በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይ የተናገሩት- 1955 ዓ.ም.
ታላቁ ቤተ መንግሥት በሌላ በኩል “የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት” ተብሎ ይታወቃል። ይህ ቤተ መንግሥት ላለፉት 130 ዓመታት በርካታ አገራዊና አህጉራዊ ፋይዳ ያላቸው ሁነቶች የተፈፀመበት እንደሆነ ይታወቃል። ቤተ መንግሥቱ 40 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ 13 ሔክታሩ አንድነት ፓርክ ያረፈበት ስፍራ ነው። ፓርኩ የገንዘብ ድጋፍ በሰጡ ተባባሪ አካላት የተገነባ መሆኑ ይነገራል። በዚህም ፓርክ የጥቁር አንበሳ ሥፍራ፣ የአገር በቀል እፀዋት ማሳያ፣ የየክልሉ እልፍኞች፣ የአረንጓዴ ሥፍራ፣ ታሪካዊ ሕንፃዎችና አውደ ርዕዮታቸው እንዲሁም የአንድነት የእንስሳት ሥፍራ የሚባሉ የጉብኝት መዳረሻዎች ይገኛሉ።
ከስድስቱ የጉብኝት መዳረሻ ሥፍራዎች “ታሪካዊ ሕንፃዎችና አውደ ርዕዮቻቸው” በሚል በቀረበው ሥፍራ ታዋቂ አደባባዮች፣ ታላላቅ ሕንፃዎችና ግንባታዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ፊት በር፣ አላማጣ በር፣ “ደጋ አራርሳ” ተብሎ የታወቀው የሕዝብ ማቆያ ሥፍራ፣ ታላቅ የግብር አዳራሽ፣ ዙፋን ቤት / አዳራሽ (የደርግ መሰብሰብያ አዳራሽና እስር ቤት)፣ የአፄ ምኒልክ እልፍኝ፣ የአፄ ምኒልክ ጽ/ቤትና ጸሎት ቤት (እንቁላል ቤት)፣ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል እልፍኝ፣ የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) መቆያ ክፍል፣ የልዑላን መኝታ ቤቶች፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና የዙፋን ችሎት (የደርግ ሊቃነ መናብርት ጽሕፈት ቤት) ይገኙበታል።
በፓርኩ ታሪካዊ ሥፍራ የኢትዮጵያ መንግሥታት ታሪክ መነሻና መድረሻ በአውደ ርዕይ ተዘጋጅቶ ለእይታ ቀርቧል። በዚህም ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ የመንግሥታት ታሪክ እንዳለን ለማየት ይቻላል። የኢትዮጵያ መንግሥታት ታሪክ መነሻና መድረሻ ተዘጋጅቶ ለእይታ ከመቅረቡ ጋር በተያያዘ ከፓርኩ ዳይሬክተር፣ ከምሁራን እና በወቅቱ ታሪካዊ ቦታውን ሲጎበኙ ያገኘናቸውን በማነጋገር ለንባብ አቅርበናል። መልካም ንባብ!
የአንድነት ፓርክ ዳይሬክተር ዶክተር ታምራት ኃይሌ የኢትዮጵያ መንግሥታት ታሪክ መነሻና መድረሻ ተዘጋጅቶ ለእይታ መቅረቡ ዋና ዓላማውንና ፖለቲካዊ ጥቅሙን ሲገልፁ፤ የመንግሥታት ታሪክ መቅረቡ በዘመነ መንግሥታቸው የፈፀሟቸውን ታላላቅ ክንውኖች በመዘከር ትውልድን የማስተማር፣ የማሳወቅ ዓላማ አለው። ፖለቲካዊ ጥቅሙ ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደምንመለከተው መንግሥታት ከእነሱ ቀደም ብለው የነበሩ መሪዎችንና የመንግሥታት ዓይነቶች በማጣጣል፣ በማጥፋት እንዲሁም ሥፍራን ትኩረት በመንሳት ተጠምደው ይታዩ ነበር። ለነዚህ ማሳያ የሚሆኑ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጊዜ ስለልጅ እያሱ የነበረው አረዳድ፤ ደርግ ሥልጣን በያዘበት ጊዜ ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የነበረው አረዳድና አያያዝ፤ የማጣጣል እንዲሁም የመደበቅ ነገሮች ነበሩ።
እንዲህ አይነቱ አረዳድ ለአገርም ለፖለቲካውም ስለማይጠቅም የነበሩትን የነገሥታት አይነቶችንና ምንነት እንዲሁም የመሪዎችን ማንነት በሚዛናዊነት ለማስቀመጥ ጥረት ተደርጓል። ስለሆነም ፖለቲካዊ ጥቅሙ በቀጣይ የማጣጣል፣ የመደበቅ፣ የመፋቅ እና የማውደም ነገሮች እንዲቀሩ እንዲሁም በዚህ መጠመድን ያስተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከቀደመው ዘመን መልካም ነገሮች ለማስቀጠል፤ መልካም ያልሆኑትን ተምረንበት እንዳይደገሙ ለማድረግ ያግዛል ይላሉ።
ለእይታ የቀረበው አውደ ርዕይ የኢትዮጵያ ታሪክ እስከ አንድ መቶ ሃምሳ ዓመት የሚሆን ታሪክ ነው ያላት የሚለውን ያስቀር ይሆን ወይ? የሚል ጥያቄ አንስተንላቸው ዶክተር ታምራት ሲመልሱ፤ ‹‹አያስቀርም። ምክንያቱም የታሪክ አረዳድን ማወቅ በጣም ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ እና የኢትዮጵያ የመንግሥታት ታሪክ ለየቅል ናቸው። ታሪክ ብለን ስንል ብዙ ጊዜ የተዛባ አረዳድ አለን። የሕዝቦች ታሪክ እንደማህበረሰብ ሰብል እያመረቱ፣
ከብት እያረቡ በአንድ ቦታ ላይ የመኖር ታሪክ አለ። በሌላ በኩል እነኝሁ ሕብረተሰቦች የሥልጣን ተዋረድ ባለው የኃይል አደረጃጀት መንግሥት መስርተው የሚኖሩበት የታሪክ ዘመን አለ።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ ከ3 ሺህ በላይ ከ5 ሺህ በላይ ጥንታዊና የሰው ልጅ ታሪክ ከተመዘገበበት በቃልም ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮ ሲኖሩ ነበር። ስለአንድ መቶ እና አንድ መቶ ሃምሳ ዓመት ታሪክ ስናወራ ደግሞ ከአገረ መንግሥት ጋር የተያያዘ ነው። አገረመንግሥት ደግሞ የተለያዩ አላባውያን አሉት። አንደኛው አላባ የራሱን የሥልጣን ተዋረድ ተጠቅሞ የተቋቋመ ተቋማት መኖሩ ነው።
ይሄን ተቋም ስንመለከት በአክሱም፣ በዛጉዬ፣ በጎንደር፣ በሸዋ፣ በአዳል፣ ወዘተ. እንዲሁም በደቡብም በደቡብ ምዕራብም የተለያዩ መንግሥታት ነበሩ፤ እንደየራሳቸው የተለያዩ የታሪክ ጊዜያት አላቸው። ሁለተኛው አላባ ደግሞ እነዚህ ወደ አንድ የመጡበትን ጊዜ መልካዓምድራዊውን በማየት የምንናገርበት ነው።
ይሄ ከሆነ አንድ መቶ ሃምሳ ዓመት ሊሆን ይችላል። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ ግን አንድ መቶ ሃምሳ ዓመት አይደለም፤ በጣም ጥንታዊ ነው። ስለሆነም የምናወራው ታሪክ ስለኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ ነው፤ ስለመንግሥታት ታሪክ ነው፤ ወይስ ስለመልካዓ ምድር ነው ብሎ ማለት ያስፈልጋል። ይህንንም ብዥታ ማጥፋት ይኖርብናል›› ብለዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በቅርስና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳሬክተር ናቸው። ስለፓርኩ ታሪካዊ ሥፍራዎች ዋና ዓላማና ፖለቲካዊ ጥቅሙ በተመለከተ ከዶክተር ታምራት ጋር የተመሳሰለ ሐሳብ አላቸው። የኢትዮጵያ ታሪክ እስከ አንድ መቶ ሃምሳ ዓመት ነው ለሚሉት አስተያየታቸውን ሲሰጡ፤ አንዳንዶቹ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ከአፄ ቴዎድሮስ ጊዜ ጀምሮ ያለው ነው የሚሉ አሉ፤ የኢትዮጵያ ጂኦፖለቲካ ድንበሩ የተፈጠረው አንድ መቶ ዓመት ነው የሚሉ አሉ።
የኢትዮጵያ ታሪክ የሦስት ሺህ ዓመታት ታሪክ ነው የሚሉ አሉ። የመንግሥታቱን ታሪክ ከሆነ ያ ሌላ ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ ማለት ግን የሕዝቦች ታሪክ ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ ከሦስት ሺህ ዓመታትም በላይ ጥንታዊ ነው። አገራችን የሰው ዘር መገኛ ነች እያልን የምንኮራ ሕዝቦች በሌላ በኩል ሦስት ሺህ፣ አንድ መቶ ሃምሳ፣ አንድ መቶ እያልን የምንል ከሆነ የሚጣረስ ነው ይላሉ።
መምህር መክብብ ገብረማርያም በአዲስ አባበ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ከፍተኛ የጥናት ባለሙያ ናቸው። የአንድነት ፓርክ ታሪካዊ አውደ ርዕዩን በማየት የአሁኑ ትውልድም ቢሆን የሚሠራው መልካም ሥራ ለነገው ተተኪ ትውልድ የሚተላለፍ መሆን እንደሚገባው፤ መልካም ታሪክ መሥራት እንደሚያስመሰግንና መጥፎ ታሪክ መሥራት ደግሞ እንደሚያስወቅስ የሚያስተምር ዋና ዓላማ ያለው ይመስለኛል ብለዋል።
ፖለቲካዊ ጥቅሙን ሲናገሩ፤ በመጀመሪያ ኢትዮጵያውያንን በጋራ አስተሳስረው የቆዩ የተለያዩ የሃይማኖት ተቁዋማትን፣ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህላዊ አኗኗርና ሌሎችንም ሳይለይ የኋላ ታሪካችንን ያስተላለፈልን ይህ ታላቁ ቤተ መንግሥታችን ነው ብሎ ተቀብሎ የተሻለ ታሪክ ለመሥራት የሚያነሳሳ መሆኑን ይገልፃሉ። በሁለተኛ ደረጃ ብለው ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ ከ120 በላይ ኤምባሲዎች አሉ፤ ከ20 በላይም የውጭ እህት ከተሞች ጋር ከተማዋ ተፈራርማለች። ሌሎችም ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ድርጅቶች አሉ። እነዚህ አዲስ አበባን ሁለተኛ ከተማቸው እንደሆነች በመቁጠር ታሪካዊው ርዕዩንም በማየት የኋላው ታሪካችንን እንዲማሩበት፣ እንዲያደንቁትና እንዲዝናኑበትም ያደርጋል ሲሉ አስተያየት ይሰጣሉ።
ለዕይታ የቀረበው ታሪካዊው አውደ ርዕይ ኢትዮጵያ እስከ አንድ መቶ ሃምሳ ዓመት የሚሆን ታሪክ ነው ያላት የሚለውን ያስቀር ይሆን ወይ? ለሚለው ጥያቄ መምህር መክብብ ሲመልሱ ‹‹አዎን ያስቀራል፤ አንድ መቶ ሃምሳ ዓመት ማለት የአንድ ሰው ዕድሜ ሊሆን የሚችል ነው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ ደግሞ በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ነው። የአንድ መቶ ሃምሳ ዕድሜ ነው የሚለው ትርክት ግን ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነን ያሳለፍናቸው የመራራና የመልካም ታሪክ ሂደቶችን ያላገናዘበ ነው›› ብለዋል።
በደርግ ጊዜ የተካሄዱት መልካም ያልሆኑ ሥራዎች እንደቀረበው ሁሉ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመንም የተካሄደው አልተካተተም ለሚሉ ወገኖች ምላሻችሁ ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ ዶክተር ታምራት ሲመልሱ፤ ‹‹በመንግሥታት አውደ ርዕይ ውስጥ ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ እስከ አቶ ኃይለማርያም የአገር መሪዎች አጭር ታሪክ እና በዘመናቸው ያደረጉትን የሚገልጽ አቅርበናል። የዙፋን ቤቱ ምድር ቤት በንጉሡ ጊዜ የመጠጥ ማቀዝቀዣ ነበር። በደርግ ጊዜ ባለሥልጣናት የታሠሩበት፣ የተገረፉበት እንዲሁም የተገደሉበት ሥፍራ ነበር። ሕንፃው ራሱን እንዲገልጽ ነው የተደረገው።
ሌሎቹም ታሪካዊ አውደ ርዕዮቹ ሕንፃውንና ሥፍራውን ተከትሎ ራሳቸውን እንዲገልፁ ተደርጓል። ይህ ሲሆን አንዱን ከፍ አንዱን ዝቅ ለማድረግ የተደረገ ነገር የለም። አፄ ምኒልክ ከዚህ ግቢ ውስጥ ሆነው የወሰዱት የኃይል እርምጃ የለም›› በማለት መልሰዋል። መምህር መክብብ በጉዳዩ ላይ ምላሻቸውን ሲሰጡ፤ ‹‹ለኢትዮጵያ ክብርና ዘላለማዊነት የለፉ ብዙዎች ነገሥታትም ሆኑ መንግሥታት በዘመናቸው ለሥራቸው ዕንቅፋት ይሆኑብናል የሚሉትን ሲመክሩ፣ ሲገስፁና ሲቀጡ ይስተዋላሉ። ይህን ደግሞ አገርን ለማቅናትና ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ሲሉ ተጠቅመውበት አልፈዋል።
በደርግ ጊዜ እንደነበረው በግቢው ውስጥ የማሰቃያ ቦታ አልነበረም›› ብለዋል። ረዳት ፕሮፌሰር አበባውም አስተያየታቸውን ሲሰጡ፤ ‹‹በሁሉም መንግሥታት በጎም መጥፎም ተግባራት ተፈፅመዋል። ቦታውን በደንብ ማወቅ ያስፈልጋል። ቀደም ሲል የመጠጥ ማቀዝቀዣ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው በደርግ ጊዜ ወደ እሥር ቤት ተቀይሯል። ያንን ለመዘከር በቦታው ላይ ተቀምጧል እንጂ የደርግን ህፀፅ ብቻ አስቀምጦ የሌላውን ሳይነኩ ለመቅረት አይደለም። አፄ ምኒልክ እሥር ቤት አድርገውት ቢሆን ኖሮ ያንን በሚያሳይ መልኩ ይቀርብ ነበር›› ብለዋል።
በደርግ ጊዜ የነበረው የመገዳደሉና የመጠፋፋቱን ሂደት ከአውደ ርዕይው መረዳት ይቻላል። ይህን በመመልከት አሁንም ከባለፈው አልተማርንም ለሚሉ ሰዎች ዶክተር ታምራት ምላሽ አላቸው። እኔ እንደማውቀውና እንደተማርኩት በዓይነቱም በመጠኑም የተካሄደው ነገር ሰፊና አሰቃቂ ነበር። የአንድ ሰው ሕይወት ክቡር ነው። ነገር ግን አልተማርንበትም ከማለት በፊት ከነበረው ጋር ምን ያህል ተመጣጣኝ ነው? ሊነፃፀርስ ይችላል ወይ? ብሎ መመርመር ያስፈልጋል ይላሉ።
መምህር መክብብ በደርግ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከመሳፍንት ዘመን ጀምሮ የተከሰቱት የርዕስ በርዕስ መጠፋፋትና መተላለቅ እንደማይጠቅም የምንማርባቸው አሰቃቂ የሆኑ ታሪኮች አሉ። ከነዚህ መጥፎ ታሪካችን ልንማር ይገባል። ሲከናወን የነበረውን ካነበብን ከበፊቶቹ ጋር በንፅፅር ሊቀርብ የሚችል አይደለም ብለዋል። ረዳት ፕሮፌሰር አበባውም በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፤ የተሳሳተ የፖለቲካ አካሄድ ከ1940 ዎቹ እና 50 ዎቹ ጀምሮ ማካሄድ ጀምረናል።
ፖለቲካ ውይይትና ስምምነትን ይጠይቃል። ከውይይትና ከስምምነት ይልቅ አቋም ይዞ ላለመወያየት መፈለግ እስከ አሁን ድረስ አለቀቀንም። በተማሪዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴም፣ በአብዮቱም ዘመን ቀጥሎ ከዚያም በኋላ የፖለቲካው ውርዴ አለቀቀንም። በመሐል ሊያሸጋግረን የሚችል ፕላት ፎርም አልመሰረትንም። የተለያዩ የአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ዋና ማሳያ የሆኑትን በመዘክርነት መቅረቡ ትውልድን ያስተምራል ብለዋል።
በዙፋን (ዘውድ) ቤቱ ምድር ቤት ውስጥ ስለነጭ ሽብርና ቀይ ሽብር የሚያመላክት፤ «መስከረም 1969 ዓ.ም. ግራ ዘመም የነበረው ኢሕአፓ አባላቱ መታሠራቸውን ተከትሎ ኢሕአፓ በመኢሶን አባላት ላይ ነጭ ሽብር ማካሄድ ጀመረ። መስከረም 13 ቀንም ኢሕአፓ ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያምን ለመግደል ያልተሳካ ሙከራ አደረገ። ይህንን እርምጃ ነጭ ሽብር ብሎ የሰየመው መኢሶን ነበር።
መኢሶንና ሌሎች ድርጅቶች ደርግ ነጭ ሽብርን እንዲመክት ጥያቄ አቅርበው ነበር። በየካቲት ወር 1969 ዓ.ም. አያሌ የደርግ ደጋፊዎች በኢሕአፓ ነጭ ሽብር ተገደሉ። በዚህ የተነሳ ደርግ በነጭ ሽብር ላይ አፀፋ ለመውሰድ አባላቱንና ደጋፊዎቹን አስታጥቆ ቀይ ሽብርን አወጀ። ከመጋቢት 1969 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 1970 ዓ.ም. የሽብር እርምጃዎች በአያሌዎች ላይ ተወሰደ።» በሚል በዲስፕሌይ ለዕይታ ቀርቧል። በዚህ መልኩ በመቅረቡ ስለሁለቱም ሽብሮች ግንዛቤ ይሰጣል። በአገር ደረጃ ስለቀይ ሽብር ብዙ ስለሚወራና የሰማዕታት መታሰቢያም ስለቀረበ ስለነጭ ሽብር ሰምተው የማያውቁ ሰዎች በምድር ቤቱ በቀረበው ግር ሲላቸው ይስተዋላል።
የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ብቻ በመስቀል አደባባይ በአገር አቀፍ ደረጃ መቅረቡን በተመለከተ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አስተያየት ሲሰጡ፤ ‹‹ ማን ነው ሰማዕቱ? ማን ነው አጥፊው? ይህን በተመለከተ ብዙ ጊዜ የነብሩና የአዳኙ ታሪክ ይነሳል። አዳኙ ነብሩን ሲገድል ጀግና ነው፤ ነብሩ ግን አዳኙን ከገደለው የአውሬ፣ የአረመኔ ድርጊት ነው። የቀይ ሽብር ሰማዕታት ከሚባል ነጭ ሽብርንም እንዲያካትት “የሽብሩ ሰማዕታት” ተብሎ ማስቀመጥ ይገባል። ምክንያቱም በፖለቲካ አመለካከት አንዱ አንዱን ገድሏል።
የቁጥር መብዛትና ማነስ አይደለም፤ አንድም ብዙ ነው። አንዱን ቅዱስ አንዱን እርኩስ ከማድረግ ይልቅ ሚዛን ላይ አስቀምጦ ሁሉንም ለምን አንዘክርም›› ብለዋል። መምህር መክብብ በጉዳዩ ላይ ሲናገሩ፤ ‹‹በአገር አቀፍ ደረጃ ከተሠራ ባለፉት ሦስት ሺህ ዘመናትም የመንግሥትን ሥርዓት በተቃወሙት ላይ የተለያዩ በደሎች ደርሰዋል፤ በዚህም ብዙዎች መስዋዕት ሆነዋል። እነዚያንም የሚዘክር ቢሆን መልካም ነበር። ካልሆነ ግን ነጭ ሽብርን ገለል አድርጎ ቀይ ሽብርን ብቻ ነጥሎ አጉልቶ ማቅረብ አግባብነት የለውም፤ ይህ የተሳሳተ ሚዛን እውነተኛውን ታሪክ ለሚፈልግ ትውልድ ያደናግራል›› በማለት ገልፀዋል።
ዶክተር ታምራት በደርግ ጊዜ በእሥር ቤትነት ያገለግል የነበረው ምድር ቤት ውስጥ በየግድግዳው ላይ በእሥረኞች የተጻፉ ጽሑፎች የሚኖርበት አጋጣሚ ሊኖር ስለሚችል አሁን በሚታየው መልኩ ቀለም መቀባቱ ለምን አስፈለገ ለሚለው ጥያቄያችን ምላሽ ሲሰጡ፤ አንድነት ፓርኩን ተቀብለን ስናደራጅ የዙፋን ቤቱን ምድር ቤት ያገኘነው አሁን በሚታየው መልኩ ስለሆነ ለምን በዚህ መልኩ እንደታደሰ የማውቀው ነገር የለም ብለዋል።
መምህር መክብብ አሁን በሚታየው መልኩ ቀለም መቀባቱ ተገቢነት ላይ ያላቸውን ሐሳብ ሲያካፍሉ፤ ለቤተ መንግሥት የምንሰጠው ክብርና ከሱም የምንጠብቀው ዓለም አቀፍ ገፅታ አለ። ያንን ታላቅ ገፅታ የሚያሳጣብን ይመስለኛል። በእስር ላይ በመቆየታቸው፣ በመሰቃየታቸው፣ ወዘተ. አዕምሯቸው ከሚችለው በላይ ሆኖ ግድግዳውን ቦርቡረው እነሱን የማይመጥን ጽፈው ሊሆን ይችላል። ያንን ቤተ መንግሥት ውስጥ ለዕይታ ማቅረቡ አግባብ አይመስለኝም ብለዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ምድር ቤቱ ከዚህ በፊት እድሳት ሲደረግለት ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎ እንደሆነ ገልፀው፤ የተጻፈ ነገር እንዳልነበረ፣ ጽፈንበታል የሚሉ ሰዎችም እስከ አሁን እንዳልገጠማቸው፣ ግድግዳው ከጠንካራ አለት የተሠራ ስለሆነ ለመጻፍም ምቹ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
‹‹አጨቃ ጫቂ ነገር የነበረው የቀለሙ ጉዳይ ነው›› ይላሉ። ነጭ ቀለሙን ተቀብለናዋል። የነበረው ገጽታ ግን ለወጣትና ለህጻናት አይደለም፣ ነፍስ ላወቀና ምራቅ ለዋጠም ቢሆን በጣም አስፈሪ ነበር። ቀለል ባለ መንገድ ማስተማሪያ እንዲሆን ለማድረግ ተብሎ የቀረበ ነው በማለት ያስረዳሉ።
ዶክተር ታምራት ለጎብኝዎች መልዕክት ሲያስተላልፉ የታሪካዊ አውደርዕዮች ላይ ያለውንም ሆነ ሌሎች ስፍራዎች ላይ ያለውን ለመጎብኘት ሲመጡ በጥንቃቄ የተዘጋጀ ስለሆነ እንዲሁም በጣም ሰፊ በመሆኑ እረጋ ብሎ በማስተዋል መመልከት ስለሚያስፈልግ ጊዜ ሰጥቶ ለመመልከት ወስኖ መምጣት ያስፈልጋል። ጊዜ ወስደው የሚመለከቱ ከሆነ ይዝናኑበታል፤ ይማሩበታል።
ታሪክም፣ ባህልም፣ ቅርስም፣ ተፈጥሮም ይጠብቁበታል። ለአገር ገጽታ ግንባታም ይጠቀሙበታል። በልዩ ቲኬት የወሰዱ ሙሉ ፓኬጅ አለን፤ በተለያዩ ቋንቋዎች አስጎብኚ ይመደብላቸዋል። መደበኛ ለቆረጡ ሰዎች ደግሞ ይሄ እንዳይጎድል በር ላይ መግለጫ ይሰጣል፤ አቅጣጫና መረጃ የሚሰጥ በራሪ ወረቀት ተዘጋጅቶ ቀርቧል። ከዚህ በተጨማሪ በየታሪካዊ ሕንፃዎቹ ላይ ዲስፕሌዮች አሉ። እልፍኞች ጋ በኦዲዮ ቪዥዋል የሚገልፁ አሉ ብለዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር አበባየውም ጎብኝዎችን በተመለከተ ሲናገሩ ከስያሜው ጀምሮ ብሩህ ማሰብ ያስፈልጋል፤ ቀደም ሲል ጀምሮ ጠንካራ የሆነው በአንድነታችን ነው። አንዱን ከፍ አድርጎ ሌላውን ዝቅ አድርጎ የመመልከት ነገር ትቶ ሁሉንም አይቶ አገር እንድታድግ ብሩህ መመኘት ያስፈልጋል። አገራችን በቅድሚያ የምታድገው አዕምሯችን ውስጥ ባለው የአገር ሀሳብ ነው። የወደፊቷን ኢትዮጵያን ለመገንባት የእኔ ድርሻና ፋንታ ምን ሊሆን ይገባል እያሉ መመልከት ያስፈልጋል። በተለይ የጆኔፍ ኬኔዲን ‹‹ለአገሬ ምን ውለታ ልዋል እንጂ አገሬ ምን ትዋልልኝ ብለህ አታስብ›› የሚለውን አባባል ሰዎች ቢያጤኑት መልካም ነው ይላሉ።
መምህር መክብብ ታሪካዊ አውደ ርዕዮችን ለመጎብኘት ለሚመጡ ሰዎች መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ ወደ ታሪካዊ የዳግማዊ ምኒልክ ታላቁ ቤተ መንግሥት ውስጥ ሲገቡ የኢትየጵያን ታላቅነት ማየት የሚያስችል አዕምሮን ይዞ መግባት ያስፈልጋል። አጥብበው ከገቡ ግን ባጠበቡት ልክ ነው የሚረዱት። የዕይታ አድማሳቸውን አስፍተው ከገቡም የስፋቱን ያህል ማየት ይችላሉ ብለዋል።
በመጨረሻም ቢካተት ብለው የሰጡት አስተያየት ደግሞ፤ በብላቴን ጌታ ማህተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል በ1962 ዓ.ም. “ዝክረ ነገር” በሚል ርዕስ በቀረበው መጽሐፍ ላይ ወደ ታላቁ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተመንግሥት የሚያስገቡ ስምንት በሮች አሉ (ፊት በር፣ እቴጌ በር፣ ሠረገላ በር፣ ሥርቆሽ በር፣ ብር ቤት በር፣ ጎተራ በር፣ ገብርኤል በር እና ቄራ በር)። ከእነዚህም በተጨማሪ ገና ከመግቢያዎቹ በሮች ጀምሮ ወደ ግብር ቤቱ በር ድረስ የሚያደርሱ፣ ከውስጥም ተቀብለው የሚያስቀምጡ ግብር የሚያበሉና ሌሎችም አለባበሳቸው ቁመናቸውና ወዘተ. ማንነት ሊያሳዩ የሚችሉ በአካልም ሆነ በተንቀሳቃሽ ምስል ማቅረብ ይቻላል። አሁን በግብር ቤቱ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ከመታየታቸው ውጭ ሌሎች እንብዛም የሚታዩ ነገሮች ስለሌሉ በደንብ ከታሰበበት በአዳራሹ ውስጥ ሊጎበኙ የሚችሉ ብዙ ነገሮችን ማዘጋጀት ይቻላል ብለዋል።
በአንድነት ፓርክ ታሪካዊ ሥፍራውን ስትጎበኝ ያገኘናት ዝናሽ ከበደ በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ውስጥ የኪነጥበብ ኢንዱስትሪ ማበልፀግና ማስፋፋት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናት።
አስተያየቷን ጠይቀናት እንደሚከተለው ሰጥታናለች፤ ‹‹በቅድሚያ ዶክተር አብይ አህመድ በዚች በቆዩባት አጭር የሥልጣን ጊዜ ውስጥ ቀደምት የኢትዮጵያ ታሪክ ተደራጅቶ ለሕዝብ ዕይታ እንዲቀርብ ሁኔታዎችን ስላመቻቹ በዚህ አጋጣሚ አድናቆቴን መግለጽ እወዳለሁ። በርቱ! ከዚህ በላይ ጠንክረው ሠርተው አሳዩን እላለሁ›› ብላለች። አስተያየቷን በመቀጠል ‹‹አዲስ አበባ ላይ በስፋት ሊጎበኝ የሚችል ታሪካዊ ቦታ አልነበረም። በአንድነት ፓርክ ውስጥ ግን በስፋት ሊጎበኝ የሚችል ታሪካዊ ቦታ አግኝተናል።
ቤተ መንግሥቱ ጫካ እንደሆነና የሚያስፈራ ሁኔታ እንዳለው ነበር የሚታወቀው። ገብተን የተለወጡ ነገሮች አይተናል። የበፊቱን ገጽታ የሚያሳይ በፎቶ፣ በተንቀሳቃሽ ምስል ወይም በጽሑፍ ቢቀርብ ጥሩ ነበር፤ ያም ታሪክ ነውና። አሁን የተሠራውን ሥራም አጉልቶ ያሳያል። በነገሥታቱ ታሪክ ላይ በደርግ ላይ እንደቀረበው በሌሎቹም ላይ እንደዚሁ ሚዛኑን የጠበቀ ክፉውንም ደጉኑም ሊያሳይ የሚችል ቢቀርብ ለማስተማሪያነት ይረዳል።
በአንድነት ፓርክ ስለነጭ ሽብር እና ቀይ ሽብር ግንዛቤ ለመያዝ በሚያስችል ደረጃ ቀርቧል። በአገር አቀፍ ደረጃ ስለቀይ ሽብር ብቻ የሚገልጽ የሰማዕታት መታሰቢያ ከሚቀርብ ይልቅ ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ስለነጭ ሽብርም ቢቀርብ ለማነፃፀር ይረዳል። ማንኛውም ሰው ታሪካዊ ቦታውንም ሆነ ሌላውን ቦታ ሳያይ ወይም በቅጡ ሳይረዳ ለፍረጃና ለፍርድ ባይቸኩል ጥሩ ነው። አንድነት ፓርክ ውስጥ ያለውን ጊዜ ሰጥቶ አይቶ ቢማርበትና ቢያውቅበት ጥሩ ነው። እኔ ያነበብኩትን ታሪክ በአካል ተገኝቼ በማየቴ በጣም ዕድለኛ ነኝ እላለሁ፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጥሩ መንፈስ ጊዜ ሰጥተው ቢመለከቱት መልካም ነው እላለሁ›› በማለት አጠናቃለች።
ሌላው ታሪካዊ ሥፍራውን ሲጎበኝ ያገኘነው ወጣት አንሙት ከልካይ በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የባህል እሴቶች ባለሙያ ነው። በመጀመሪያ በሶሻል ሚዲያው የሚወራውና ገብቼ ያየሁት በጣም የተለያዩ ሆነው ነው ያገኘሁት ይላል። በመቀጠል አቀራረቡ ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ታሪካዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ነው። በአንድነት ፓርክ ታሪካዊ ቦታውን ከማየቴ በፊት የማውቀው ስለቀይ ሽብር ነው።
አሁን ባየሁት ደግሞ ለቀይ ሽብር እርምጃ መነሻው ነጭ ሽብር እንደነበረ ለመረዳት ይቻላል። በመሆኑም ለካስ ይህም ነበር እንድል አድርጎኛል። በአንድነት ፓርክ የአገራችንን ገጽታ በሚገነባ መልኩ ከነገሥታቱ ታሪክ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያለውን የሚያሳይ ቀርቧል። ስለዚህ ማህበረሰባችን በማህበራዊ ሚዲያ አባባሎች ሳይደናገሩ በአካል መጥተው እውነተኛውን መረጃ አይተው ሁኔታዎችን አመዛዝኖ መረዳት ይኖርባቸዋል። እኛ ኢትዮጵያውያን ተባብረን እንደኖርን ሁሉ ተባብረን መቀጠል አለብን ብሏል።
በአንድነት ፓርክ በታሪካዊ ስፍራው የኢትዮጵያ መንግሥታት ታሪክ መነሻና መድረሻ በአውደ ርዕይ ተዘጋጅቶ ለዕይታ መቅረቡ ዋና ዓላማ፣ ፖለቲካዊ ፋይዳውና የታሪክ አረዳድ እንዲሁም ሚዛናዊነት በተመለከተ ግንዛቤ ሊሰጥ በሚያስችል መልኩ ለማቅረብ ተሞክሯል። የመጽሔት ዝግጅት ክፍላችን አንድነት ፓርክን ለመጎብኘት የሚመጡ ሰዎች አዕምሯቸውን ነፃና ሰፊ አድርገው ቢመጡ በአሰፉት ልክ ግንዛቤ ይዘው ለመሄድ ያስችላቸዋል የሚለውን የምሁራኑን ሐሳብ የሚጋራ ስለሆነ ታሪካዊ ሥፍራውንም በዚሁ መልኩ እንዲጎበኙ እኛም እናሳብባለን።
ዘመን መፅሄት ታህሳስ 2012
ስሜነህ ደስታ