታል።ግን አበባው ልጁ ዘፋኝ እንዲሆን አይፈልግም።ምክንያቱም የእርሱን ህይወት እንዲደግመው አይፈልግም።
‹‹ባለቤቴ ባትኖር አይደለም በሙያው ውስጥ መቆየት በህይወት የመኖር እድልም አይኖረኝም ነበር›› የሚለው ባለታሪኩ፤ በሙያው ከማበረታታት አልፋ ምሽት ላይ እስኪገባ ድረስ ትጠብቀው እንደነበር ይናገራል።ቶሎ ካልገባም ጭለማን ተጋፍጣ ለህይወቷ ሳትፈራ በር ላይ ቆማ ታመሻለች።በዚህም እርሷ የህይወቴ ቤዛ ሆናኛለችም ሲል ስለእርሷ ክብር ይመሰክራል።
መልዕክት
‹‹ተስፋ አለመቁረጥን፣ ትዕግስትንና ተስፋ ማድረግን ከእኔ ቢወስዱ ደስ ይለኛል›› የሚለው እንግዳችን፤ የፈለገውን ነገር በግጥምና በዜማ መተንፈስ እንደሚችል ይናገራል።የጎደለው ቁሳዊው ነገር ሲሆን፤ ቀደም ሲል ስለሌለኝም አልጓጓለትም ይላል።ግን ተስፋ እንዳለውም ይገልጻል።ምክንያቱም አምላክ ከፈቀደ በአንድ ቀን ጀንበር ሊሰጠኝ ይችላል ብሎ ስለሚያምን ነው።እናም ሰዎችም ማድረግ ያለባቸው የተሰጣቸውን በማመስገን መጠቀም ነው።
‹‹ላለው ይጨመርለታል›› የሚባለውም ያለውን ያከበረ እንደሆነ የሚናገረው አበባው፤ ለሚቀጥለውም እግዚያአብሔር የፈቀደውን ያደርጋል ብሎ መስራት እንደሚያስፈልግ ይመክራል። ስላልተደረገልን በማማ ረር የምናመጣው አንዳች ነገር የለም።በወቅቱ የተሰጠንና የተገኘን ነገር በአግባቡ መጠቀም ብቻ ነው መፍትሄውም ይላል።ብዙ አስተማሪ መልዕክቶች ቢኖሩትም አምድ ገደበንና ሀሳባችንን በዚህ ቋጨን።ሰላም !
አዲስ ዘመን ጥር 17 ቀን 2012 ዓ.ም
ጽጌረዳ ጫንያለው