ጊዜው በኅዳር ነበር። በሥራ ጉዳይ እግሬ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ሳይረግጥ አይውልም። በዚህ ምክንያት በየመግቢያው በጥበቃ ላይ የተሰማሩት አካላት ከታካሚዎች ጋር የሚፈጥሩት እሰጣ ገባ እመለከት ነበር። በወጉ ምላሽ ሰጥቶ ከማስረዳት ይልቅ የደከሙና ጉልበት ያጠራቸውን ታማሚዎች ገፍትሮ ማስለቀስ ከነውር አይቆጠርም። እኔም ለአንድ ጉዳይ በተመላለስኩ ቁጥር የደብዳቤ ቀን መቀየሩ ቢሰለቸኝ ለበላይ ኃላፊያቸው ጉዳዩን አቀረብኩ። ዳሩ ምን ዋጋ አለው እነሱም እንደኔው ኖረዋል፤ ውርጅብኝ ተቀባይ።
‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ›› አይደል ተረቱ። ሕክምና ፈላጊ ሆድ የባሰው ነው። በበሽታው ምክንያትም ባህሪው ሊቀየር ይችላል። በመሆኑም ከበር ጀምሮ መልካም ፊት ማየትን ይሻል። ከበር የተሰበረውን ስሜቱን ‹‹አንቱ›› የተሰኙት ዶክተር ሊጠግኑለት አይችሉም። ስለዚህ ሕክምና ከበር ይጀምራል መባሉም ለዚህ ይመስላል።
«የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጥበቃዎቹ ባህሪ ፊት ይጋረፋል። ሌላ ተጨማሪ ሕመም ይቀሰቅሳል። መድሐኒት እንደልብ ከውስጥ የላቸውም። ለመግዛት በተመላለስኩ ቁጥር ነግሬያቸው እወጣለሁ፤ ስመለስ ግን አላውቅሽም ይሉኛል፤ አምባጓሮ ይፈጥሩብኛል። አንድ ቀን መድሐኒት ለመግዛት ከግቢው እንደወጣሁ በር ላይ አውለውኛል» ያሉት ባለቤታቸውን በማሳከም ላይ የነበሩት ወይዘሮ ሒክማ ሰብረዲን ናቸው።
ወይዘሮ ሂክማ እንደተናገሩት፤ «የሆስፒታሉ ዶክተሮች አቀባበላቸው እና አገልግሎት አሰጣጣቸው በጣም አሪፍ ነው። ግን ምን ዋጋ አለው ከበር የሚያስገቡት ጥበቃዎች ለታማሚ የሚሆን ባህሪ የላቸውም። ሆድ ብሷቸውና ተረብሸው የሚመጡ ታካሚዎች የሚበዙ በመሆናቸው በሆስፒታሉ ላይ እንዲያማርሩ ያደርጓቸዋል።
ልጅ፣ቤተሰብ፣እናት እና አባት ያላቸው አይመስሉም። በተለይም በኢሚግሬሽን በኩል ባለው በር የሚሆኑት የጥበቃ ሠራተኞች ይብሳሉ›› ብለዋል። ለባለቤታቸው መዳን ከጸለዩት በላይ ‹ፈጣሪያቸውን የእነሱን አይን መልሰህ እንዳታሳየኝ› ብለው ማልቀሳቸውን አንስተዋል።
አቶ ተመስገን መኮንን በቅዱስ ጳውሎስ ሚዲካል ኮሌጂ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት፤ የታማሚዎች ሕክምና እንደተባለው ከበር ይጀምራል። በአቀባበል ከበር ጀምሮ ደስተኛ የሆነ ታካሚ በሚሰጠው ሕክምና ለመዳን እምነት ያሳድራል።
ቀደም ሲል የጥበቃ ሠራተኞች የቅጥር ሁኔታ በሆስፒታሉ ስር መደብ ኖሮት የሚፈጸም እንደነበረ የሚገልጹት ምክትል ኃላፊው፤ በደረጃ እድገትም ሆነ በዝውውር በሰፊው ሠራተኞች ይለቁ ነበር። በዚህ ምክንያት ከሦስት ዓመት በፊት የጥበቃና የጽዳት ሠራተኞች በውጪ እንዲቀጠሩላቸው ተደጋጋሚ ጨረታ ወጥቶ እንደነበረ ያሳታውሳሉ።
በ2011 ዓ.ም ግማሽ ዓመት ጀምሮ በወጣው ግልጽ ጨረታ «ላየን ሴኩሪቲ ኤጀንሲ» የተሰኘ ድርጅት አሸንፎ ማቅረብ ጀመረ። አጀንሲው የስው ኃይል ማቅረቡን እንጂ እንደዚህ ዓይነት ከሕክምና አገልግሎት ጋር በተገናኘ የተለየ አሠራርም ሆነ ልምድ አልነበራቸውም። በተለያዩ ሥልጠናዎች ሥራውን ወደሚፈልገው ችሎታ ለማድረስ እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል። አቤት ሆስፒታልን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ የአስተዳደሩ የሰው ኃይል በኤጀንሲዎች አማካኝነት እንዲሟሉ ተደርጓል። ሆስፒታሎቹም የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ብቻ እንደሚሰሩ አስረድተዋል።
በጠቅላላው 200 የሚደርስ የሰው ኃይል በኤጀንሲው አማካኝነት የቀረበላቸው ሲሆን ለፈረቃ (ለሽፍት) መሪዎች ሥልጠና መስጠታቸውን ተናግረዋል።
በአገሪቱ ውስጥ ለመስሪያ ቤቶች የሰው ኃይል የሚያቀርቡ ድርጅቶች አገልግሎትን ማዕከል ያደረጉ አይደሉም። በዚህ ምክንያት በየትኛውም ረገድ የሚመጡት ተቀጣሪዎች ያን ያክል በሚሰማሩበት ሥራ ሥልጠና የወሰዱ አለመሆናቸውን አንስተዋል። በመሆኑም በተደጋጋሚ ችግሮች እንደገጠሟቸው ያስረዳሉ።
በኤጀንሲው የቀረቡልን የሰው ኃይሎች በአብዛኛው የመጡት ከአዲስ አበባ ዙሪያ ነው። ታካሚዎችም በአብዛኛው የሚመጡት ከዚሁ አካባቢ በመሆኑ ይገጥሙ የነበሩ የተግባቦት ችግሮችን መቅረፍ እንዳስቻላቸው በበጎ ጎን አብራርተዋል።
ታካሚዎችን በተገቢው እንክብካቤ አድርጎ ከሚፈልጉት አገልግሎት ጋር በማገናኘት በኩል ችግሮች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ተመስገን፤ ከጥበቃ ሠራተኞች ጋር እሰጣ ገባ እንዳይፈጥሩና ምልልሶች እንዳይኖሩ ሰፊ ሥራዎች ተሰርተዋል።
ቋሚ የሆስፒታሉ ተንቀሳቃሽ (ራነርስ) አቅጣጫና አገልግሎት ከሚገኝበት ክፍል አድራሾች አሰማርተዋል። ካርድ ማውጣት፣ ካርድ መሰብሰብና ታማሚን ማድረስ የመሳሰሉ ተግባራትንም ይከውናሉ ነው ያሉት።
በጥበቃ ላይ የተሰማራ አካል ታካሚዎችን የመጠበቅ፣ ሠራተኛውን እና ንብረትን በተገቢው የመጠበቅ እንዲሁም አካባቢውን ሰላም እንዲሆን በማድረግ በኩል ኃላፊነት ነበረባቸው። ነገር ግን የሚገጥሙ ሰፊ ችግሮች አሉ። በሌላ በኩል እጅ ከፍንጅ የተያዘ ባለመኖሩ ርምጃ መውሰድ አልቻልንም እንጂ በካርድ ክፍል አካባቢዎች ገንዘብ ተጠየቅን የሚሉ ቅሬታዎች ጭምር የቀረቡበት ጊዜ እንደነበር ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ የሰው ኃይል አቅራቢ ኤጀንሲዎች ከፍተኛ ሀላፊነት ይወሰዳሉ። ለምሳሌ እቃ ቢጠፋ ከፋዮቹ አቅራቢዎቹ ናቸው። ላፕቶፕ ጠፍቶ እንደከፈሉም በምሳሌነት ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈ ከጥበቃዎች ምን ያህል ገንዘብና ለምን ያህል ጊዜ ኮሚሽን እንደሚቀበሏቸው በግልጽ እንደማያውቁት አስረድተዋል።
በአብዛኛው መስሪያ ቤቶች በቋሚነት የሚሰሩ ባለሙያዎች እንደአይነኬ ራሳቸውን እስከ መቁጠር ይደርሳሉ። በዚህ የተነሳም በመንግስት ስራ ላይ የሚያደርሱት በደል የበረታ ነበር። የኤጀንሲዎች ቅጥር እንደዚህ አይነት አላስፈላጊ መመጻደቆችን በማስቀረትና በመቀነስ በኩል ሚና እንደሚጫወትም አብራርተዋል።
በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደምሰው አሰፋ በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ የሚያሰራቸው ጥበቃዎች በአጀንሲ የተቀጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በቁጥር 61 የጥበቃ ሰራተኞች ሲሆኑ በግዥ ኤጀንሲ በኩል በጨረታ ተወዳድረው ‹‹አትላስ ››በተሰኘ ኤጀንሲ እንደቀረቡላቸውም ተናግረዋል።
ዘርፉ ሕክምናም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ታካሚን እንደየባህሪው ማስተናገድ የሚችሉ ናቸው ወይ በሚል ለተነሳው አቶ ደምሰው፤ በዚህ ደረጃ መገመት ከባድ መሆኑን ይገልጻሉ። ይሄ ችግር በየትኛውም ሆስፒታሎች የሚሰማ ቅሬታ ነው። ጥበቃዎቹም ተቀያያሪ ናቸው። ቁጥጥር የሚያደርገውም ቀጣሪው ኤጀንሲ እንደሆነ ያብራራሉ። በጥበቃ ሰራተኞቹ ላይ ስህተቶች ባጋጠሙ ወቅትም በደብዳቤ ለግዥ ኤጀንሲና ለቀጣሪው ኤጀንሲ እንዳሳወቁ ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ አክለው እንዳሉት ፤አሰልጥኖ የሚያመጣቸው ቀጣሪው አካል ነው። ስለዚህ በሆስፒታሉ በኩል ምንም አይነት የስልጠና ተግባር አልተሰጣቸውም።
ለሆስፒታሉ የጥበቃ ሰራተኞቹ በሌላ አካል እንዲቀርቡለት ሲደረግ ከዚህ በፊት ከነበረው የቅጥር አሰራር የተሻለ ለውጥ ይዞ መምጣት እንዳለበት የሚጠበቅ ነው። ሥለዚህ ኤጀንሲው ያቀረባቸው የጥበቃ ሰራተኞች በአገልግሎት እርካታን እያስገኙ ነወይ? በሚል ለተጠየቀው፤ የባለቤት ስሜታቸው፣አገልግሎት አሰጣጣቸው፣ አልፎ አልፎ የሥነምግባር ችግሮች እና ሰራተኞቹን በመለየት በኩል ከፍተኛ ችግሮች መኖራቸውን አብራርተዋል። እነዚህን ችግሮች በዝርዝር በደብዳቤ ለአቅራቢው ከማሳወቅ የዘለለ ሆስፒታሉ በቅጡ እንኳን ማዘዝና ማሰራት የሚቸገርባቸው ጉዳዮች መኖራቸውንም አክለዋል።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 8/2012
ሙሐመድ ሁሴን