የደራ ንግድ ከሚካሄድባቸው የአዲስ አበባ ሰፈሮች መካከል ቺቺንያ አንዷ ናት። የዛችን መንደር መታወቂያ አብዛኛው ከጫት፣ ከመጠጥና ከሺሻ ጋር የተያያዘ ነው። እነዚህ ንግዶች የሚካሄዱት ከፊሎቹ ከመንግሥት ህጋዊ ንግድ ፈቃድ ወጥቶባቸው ሲሆን፤ ከአብዛኞቹ በስተጀርባ ድብቅ ማስቃሚያ፣ ሺሻ ማስጨሻና ሌሎች ተግባራት የሚከናወኑባቸው ቤቶች ናቸው። በመንገድ ዳር የጀበና ቡና የሚያፈሉት ሳይቀሩ «መቀመጫ» ቦታ አመላካች ናቸው።
በየደረጃው ያሉትን የጫት ማስቃሚያና የሺሻ ማስጨሻ ቤቶችን ከነዋጋቸው ይጠቁማሉ። እነሱም ቡና በማቅረብ የጉዳዩ አካል በመሆን ተባባሪ ሆነው ይታያሉ። የአካባቢው ነዋሪዎችም በሚያዩት ድርጊት የነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ
በሱስ እየደነዘዘና ከመስመር እየወጣ መሆኑ ቢገባቸውም አይቶ እንዳለየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ አብሮ መኖርን ቀጥለዋል። ዜጎችን የመቅረፅ ትልቅ ኃላፊነት የተጣለባቸው ትምህርት ቤቶች ግን ችግሩ እንዳሳሰባቸው ይናገራሉ።
የካፑቹን ደናግል ሲስተሮች ማህበር የማሪያ ሩባቶ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህርት ሲስተር ጃለሌ ማሞ እንደሚናገሩት አካባቢው እንደ ሲጋራ፣ ጫትና መጠጥ የመሳሰሉት ለሱስ የሚዳርጉ ሸቀጦች በስፋት የሚቸበቸቡበት ነው። እነዚህም በቀላሉ በተማሪዎቹ የሚታዩና ተማሪዎቹ እንዲሞክሯቸው የሚገፋፉም ናቸው። በአሁኑ ወቅት ከትምህርት ቤቱ ፊት ለፊት አስር ሜትር በማይሞላ ርቀት በርከት ያሉ ጭፈራ ቤቶችና ጫት ቤቶች አሉ። ከዚህ ቀደም ከጭፈራ ቤቶች መካከል ታሽገው የነበሩ ቢሆንም ከሁለት ቀን በኋላ ተከፍተው ወደተለመደው ሥራቸው ገብተዋል። ይሄንን ለማስቆም ከወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት እስከ ክፍለ ከተማ ድረስ ብዙ ተሞክሯል ፤ ወላጆችም ከአካባቢው እንዲነሳ ፊርማ አሰባስበው ጠይቀዋል፤ ሆኖም እስካሁን ጠብ የሚል ውሳኔ አልተገኘም። ተማሪዎች ሲለቀቁና በተለይ ዝናብ ሲጥል ገብተው እንዲቀመጡ የሚጋብዙም እንዳሉ ይናገራሉ። ይሄንን እያያ የሚያድግ ተማሪ ቀጣዩ ዕድሉ ምን ሊሆን ይችላል? ሲሉ ይጠይቃሉ።
«አንዳንዶቹ ቤቶች በራቸው ላይ ቡና ይባል እንጂ ውስጣቸው መጠጥና ሌሎች ነገሮች የሚቀርቡባቸው ናቸው። ውስጥ ለውስጥም በራቸውን ዘግተው ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ አሉ። ከዚህ ቀደም አንዲት ተማሪ ወደእነዚህ ቤቶች ስትገባ ወላጆች አይተው ለትምህርት ቤቱ ጥቆማ ሰጥተዋል። ወላጆችም በአካል ሄደው ለሚመለከተው አካል ጠቁመዋል፤ እኛም ስንንቀሳቀስ የምናያቸው ነገሮች አሉ። ከሚመለከታቸው አካላት አመርቂ ምላሽ ስላላገኘን ተማሪዎች የችግሩ ሰለባ እንዳይሆኑ የተጠናከረ የምክርና ከትምህርት ቤት ሲወጡም ክትትል እያደረግን እንገኛለን»
በተመሳሳይ የዶክተር ሐዲስ አለማየሁ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አለማየሁ ገሰሰ እንደሚሉት በአካባቢው ህጋዊ ፈቃድ ያላቸው ጫት፣ ሺሻና መጠጥ ቤቶች በስፋት አሉ። የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችም ለዚህ በስፋት የተጋለጡ ናቸው። በጉዳዩም ከወላጅ፣ ከወረዳው ምክር ቤትና ትምህርት ጽህፈት ቤት ጋር በስፋት ስንወያይበት ቆይተናል። በእያንዳንዱ ሱቅ ፊት ለፊት ፈቃድ አውጥተው ከሚሠሩት ውጪ በየመንደሩ በድብቅ የሚሠሩትን ማስቃሚያ፣ ማስጨሻና መጠጥ ቤቶች ለመቆጣጠር ከፖሊስ፣ ከደንብ ማስከበርና ንግድ ቢሮ ጋርም ክፍለ ከተማ ድረስ በተደጋጋሚ ተወያይተንበታል። ዘንድሮም ጥቅምት አራትና ታህሳስ ሃያ አንድ የወላጆች ጉባኤ ሲካሄድ ወላጆች ስጋታቸውን መናገራቸውን ይገልጻሉ።
ከዓመት በፊት በአጥር አልፎ ትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚገባ መጠጥ፣ ጫትና ሲጋራ ነበር። በዚህ ጉዳይ የተያዙ ተማሪዎችን አባረናል። ከወላጆች ጋር በተደረገውም ስምምነት በመሰል ተግባር በአጥር ሲቀባበል የተያዘ ተማሪ እንዲባረርም ከስምምነት በመድረስ በአካባቢው ያለው ነዋሪ ማንኛውም ተማሪ መጠጥ ቤት፣ ጫት ቤትና ጥርጣሪ ያለባቸው ግቢዎች ሲገባ እንዲጠቁሙ መደረጉንና አንዳንዶችም አስተያየት የሚሰጡ መኖራቸውን ይገልፃሉ ።
በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ አራት የመምህራንና ትምህርት አመራር ልማት ቡድን መሪ አቶ ደሴ ተሻለ የጉዳዩን አሳሳቢነት ይናገራሉ። በወረዳው አዋኪ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተብለው ከተለዩት ስድስት ጉዳዮች መካከል አንዱ ይሄው የተማሪዎች ለሱስ ተጋላጭነት መሆኑን ይጠቅሳሉ። እንደ አቶ ደሴ ማብራሪያ በአካባቢው ካሉ ትምህርት ቤቶች በተለይ ማሪያ ሩባቶ የሚባለው ከፊት ለፊቱ ካለው በርካታ መጠጥ ቤቶች የሚርቀው በመንገድ ብቻ በመሆኑ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል።
አቶ ደሴ እንደሚሉት የትምህርት ቤቶችን አካባቢ ለመቆጣጠር የወጣ መመሪያ አለ፤ በዚያ መሰረት የንግድ ቤቶች ከትምህርት ተቋማት ቢያንስ 50 ሜትር ርቀት ውስጥ መገኘት አልነበረባቸውም። ሆኖም ንግድ ቤቶቹ በወረዳ ሦስት ስር ያሉ በመሆናቸው በቀጥታ ማነጋገር ስላልተቻለ ለወረዳው ትምህርትና ንግድ ጽህፈት ቤት ደብዳቤ ተጽፏል። ከነጋዴዎቹና ከትምህርት ቤቱ ኃላፊዎችም ጋር በአካልም በመገናኘት ውይይት ተደርጓል። በዚህም ለጊዜው ቡና ቤቶቹ በር ላይ የነበሩትን የጀበና ቡናዎች እንዲነሱ ተደርጓል፤ በቅርብ ከነበሩት ሁለት ጫት ቤቶች አንደኛውን ለመዝጋትም ተችሏል። የሌሎቹ ጉዳይ ግን ገና በሂደት ላይ ነው።ንግድ ቤቶችን ለማዘጋት የክፍለ ከተማ ድጋፍ የሚያስፈልገን በመሆኑ ለእነሱ ማሳወቃቸውን ይገልጻሉ ።
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል በትምህርት ተቋማት የሥነዜጋና ሥነምግባር ግንባታና ዴሞክራሲያዊነት፣ ተግዳሮቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች በሚል ግንቦት 2009 ዓ.ም ባካሄደው ጥናት ላይ የተመለከተውም የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ኃላፊነት የተጣለባቸው ቢሆንም ይህንን ኃላፊነት በበቂ ሁኔታ እንዳይወጡ የሚያደርጉና ከትምህርት ተቋማቱ ዙሪያ የሚገኙ ውጫዊ ከባቢያዊ ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቅሷል። ከዚህም መካከል የጫት መቃሚያና መሸጫ፣ የአልኮል መጠጥ ቤቶችና ማከፋፈያዎች፣ የሀሺሽና ሺሻ ማጨሻ ቤቶች፣ ጭፈራ ቤቶች፣ ቁማር ቤቶች (የካርታ ጨዋታ፣ ፑልና ከረንቡላ) እና የቪዲዮ ወይም ፊልም ቤቶች ተማሪዎች ዓላማቸውን እንዲስቱና የትምህርት ተቋማትም የመማር ማስተማሩን ሥራ በአግባቡ እንዳይወጡ ከሚያደርጉ መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ