አዲስ አበባ፡– ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከህዳር ወር 2011ዓ.ም ጀምሮ ሲሰጥ በቆየው ሀገር አቀፍ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት እድሜያቸው 14 ዓመት ለሆናቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ታዳጊዎች ተደራሽ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የክትባት መርሃ ግብር ባለሙያ አቶ ጌትነት ባይህ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለጹት በህዳር ወር 2011ዓ.ም በተጀመረው ሀገር አቀፍ የመከላከያ ክትባት ዘመቻ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተከናወነ ሲሆን፣ ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑትን ደግሞ ከሶማሌ ክልል በስተቀር በአካባቢያቸው በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ክትባት ተሰጥቷል፡፡ የክትባት መርሃ ግብሩም በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነና በሶማሌ ክልልም ክትባቱ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ክትባቱ ከመጀመሩ በፊት መካንነትን እንደሚያስከትልና የወሊድ መከላከያ እንደሆነ በህብረተሰቡ ይነገር የነበረውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቀየር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቀድሞ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የቅስቀሳ ሥራ ማከናወኑን የጠቆሙት አቶ ጌትነት፤ ቅስቀሳው አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ታዳጊዎችን ለመከተብ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ያገዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ጌትነት ገለጻ፣ እስካሁን በተሰጠው ክትባት ለጉዳት የተዳረገ እንደሌለ፤ መጠነኛ ጊዜያዊ ራስ የመሳት ሁኔታ ቢከሰት የመድኃኒቱ ባህርይ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
አሁን ክትባቱን የወሰዱት ከስድስት ወር በኋላም በድጋሚ ይከተባሉ፡፡ በሽታውን መከላከል የሚቻለው ሁለቴ ከተከተቡ በኋላ ነው፡፡ መርሃ ግብሩ ከስድስት ወር በኋላ በተመሳሳይ ስለሚከናወን ታዳጊዎቹ መዘንጋት የለባቸውም፡፡በ2011ዓ.ም በሀገሪቷ የተጀመረው የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ መከላከያ ክትባት መደበኛ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በሽታን ቀድሞ መከላከል እንዲቻልና በሽታው ከተከሰተ በኋላም ዓለም ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበትን የህክምና ዘዴ ለመጠቀም እንደ ታይላንድ ተሞከሮ ካላቸው ሀገሮች ባለሙያዎችን በመጋበዝ ለሀኪሞች ሥልጠና በመስጠት የበኩሉን ሚና በመወጣት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር የአባላት ዘርፍና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ዳንኤል ተስፋይ አስታውቋል፡፡
አቶ ዳንኤል በተለይም በመከላከሉ ላይ ትኩረት ቢደረግ የታማሚዎችን ቁጥር ከመቀነስ በተጨማሪ በሽታው ካጋጠመ በኃላ የሚወጣውን ገንዘብና ድካም ለመቀነስ በእጅጉ እንደሚያግዝ አመልክተዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በዓለም ላይ በገዳይነታቸው ከሚታወቁት የካንሰር አይነቶች የሴቶችን የመራቢያ ክፍል የሚያጠቃው የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ አንዱ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም በሁለተኛ ደረጃ ጉዳት እያስከተለ ነው፡፡
በየዓመቱ 4ሺ600ሴቶች በማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ እንደሚያዙና ከነዚህ ውስጥም 3ሺ200ዎቹ ህክምና ሳያገኙ እንደሚሞቱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
ለምለም መንግሥቱ