አዲስ አበባ፡- የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በመቶ ቀናት እቅዱ ከያዛቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናትን ወደ ማዕከል የማስገባት ጥረቱ አለመሳካቱን ገለጸ።
በሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ እንደ ገለፁት፤ ሚኒስቴሩ በመቶ ቀን እቅዱ ፈተና የሆኑ ጉዳዮችን ለይቷል። በዚህም ህጻናትን ወደ ማዕከላት ማስገባት የመጀመሪያውን ድርሻ ይይዛል። የጎዳና ህጻናትን በመታደግ ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ ቢሠራም ወደ ማዕከል ለማስገባት የተደረገው ጥረት ግን በሚፈለገው ልክ አልተሳካም።
በመቶ ቀናት ውስጥ 300 ህጻናትን ከጎዳና ላይ አንስቶ ወደ ማዕከል ለማስገባት የታቀደ ቢሆንም አንዳንድ ክልሎች ካደረጉት መጠነኛ ጥረት ውጪ የታቀደውን ያህል አልተሠራም። በተለይም በፌዴራል ደረጃ የጎዳና ህጻናትን ወደ ማዕከል ለማስገባት አለመቻሉን ተናግረዋል።
በህጻናት ድጋፍ አገልግሎት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚገመት በአይነትም ሆነ በገንዘብ ተሰባስቦ ችግሩ ላለባቸው ህጻናትና ወጣቶች መስጠት መጀመሩን ያነሱት ወይዘሮ አለሚቱ፤ በተለይም አንዳንድ ክልሎች በማህበረሰብና በግለሰቦች ድጋፍ ማዕከላት እንዲገነቡ ጥረት ቢደረግም በግለሰቦች እጅ የሚገኙትንና በህግ ሂደት ላይ ያሉትን አስመልሶ መጠቀም አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ጠቁመዋል።
በሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የሴቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ በበኩላቸው፤ በመቶ ቀን እቅዱ ጥሩ እንቅስቃሴ እየታየ ቢሆንም በታቀደው ልክ መንቀሳቀስ አልተቻለም። በተለይም የመፈጸም አቅም ማነስና ከበጀት ጋር ተያይዞ ከዘርፍ ዘርፍ ልዩነት ተስተውሏል። ለሚከሰቱ ችግሮች ቅንጅታዊ አሰራር ያለመኖር የመቶ ቀን እቅዱ በውጤት እንዳይደገፍ አድርጓል ብለዋል።
ሴቶችን በሚመለከት «የጀግኒት» ንቅናቄ አንዱ ማሳያ መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ስመኝ፤ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተኮር ሥራ የተሻለ ለውጦች አስገኝቷል። እንቅስቃሴዎቹ በሴቶች ላይ «እንችላለን!» የሚል ስሜትና የአቅም ግንባታን ፈጥረዋል። ይሁን እንጂ አላሻግር ያሉ ምክንያቶች አሁንም በመኖራቸው፤ በመንግሥት አቅም ብቻ የማይሠሩ እንደ ማዕከላት ግንባታ አይነቶች ሚኒስቴሩን እየፈተኑት መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው