አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ አገልግሎት ረጅም ጊዜ የሚወስድ፣ ውስብስብ፣ ግልፅነት የጎደለውና ለሙስናና ብልሹ አሰራር የተጋለጠ ሆኖ የቆየ ሲሆን በዚህም አጠቃላይ ሂደቱ ረጅም ጊዜ የሚወስድ፣ እንደደሀገርም የገበያ ተወዳዳሪነትን ገድቦት እንደቆየ ይነገራል፡፡
ይህ ስርዐት ዘርፉን ወደኋላ ከማስቀረቱም በተጨማሪ በገቢና ወጪ ንግድ የተሰማሩ ባለሀብቶች ጉዳዮቻቸውን ለማስፈፀም የፈፃሚውን አካል በተደጋጋሚ ደጅ ሲጠኑ አለፍ ሲልም እጅ መንሻ ካልያዙ ጉዳያቸውን ማስፈፀም የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰው ሲማረሩ ማየትም መስማትም የተለመደ ነው፡፡
ስርዐቱ ለበርካታ አመታት የገቢና ወጪ ንግዱ ጉዞ የኋሊት እየሄደ መድረስ ያለበት የዘመነ አሰራር ላይ እንዳይደርስ ፣ ባለሀብቱ በአገልግሎት አሰጣጥ እንዲማረር ሲያደርግና መንግስትም ማግኘት ያለበትን ጥቅም እንዳያገኝ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡
ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት በአለምአቀፍ ንግዱ ላይ በተለያየ መንገድ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላትን የመረጃ ልውውጥ ለማሳደግና አሰራራቸውን ለማዘመን የሚያስችል የኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎት ሥርዓትን ለተገልጋዮች የሚያቀርብበትን ስርዐት ዘርግቶ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል፡፡
የኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎት ሥርዓት በአለምአቀፍ ንግድ ተሳታፊ የሆኑ የንግድ፣ ትራንስፖርትና ልዩ ልዩ ተቆጣጣሪ ተቋማት በገቢ፣ ወጪና ተላላፊ እቃዎች የሚጠይቁትን መረጃና ሰነዶች በኤሌክትሮኒክስ ስርዐት በታገዘ አንድ የኤሌክትሮኒክስ ማዕከል የሚያቀርቡበት ሥርዓት ነው፡፡
ስርዐቱ በአለምአቀፍ ንግድ አሰራር ሚና እና ድርሻ ያላቸውን 40 ያህል ተቋማትና የስራ ሂደቶች በማስተሳሰር አለምአቀፋዊ የንግድ አሰራርን ማዘመንና ማቅለልን ዋና አላማው አድርጎ እየተከናወነ ሲሆን ይህም ተደጋጋሚ ሂደቶችን በማስቀረትና ውሳኔ የሚሰጥበት አንድ ማዕከል ብቻ በማመቻቸት ለተጠቃሚዎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስችላል፡፡
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎት ሥርዓትን ከትናንት በስቲያ የክልል ፕሬዚዳንቶች፣ ሚኒስትሮች፣ የልዩ ልዩ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች፣ ባለሀብቶች፣ የተወካዮች ም/ቤት አባላት፣ የልማት አጋሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት መርቀው ስራ ያስጀመሩ ሲሆን ለፕሮግራሙ አጠቃላይ ሂደት ጉልህ ድርሻ ላበረከቱ ባለድርሻዎችና አጋር አካላት በእለቱ እውቅናና ሽልማት አበርክተዋል፡፡
ፕሮግራሙ ተመርቆ በይፋ ስራ በጀመረበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፤ የኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎት ሥርዓት በዓለም አቀፍ ንግድ አገልግሎት ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ፕሮጀክት ሲሆን በዘርፉ ተሳታፊ የሆኑ ተቋማትን የአሠራር ሂደቶች በማቃለልና በማቀናጀት በአንድ የኤሌክትሮኒክስ ማዕቀፍ ለተገግልጋዮች የሚያቀርብ ሥርዓት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሯ በንግግራቸው ሥርዓቱ በመረጃና ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የአካል ምልልስንና የወረቀት ሥራን በከፍተኛ መጠን መቀነስና ማስቀረት የሚችል ሲሆን ይህም አጠቃላይ የጉምሩክ ስርዐቱን እጅግ የዘመነ የሚያደርግና ለተገልጋዮችም ቀላል፣ ቀልጣፋ፣ የሚተነበይና ግልፅ የሆነ አገልግሎት ማቅረብ የሚስችል ስርዐት ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ለማስፈፀም በአማካይ እስከ 44 ቀን ጊዜ እየወሰደ ያለውን የስራ ሂደት በመጀመሪያው ምዕራፍ ወደ 15 ቀን፣ በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ሥርዓቱ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ ወደ 3 ቀናት ዝቅ እንደሚያደርገው የተናገሩት ወ/ሮ አዳነች፤ በሙስና ምክንያት በየአመቱ እየባከነ ያለውን ከፍተኛ ገንዘብ ማስቀረት የሚያስችል እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
የፕሮግራሙ የሶፍትዌር ልማት ሥራ በደቡብ ኮሪያ ተቋም እየተከናወነ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ውጤታማነቱ በሙከራ ትግበራ የተረጋገጠ በመሆኑ ለሙሉ ትግበራ ዝግጁ በሆነ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን መንግስት ለዚህ ስራ 32 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በመመደብ ለተግባራዊነቱ የራሱን ድርሻ መወጣቱ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው ስርአቱ በዘርፉ የሚስተዋለውን ውስብስብ እና ለሌብነት የተጋለጠ አሰራር ከማስቀረቱም በላይ አለም እየተከተለ ያለውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የገቢና ወጪ ንግድ ስርዐት በመቀላቀል ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
መንግስት የሚሰጠውን የተቀላጠፈ አገልግሎት ባለሀብቱ በመጠቀም የጎደለውን ደግሞ እንዲሞላ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነጋዴዎች ወደዚህ ቀልጣፋ ስርአት እንዲገቡ መስራት እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እውቅናና ሽልማት ያገኙ ተቋማት፣ አጋር ድርጅቶችና ፈጻሚዎችም በዚህ መነሳሳት ለቀጣይ ስራ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁና ለተገልጋዮች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሰጡ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
ባሳለፍነው ታህሳስ 23/2012 ዓ.ም 16 የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ26/2012
በድልነሳ ምንውየለት