አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች 101 ሺ 841 ተመዛኞች መመዘናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ፣ የሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን አስታወቀ። ከተመዛኞቹ 53 ሺ 26ቱ ምዘናውን ማለፋቸውንም ገልጿል።
የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሸዊት ሸንካ የባለስልጣኑ የስድስት ወር ሥራ አፈጻጸም በግሎባል ሆቴል ትናንት በገመገመበት ወቅት እንደተናገሩት፣ በተለያዩ ዘርፎች የሙያ ብቃት ምዘና ፈልገው ጥያቄ ያቀረቡ ተመዛኞች ቁጥር ወንድ 35 ሺ 110 ሴት 66ሺ 731 በድምሩ 101 ሺ 841 ተገልጋዮች ሲሆኑ፣ አገልግሎቱንም በጠየቁበት አግባብ አግኝተዋል። ምዘናውን ከወሰዱት መካከልም ወንድ 18 ሺህ 544 ሴት ደግሞ 34 ሺህ 482 በአጠቃላይ 53 ሺ 26ቱ ብቁ መሆናቸው ተረጋግጧል።
ምዘናው ከተሰጠባቸው ዘርፎች መካከልም የመካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ሙያተኞች፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች፣ የመደበኛ ሰልጣኞች እና የአጫጭር ስልጠና አገልግሎቶች እንደሚገኙበት ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል።
በባለስልጣኑ የእቅድ ዝግጅትና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ዘመነ አብዩ በበኩላቸው እንዳስረዱት የግማሽ ዓመቱ የምዘና አፈጻጸም በምዘና ዘርፎቹ ሲታይ አጫጭር የሥልጠና ዘርፎች ላይ የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል። ከተመዘኑት 27 ሺ 883 ተመዛኞች መካከልም 19 ሺ513 ወይም 70 በመቶ ገደማ ብቁ መሆናቸው ተረጋግጧል። በሌላ በኩል ደግሞ 26 ሺ 512 የከፍተኛ ኢንዱስትሪ ተመዛኝ ሙያተኞች መካከል ዘጠኝ ሺህ 730 ወይም 36 ነጥብ ሰባት በመቶ ብቻ ብቁ መሆናቸውንና አፈጻጸሙም ዝቅተኛ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት የተመዛኞች የማለፍ ምጣኔ እየጨመረ መሄዱ የተመዛኞቹን የብቃት ደረጃ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የተቋማትን ውጤታማነት ለማሳደግም ያግዛል።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2012
ሙሐመድ ሁሴን