ሁልጊዜ አዲስ ጣዕም በመፍጠር ትታወቃለች። ‹‹አዲስ ጣዕም›› የተሰኘ የቴሌቪዥን ሾው አዘጋጅና ዳይሬክተር ነች። በዓለምአቀፍ ደረጃ ታዋቂ ሼፍ የሚል ማዕረግን አግኝታለችም። የ21 አገራት ምግብን ጠንቅቃ መስራት የምትችል፤ ‹‹ናቹራል ሙዚዬም ላስቬጋስ›› ውስጥ ቋሚ ሾው የምታሳይበት ስፍራ ያላት፤ የወርቃማ ሰንሰለት ደራሲና አመጋገብ በሕይወት ጭምር ያስተማራት እንስትም ነች የዛሬ የሕይወት እንዲህ ናት አምድ እንግዳችን ሼፍ አዲስአለም ብዙአየሁ።
አዲስ አለም ተጀመረ
ትውልዷ ባህርዳር ከተማ ቀበሌ 13 በተለምዶ ‹‹ሽንብጥ›› ተብላ በምትጠራው ስፍራ ነው። ለቤተሰቡ ማሳረጊያ ልጅ የሆነችው አዲስአለም፤ የመጨረሻ ልጅ በቤተሰብ ውስጥ ልዩ እንክብካቤ ይደረግለታልና እንግዳችንም ይህንን ዕድል አግኝታለች። በተለይ ደግሞ ቤተሰቡ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ስለሚገኝ ሁሉ ነገር ተሟልቶላት ተንደላቃ እንድታድግ ነው የሆነችው። አዲስአለም ስም እንኳን ሲወጣላት ለየት ባለሁኔታ ነው። ስም አውጪው አባቷ ሲሆኑ፤ ይህንን ስም ያወጡላትም አዲስ የሥራ ምዕራፍ በመጀመራቸው እንደሆነ ትናገራለች። መጀመሪያ በሌላ ተቋም ሱፐርቫይዘር ሆነው ይሰሩ ነበር። ከዚያ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቀው በሕክምናው ዶክተር ሆኑ። ይህ የተሳካውና ወደ ሌላ የሥራ ዘርፍ የተዛወሩት እርሷ ስትወለድ ነው። በዚህም አዲስ የሥራ ምዕራፍ ጀመርኩ ሲሉ አዲስአለም ብለዋታል።
ነፃ ሆና እንድታድግ ዕድሉ የተሰጣት እንግዳችን፤ ገና በልጅነቷ ነበር ከገንዘብ ጋር የተዋወቀችው፤ባንክ ሄዳም መበደርና ትልልቅ ኃላፊነቶችን መውሰድ የጀመረችው። ለዚህ ደግሞ መንስኤው የሰውነት ግዝፈቷ እንደነበር አትረሳውም። በዚህም የአካባቢው ሰዎች ሳይቀሩ አላደገችም ብለው ስለማያምኑዋስ ጭምር ይሆኗት ነበር። ይህ ደግሞ የ15 ዓመት ልጅ ሆና 21 ዓመት እንደሞላት ተደርጎ የቤተሰቡን ክሊኒክ እስከመቆጣጠር አድርጓታል።
በጣም ተግባቢና ተጨዋች፤ ድሃ ሀብታም ሳትል ሁሉንም በእኩል መቅረብ የምትወደው ልጅ አዲስአለም፤ ቤተሰቦቿ ሀብታም ቢሆኑም ድሃ ሀብታም ሳትል ከማንኛውም ልጅ ጋር ትጫወታለች። አልፎተርፎም ቤቷ እየጋበዘቻቸው አብራቸው ትመገብና እቤታቸው መኖር የሚፈልጉ ከሆነ እንዲኖሩ ታስፈቅድላቸው ነበር። የሕክምና ወጪ ሳይቀር በቤተሰብ ስም እንዲያገኙ ራሷን ታማሚ በማድረግ እንዲሸፈንላቸውም ታደርጋለች። በዚህም የአካባቢው ልጆች ብቻ ሳይሆኑ አዋቂዎችም ያከብሯትና ይወዷት ነበር።
አዲስአለም ከጨዋታ ሁሉ በጣም የምትወደው ድብብቆሽ ሲሆን፤ ሩጫና ሌሎች ጨዋታዎችንም ትጫወታለች። ይሁንና የከተማ ልጅ በመሆኗ ቤተሰብ ከቤት እንድትወጣ አይፈቅድላትም። ብዙ ጊዜዋን ትምህርት ቤት እንድታሳልፍ እንጂ በጨዋታ ጊዜ እንድታጠፋም አይፈለግም። በዚህም ጨዋታ ብዙ እንዳልተጫወተች ትናገራለች።
ምግብ መስራትን ከእናቷ ገና በልጅነቷ የተማረችው አዲስአለም፤ ቤት ውስጥ እናት ምግብ ስታዘጋጅ እርሷም የተለያዩ ነገሮችን ትሰራ ነበር። በዚህም ደንበኛ ምግብ አብሳይ ሆናለች። በተመሳሳይ እንግዳችን የምትፈልገውን ነገር ካላገኘች የማታቆም ልጅና የፈጠራ ሥራ የምትወድም ነች። እንዲያውም አንድ ቀን ያደረገችውን መቼም አትረሳውም።
ሰፈራቸው በጭቃ የቦካና ቤት ለመግባት የሚያስቸግር በመሆኑ የሰፈር ልጆችን ሰብስባ በወቅቱ ታስቦ የማያውቀውን ኮብል ስቶን ሰራች። ለመንገዱ ምቹ የሚሆኑ ድንጋዮችን በተገቢው ቦታ በማስገባትም መንገዱን ሰርታለች።አዲስ አለም ሼፍ መሆን ህልሟነው። ነገር ግን በወቅቱ ይህ ሙያ አይታወቅምና ከቤት እንደማያልፍ አምና የቤተሰቦቿን ሀሳብ ደግፋ እንደአባቷ የሕክምና ዶክተር ለመሆን ጠንክራ መማር ጀመረች።
ከባህርዳር እስከ አሜሪካ የዘለቀው ትምህርት
የመጀመሪያ ፊደሏ ቤተሰቦቿ ሲሆኑ፤ በሚገባ ቀለም እንድትቆጥር አግዘዋታል። ከዚያ ለአካባቢው ቅርብ በሆነ ‹‹ሽንብጥ›› በተሰኘ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስገቧት። ከአንደኛ እስከስድተኛ ክፍል ድረስ ከተማረች በኋላ ደግሞ ወደ ‹‹ፋሲሎ›› የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛውራ ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን ተከታተለች። ቀጣዩን ክፍል ደግሞ በጣና ሀይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተለች ሲሆን፤ በእነዚህ ክፍሎች የደረጃ ተማሪ ነበረች። የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ግን ለፈለገችው የሕክምና ትምህርት መግባት አያስችላትም ነበር።
ሕክምናውን መማር ትታ ባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እንደገባች የምትናገረው አዲስአለም፤ከኮሌጁ በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ የትምህርት መስክ “በአድቫንስ” ዲፕሎማ ተመርቃለች። ከዚያ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በማይክሮሊንክ ኮሌጅ ሶፍትዌር ኢንጅነሪኒግ “አድቫንሲንግ” ዲፕሎማዋን ይዛለች።
የሕክምና ትምህርት መማር አላማዋ ቢሆንም ይህንን ዕድል ለማሳካት መንገዶቹ ቀና አልነበሩም። ይህንን ህልሟን ለማሳካት የሚያስችላትን ዕድል አገኘች፤በዲቪ አማካኝነት ወደ አሜሪካ አቅንታለች። በዚያም የሕክምና ትምህርት መግቢያ ኮርሶችን ለአራት ዓመታት ተከታትላ ሌላ የትምህርት ዕድል በማግኘቷ ወደ ምግብ ሥራ ትምህርት ገብታለች። ሆኖም ይህ የትምህርት ፍቅሯ በልቧ ውስጥ የተሳለ በመሆኑ አራት ዓመቱ እንዲያዝላት በማድረግ አፕላይድ ሳይንስ በዋናነት የሥነምግብ ጥናት እንድትማር ሆናለች።
‹‹አባቷ ማንም እንደ አገር አይሆንም። እናም አሜሪካ ስትገቢ ወረቀት እንጂ ብር ይዘሽ እንዳትመለሽ። ብሎ ቃል አስገብቶኛል›› የምትለው ባለታሪኳ፤ ይህንን ቃል ይዛ በመጓዟ ሁሌ የተሻለ የሙያ ትምህርት ይዛ ለመመለስ ትተጋ እንደነበር አጫውታናለች።
በአሜሪካ እንደደረሰች ቤተሰቦቿ ጋር ብታርፍም ከሁለት ዓመታት በላይ በከተማዋ መቆየት አልቻለችም። ምክንያቱም የአየሩ ሁኔታ በኒውዮርክ ለእርሷ ምቹ አልነበረም። ስለዚህም ቤተሰብን ትቶ በራስ እየሰሩ መማር ግዴታ ሆነባት። በዚህም ማቄን ጨርቄን ሳትል ጓዟን ጠቅልላ ወደ ሌላኛው የአሜሪካ “ስቴት” ላስቬጋስ አቀናች። ይህንን ጊዜም ነው የሕክምና ትምህርት ለመማር የሚያስችላትን የመግቢያ ኮርሶች የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነች ለአራት ዓመት የተከታተለችው።
በክሊነር አርት ወይም በምግብ ሥራ ትምህርት ከኮሌጅ ኦፍ ሳውዘርን ኒቫዳ ሰርተፍኬት ያገኘችው አዲስአለም፤ በዚሁ ኮሌጅ በዚሁ መስክ ዲግሪዋን ተምራለች። ከዚያም አልፋ በዘርፉ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመውሰድ በአሜሪካ አገር የመጨረሻ የሚባለውን የሼፍነት ደረጃን ለመያዝም በቅታለች።
የዓለምአቀፍ ሼፎች ማህበር አባል የሆነችው እንግዳችን፤ ሁለት ትምህርት ቤቶች ላይ በመመላለስ ትምህርቷን ተከታትላለች። በዚህም እረፍት አልባ እንደነበረች ትናገራለች። ምክንያቱም ከአንድ እስከ ዘጠኝ ሰዓት እና ከዘጠኝ ተኩል እስከ ምሽት አምስት ሰዓት ድረስ ሰባቱንም ቀናት በትምህርት ላይ ታሳልፋለች። ይህ ደግሞ በአንድ ጊዜ ሁለት ዲግሪን ይዛ እንድታጠናቅቅ አግዟታል።
አዲስዓለም በተመላላሽ ሠራተኛነት ጭምር በመስራት ነው የትምህርት ወጪዋን ስትሸፍን የነበረው። በተመሳሳይ ከ15 ሰዓት በላይ እየተማሩ መስራት ባይፈቀድም እርሷ ግን ውጤታማ በመሆኗ ይህንን ፈቃድ አግኝታ በምትማርባቸው ሁለት ትምህርት ቤቶች ቋሚ ቅጥረኛ ሆናም ትሰራለች። ሥራዎቿ አዲስ መጥ ተማሪዎችን ምክር መስጠት እና የምትይዛቸውን ማስታወሻዎች ለትምህርት ቤቱ በማስረከብ ደከም ያሉ ተማሪዎች እንዲማሩበት ማድረግ ነው። ምክንያቱም ከስምንት ዓመታት በላይ ከትምህርት ሳትለይ በማሳለፏ የቤት ወጪዋን የሚሸፍንላት አካል አልነበረም።
በትምህርት የቆየችበት ጊዜ 150ሺህ ዶላር የሚያስወጣ ሲሆን፤ 115 ሺህ ዶላሩን የሸፈነው የትምህርት ዕድሉን የሰጣት የአሜሪካ መንግሥት እንደሆነና የአሜሪካ መንግሥትን እንደምታመሰግነው ያጫወተችን አዲስዓለም፤ ከቤት ወጪ በተጨማሪ 35 ሺህ ዶላሩን ግን ራሷ ብድር ወስዳ እየሰራች በመክፈል ሸፍናለች። ይህ የሆነው ደግሞ ከሁለትና ሦስት ሰዓት በላይ ሳትተኛ ለትምህርቷ ዋጋ ከፍላ ነው። ለዚህም ማሳያው በሳምንት አንድ ቀን በምታገኘው ጊዜ ሦስት ቤተሰብ ቤት በመሄድ ከምሽቱ አምስት ሰዓት እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ምግብ ማብሰሏ ነው።
የሕክምና ትምህርትም ሆነ የምግብ ሥራ ትምህርት የሰው ሕይወት በእጅ እንዳለ የሚታሰብባቸው ሙያዎች እንደሆኑ የምታነሳው አዲስአለም፤ የትምህርት አሰጣጡም ሆነ የሰዓት አጠቃቀሙ እጅግ ጥንቃቄ የሞላበት እንደሆነ ትናገራለች። በዚህም ማርፈድ የሚቻለው ሦስት ደቂቃ ብቻ መሆኑን ታነሳለች። ከዚያ ካለፈ ግን 50 ማርክ ይቀነሳል። ይህ ደግሞ ውጤትን ያወርዳል ትላለች።
ማርኩን ለማካካስ ስምንት ሰዓት የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት ግዴታ እንደሆነ የምትናገረው እንግዳችን፤ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት ማንም የሌለው ሰው ይከብዳል። ስለሆነም አማራጭ የሚሆነው በሥራ መቀጣት ወይም ዕዳ መክፈል ወይም ውጤት ዝቅ ሲል ማየት ነው። እናም በዚህ ችግር ምክንያት አንድ ትምህርት ቢ ሆኖባት እስካሁን እንደምትቆጭበት አውግታናለች።
አሜሪካና አዲስ አበባን በሥራ
የሥራ ሀሁ የጀመረው በልጅነቷ ነው። የክሊኒክ ኃላፊ በመሆን። ከዚያ ባህር ማዶ ተሻገረና ለመማር ስትል ከትምህርት ቤቷ እስከ ሰው ቤት የደረሰ ሥራ መስራቱን ቀጠለች። በታዋቂው ላስቬጋስ ውስጥ በሚገኝ ‹‹ጎርደን ራምሴስቴክሀውስ›› የተባለ ሬስቶራንት ውስጥም አንቱታን ያተረፈላትን የምግብ ዝግጅት ለሁለት ዓመታት ከውናለች። ጎርደን ራምሴየሲኤንኤ ቴሌቪዥን ላይ ሁለት ዓይነት ሾው
የሚያዘጋጅ ሲሆን፤በወቅቱ እውቅናን እንድታገኝ አግዟት እንደነበር አትረሳውም።
‹‹ማንም እንደአገር አይሆንም። ብዙዎች በሥራዬ ይፈልጉኝ ነበር። ሆኖም የአባቴ ቃልኪዳን አለብኝና አሜሪካን ትቼ ወደ አገሬ ተመለስኩ›› የምትለው ባለታሪኳ፤ አገር ቤት ከገባች በኋላ በሕይወቷ የተማረችበትን ለማስተማር እንደተጋች ትናገራለች።
በአመጋገብ የተነሳ 124 ኪሎ ግራም መድረሷን፣ የጉበት ማበጥ፣ ከፍተኛ የልብ ችግር፣ ከፍተኛ የጨጓራ አሲድ መርጨት፣ አስም ህመምተኛ መሆኗንና ወንድም፣ እናቷን እንዲሁም አባቷን ማጣቷን አብነት በማድረግ ‹‹ጉዳት በእኔ ይብቃ›› በማለት ወደ ቴሌቪዥን ሾው ዝግጅት እንደገባች አጫውታናለች።
በሙያዋ ከካንሰር፣ከልብ፣ ከሜቆዶንያ እና ከስኳር ማህበራት ጋር በጥምረት ትሰራለች። የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቶች ላይም ታማክራለች። በተመሳሳይ በዋልታ ቴሌቪዥን ‹‹አዲስ ጣዕም›› የሚል ሾው አዘጋጅና ዳይሬክተርም ነች። የእርግዝና አንድ ሺህ ቀናትን የሚያሳይ የአመጋገብ ሥርዓት ‹‹ወርቃማ ሰንሰለት›› በሚል ጽፋ በጤና ጥበቃ አማካኝነት ሙያዊ ግምገማ ተደርጎ በማለቁ በቅርቡ ታትሞ ለማስተማሪያነት ይውላል።
የ21 አገራት ሙሉ ምግቦችን እንደምትሰራ የምትገልጸው አዲስ አለም፤ በምንም ተአምር የእኛን አገር የሚያክል በተፈጥሮ የተቀመመ ምግብ እንደሌለ ትናገራለች። ሆኖም ድሃ የሚባለው ካልሆነ በቀር አይጠቀመውምና ጥቅምነቱ አልተለየም። በአገሪቱ የሀብት ደረጃ የሚለካው በታሸጉ ምግቦችና ኬሚካል በበዛባቸው ቅመሞች መመገብ ነው። ይህ ደግሞ በሽተኛው እንዲበራከት አድርጓል ትላለች።
‹‹እድገታችን እኛነታችንን አስረስቶታል›› የምትለው እንግዳችን፤ ጤናማ ያልሆኑ ትውልዶች እንዲፈጠሩ የሆነው ጤናማውን የተፈጥሮ ምግብ በመተው ወደ ዘመን አመጣሹ በማዘንበላችን ነው። እናም ይህ ትውልድ ከእኔ ተምሮ ሕይወቱን እንዲያድን በመፈለጌ ወደ አገሬ ተመልሼ በዘርፉ እንድሰራ ሆኛለሁ ብላናለች።
የዕድሜ ልክ መድኃኒት የሚወስድ አካል ሁነኛ መተማመኛው ምግብ ብቻ ነውና ይህንን አውቆ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግም የምትሰራው አዲስዓለም፤መድኃኒት ፈውስ የመስጠቱን ያህል የጎንዮሽ ጉዳትም አለው። ስለሆነም ምግብን መድኃኒት አድርጎ እንዲመገብ ለማስቻል እንደምትሰራ ትናገራለች። ሰው ሁሉ ‹‹ምግብን መድኃኒት አድርገው ካልበሉ መድኃኒትን ምግብ አድርገው መብላት ይጀምራሉና ይጠንቀቁ›› ምክሯ ነው።
ሁለተኛ አዲስ የቴሌቪዥን ሾው ይዛ እንደቀረበችና ሥራውም በወራት ውስጥ እንደሚጀመር የምትገልጸው እንግዳችን፤ ፕሮግራሙ የእናቶችንና ሕፃናትን የአመጋገብ ሥርዓት በአግባቡ የሚያስቃኝነው ብላለች።
‹‹አሜሪካ የመጨረሻው የምግብ ደረጃ ሰለብሬቲ ሼፍ በመሆን ሰርቻለሁ። ጥሩ የትምህርት ደረጃና አቅም አለኝ። የሥራ ዕድሌም ሰፊ ነበር። ግን አገርና ሕዝብን ለማዳን ወደዚህ መጥቻለሁ›› የምትለው ባለታሪኳ፤ ሕይወት ለገንዘብ ብቻ ተብሎ የሚኖርበት አይደለም። የህሊና እርካታንም ይጠይቃል። ስለሆነም ከገንዘብ ይልቅ ህሊናን መርጬም ነው እዚህ የምሰራው ትላለች።
አዲስዓለም ዛሬም የምግብን ጥቅም ለመንገር የራሷን ድርጅት ‹‹ፊውዥን የኒውትሬሽን ሆቴልና ቱሪዝም ማማከር አገልግሎት›› በማለት ከፍታ እየሰራች ትገኛለች።
ምግብ ያስተምራል
ከቤተሰብ ጋር በምትኖርበት ጊዜ ብዙ ነገሮች በድሎት የተበሉና ለጤና ጥቅም የሚሰጡ ይመስላት ነበር። ለአብነት ሥጋ፣ቅቤ፣ ማርና እንቁላል የጎንዮሽ ጉዳት እንዳላቸው አንድም ቀን አስባ አታውቅም። እንዲሁም በተቃራኒው ጤናማ የሆነው እኛ ብቻነን ትል እንደነበር ታስታውሳለች። ምክንያቱም በቤታቸው ሁሉ ነገር ሙሉ ነው።
ዛሬ ግን ያ ሁሉ ነገር የቤተሰቦቿን ሕይወት ቀጣፊ እንደነበር ተገነዘበች። አመጋገባቸውም ችግር እንዳለበት ተረዳች። በዚህም በድህነት የሚበላ ምግብ ጤናማነቱ የተረጋገጠ እንደሆነ ለሁሉም መምከር ጀመረች። ምንም ዓይነት ከተፈጥሮ የራቀ ነገር የማይካተትበት ምግብ ለጤና ተስማሚ መሆኑን ማሳወቁን አጠናክራ ቀጠለችበት።
‹‹በሕይወት መማር ለሚፈልግ ደብተሩ እኔ ነኝ›› የምትለው አዲስዓለም፤ እንደቀደምት አያቶቻችን በቤት ውስጥ ያልተዘጋጀ ምግብን መመገባችን በሽታን በምግብ መመከት እንዳንችል ሆነናል። ለዚህም ማሳያው እኔ እግሬሰውነቴን መሸከም አቅቶት ስድስት ወር ሙሉ ማንም በሌለበት ቤት ውስጥ እንድትቀመጥ የሆንኩት ነው። ስለዚህም ዳግመኛ የእኔ እጣ እንዳይገጥማችሁ በሕይወታችሁ ከመማር ቀለሙን ከእኔ ቅሰሙ ትላለች።
አዲስ አለም፤ ‹‹እናቴ እና አባቴን በልብ ህመም፤ ወንድሜን ደግሞ በኩላሊት ችግር አጥቻለሁ። ይህ ሁሉ የመጣው ደግሞ አመጋገብን ባለማስተካከል ነው። እኔም ብሆን በነበሩኝ በሽታ ተንገላትቻለሁ። እናም ቶሎ በመንቃቴና በመማሬ ራሴን በምግብ ማከም ችያለሁና እናንተም በሕይወት ሳይሆን በልምድ ከስህተታችሁ ተመለሱ›› ብላለች።
ኑሮ በአሜሪካ
በአሜሪካ ስትኖር ትዳሯን፣ ቤተሰቧን አጥታ ኀዘንና ችግሯን ተጋፍጣ ነው ያሳለፈችው። ምክንያቱም አላማ ነበራትና ነው። ለራሷ የምትተርፍበትን መንገድ መቀየስም ግዴታዋ ነው። እናም ወገቧን ታጥቃ ተምራ የትልቅ ሙያ ባለቤት ሆናለች። በምኖርበት ከተማ 35 ሺህ ኢትዮጵያውያን ቢኖሩም ለምርቃት የበቃ ሰባት ብቻ ነበር። እርሷ ደግሞ አንዷ ለመሆን የቻለችው ችግርን በመጋፈጧ እንደሆነ ትናገራለች።
እንግዳችን፤በሰው አገር የሚተረፈው ትምህርት ብቻ ነው። ገንዘብ አካብቶ ቢመጣ አሁን ባለው ኑሮ ውድነት ከቤተሰብ ያለፈ ሥራ ለመስራት ያስቸግራል። ስለሆነም ሁሌ መታሰብ ያለበት ነገ ሕይወት ለሚሆን ነገር ነው ትላለች።አሜሪካ እንዲህ በኢትዮጵያኑ የሚወራላት ገነት ዓይነት አይደለችም። በብዙ ትግል ውስጥ አልፎ ማሸነፍን ትጠይቃለች። በተለይም ራስን በራስ ለሚያስተዳድር ሰው እጅግ ፈታኝ ናት። ሆኖም ለተማረና በሙያው ለሚሰራ ሰው የሥራ አማራጯ ብዙ ነው። ፈተናን ተቋቁሞ ለሚማርም ሰው ብዙ ዕድሎችን ትሰጣለች።
‹‹ራሴን በተሳለልኝ መልካምነቷ ስዬ ነበር ወደ አሜሪካ የተጓዝኩት›› የምትለው አዲስአለም፤ በፈተና ውስጥ አልፋ እንደተማረች ትናገራለች። ሰዎች ያለሙት ነገር ላይ ለመድረስ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ከከፈሉ የሚከብዳቸው ነገር እንደሌለም ታስረዳለች።
በትምህርት ላይ እያለች በየሁለት ዓመቱ ከቤተሰቤ አንድ ሰው ይሞትባት እንደነበር ያጫወተችን አዲስአለም፤የሁሉም ኀዘን ውስጧ ዘልቆ ቢያስጨንቃትም ችግሯን ዋጥ አድርጋ ትምህርቷ ላይ ትኩረት እንዳደረገች ትናገራለች። ሰው ጠዋት ኀዘኗን አርድቷት ወዲያው ለፈተና ትሄድ እንደነበርም አትረሳውም። በተለይ ደግሞ በባህላችን መሠረት ለቅሶ ደራሽ አለና ለመድረስ የሚመጣውን እንኳን ማስተናገድ እንዳልቻለች ስታስብ ውስጧ በጣም ይታመም እንደነበር ታወሳለች።
አሜሪካ ስኖር አንድም ቀን ማህበራዊ ሕይወት ኖሯት እንደማያውቅ የምትናገረው እንግዳችን፤ እናትና አባቷ እንኳን ሞተው ‹‹ይቅርታ ፈተና ሄጃለሁ እንደደረሳችሁኝ አስባለሁ›› በማለት በር ላይ ጽፋ በመለጠፍ እንደምታልፈው ትገልጻለች። ይህ ደግሞ ኀዘኔን በደንብ ረስቼ ሙሉ ሀሳቤን በትምህርቴ ላይ እንዳላደርግም ገድቦኛል ትላለች።
በአሜሪካ ብዙዎች ትምህርት ይጀምራሉ ግን አያጠናቅቁም። ለዚህ ምክንያቱ የተማሩት ትምህርትና የሥራ ዕድሉ አለመገናኘት ነው። ከዚያም አልፎ ራሳቸውን ለማስተዳደር ያቅታቸዋል። እናም ምርጫቸው ዝቅ ያለሥራ ላይ ተሰማርቶ ገንዘብ ማግኘት እንደሆነ ያጫወተችን ባለታሪኳ፤ እርሷ ከዚህ የተለየ ዕድልን መምረጧ፤ችግርና ኀዘን መቋቋሟ በትምህርቷ የሚገባትን እንድታገኝ እንዳደረጋት ትናገራለች።
በአሜሪካ ራስን ለማኖር ሲባል በጣም የሚጠጡ መራራጽዋዎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ግን በጣሙን ዛሬ ድረስ የማትረሳው እናቷን፤ አባቷንና ወንድሟን በሕይወት ስታጣቸው ጠዋት ተረድታ ከሰዓት ፈተና የገባችበትን ነው። በተጨማሪ ፈተናውን ማቋረጥ አለመቻሏ አሳዝኗት ነበር። ምክንያቱም ዓመቱን ታቋርጣለች። ይህ ከሆነ ደግሞ የዓመት የትምህርት ወጪውን መክፈል አለባት ። ስለዚህም እያለቀሰች እንድትፈተን ሆናለች።
በአሜሪካ ማንም የሌለው ሰው ቀን፣ ሌሊት፣በዓል፣ ትምህርት ተዘጋ ብሎ ሥራ ሳይሰራ ቁጭ ማለት አይቻልም። እንዲያውም ሙሉ ሰዓት የመስሪያ ጊዜ ተገኘ ነው የሚያስብለው። እናም እርሷም በእነዚህ ቀናት የባልትና ውጤቶችን በማዘጋጀት ለሱቆች ታስረክባለች።
ሽልማት
ሳይኮሎጂ ኮርስ በወሰደችበት ጊዜ ነው አዕምሮዋ ላይ ጥቁር ጠባሳ የተጣለው። እናም ይህንን ለማጥፋት ስትል በሰራችው ሥራ ሽልማቱ ተበርክቶላታል። ነገሩ እንዲህ ነው።
መማሪያ መጽሐፉ ላይ አንድ ምዕራፍ ተሰጥቶት ኢትዮጵያና አሜሪካ ያለን የኑሮ ሁኔታ ያወዳድራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የገጠር ነዋሪ የመሰለ ሰው ትንሽ ሬዲዮ ይዞ ባትሪው ሲያልቅበት ይታያል። አሜሪካ ውስጥ ደግሞ በአፓርትመንት ውስጥ ተቀምጦ በፍላት ስክሪን የፈለገውን እየቀያየረ የሚመለከት በብርሃን የተሞላ ሰው ተቀምጧል። በዚህም ተማሪውም ሆነ መምህሩ ኢትዮጵያን የድህነት ተምሳሌት አሜሪካን ደግሞ የሀብት ተምሳሌት አድርገው ይስላሉ። ይህ ደግሞ ብቸኛ ሐበሻ ተማሪ ለሆነችው አዲስዓለም የራስ ምታት ሆነባት።
‹‹በእነርሱ አገር ድሃ የሚባል እንደሌለ አድርገው ነበር የሚያስተምሩት። እናም ይህ ህመም ተመርቀን ሳንወጣ ሊጠፋ ይገባል ብዬ ወደስራ ገባሁ›› የምትለው እንግዳችን፤መጽሐፉን ለመክሰስ አስባ እንደነበር ሆኖም አቅሟ ስለማይፈቅድ እንደተወችው ትናገራለች። በቀሏን በአደባባይ ለመመለስም ዓለምአቀፋዊ የባህል ሾው ላይ ተሳተፈች።
ፕሮግራሙ የዓለምአቀፍ ተማሪዎች ቀን ሲሆን፤ የአገራቸውን ማንነት በሚገባ ለተለያዩ ዓለማት የሚያሳውቁበት መድረክ ነው። እናም ከዚህ ሁሉ በማስላክ ሙሉ ማንነቷን በሚባል ደረጃ ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ጭምርም አሳየች።
ከቀረቡት ሾዎች ውስጥ የእርሷ ሾው አሸንፎ አንደኛ በመውጣት ሽልማትን እንድትቀዳጅ የሆነችው አዲስዓለም፤ ይህ ሥራዋ ለሌላ ተግባርም እንድትታጭ ያደረጋት ሲሆን፤ ዛሬ ድረስ በየዓመቱ ‹‹የናቹራል ሙዚዬም ላስቬጋስ›› የሚባል ሾው ተሳታፊ እንድትሆንም ዕድል አመቻችቶላታል። የተሻለ አቀራረብ ነበራትና የሾው አዘጋጆች አንድ ቋሚ ቦታም እንዲሰጣት አድርገዋል። እናም ዛሬ ድረስ በዚያ ናሽናል ሙዚዬም የሄደሰው ይህንን ሥራዋን እንዲያይ ይሆናል።
መልዕክት
‹‹እድገታችን ባህላችንን የጠበቀ ባለመሆኑ እንደሌሎች አገሮች በባህል ማደግ አልቻልንም። በዚህም ለተለያዩ በሽታዎች እንድንጋለጥ ሆነናል›› የምትለው አዲስዓለም፤የሰው ልጅ አመጋገቡ ጤናማ ከሆነ ሀኪም ሳያየው መኖር ይችላል። እኛ የምንበላው ምግብ ውጤት ነንና ጤናችንን ለመጠበቅ አመጋገባችንን መድኃኒት እናድርገው መልዕክቷ ነው።
‹‹ቤተሰብ ጤነኛ እንደሆንኩ ይጠራጠራሉ። ትክክለኛ ሥራ እየሰራሁ እንደሆነም አያምንም። ምክንያቱም ብዙ የሥራ ዕድል በአሜሪካ እያለኝ ወደ አገሬ በመምጣት እየሰራሁ አይመስላቸውም። በአገር ደረጃ ከፍተኛ ክፍያ የሚያገኙት ሼፎች ሆነው ሳሉ እኔ በራሴ እየሰራሁ መሆኑና ገንዘብ አለማግኘቴ አላሳመናቸውም። እናም በጣም ይናደዱብኛል›› የምትለው አዲስዓለም፤ሰው የሚሰራው በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በህሊና ነው። የሰዎች መለወጥ በህሊና ሲሆን ደግሞ ተሰብስቦ ክፍያ ይሆናል። እናም ይህንን እያደረግሁ በመሆኔ እግዚአብሔርን በጣም አመሰግነዋለሁ ትላለች።
የአገር ውስጥ የሙያ ፈቃድ በማውጣት እየሰራች የምትገኘው ባለታሪኳ፤ መንግሥት ቢያግዘኝ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላላቸውና ለጎዳና ልጆች የሚደርስ በትንሽ ዋጋ ብዙ ሰው የሚጠቀምበት ጤናማ ምግብ በመሀል ከተማዎች ላይ ብታዘጋጅ ደስታዋ እንደሆነም ገልጻለች። እኛም ፍላጎቷ እንዲሳካ ተመኘን ። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር 3/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው