አዲስ አበባ፣ 4ኛውን ብሄራዊ የህዝብና የቤት ቆጠራ ለማካሄድ የቆጠራ ጣቢያዎቹን ከ190 ሺ ወደ 200 ሺ ከፍ እንዲል ማድረጉን የማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ገለጸ።
የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነትና የመረጃ ስርጭት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሳፊ ገመዲ ለኢትዮጵያን ሄራልድ እንደገለጹት፤ ኤጀንሲው ቆጠራውን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ የቆጠራ ካርታ ስራ፣ መጠይቆችን እና የመረጃ ትንተና ስራዎችንም ሰርቷል፡፡ በገጠር 150 ቤተሰብ ያላቸውን በአንድ አካባቢ የሰፈሩ የህዝብ መጠንና በከተማ 200 ቤተሰብ ያላቸውን በአንደ አካባቢ የሰፈረ ህዝብ መጠን ልየታ ተሰርቶ መጠናቀቁን ገልጸው፣ ይህን መረጃ መሰረት በማድረግ ከዚህ ቀደም የነበሩትን 190ሺ የቆጠራ ጣቢያዎች ወደ 200 ሺ ከፍ እንዲሉ ማድረጉን አስታውቀዋል።
ለቆጠራ ጣቢያዎቹ 38 ሺ ተቆጣጣሪዎችና 152 ሺ የተመረጡ የቆጠራ ማእከላት እንደሚኖሩ ጠቅሰው፤ አንድ ተቆጣጣሪ ሶስት የቆጠራ ጣቢያዎችን መቆጣጠር እንደሚችልም አመልክተዋል። ኤጀንሲው ቆጠራውን ለማካሄድ 180ሺ ታብሌት ኮምፒውተሮችን ገዝቷል። ኮምፒውተሮቹም የቆጠራ ካርታ ሶፍትዌር የተገጠመላቸው በመሆኑ ቆጠራው በሚካሄድበት ጊዜ ስህተት ሲፈጠር ስህተቱን በማረም ትክክለኛ መረጃ እንዲኖር ያስችላሉ ብለዋል።
4ኛው ብሄራዊ የህዝብና የቤት ቆጠራ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ ስልጠናዎችን በመስጠትና አዳዲስ ተግባራትን በማከናወን የተሳካ እንዲሆን በማድረግ ከባለፉት መሰል ቆጠራዎች የተሻለ እንደሚሆን ኤጀንሲው ተሰፋ ማድረጉንም አቶ ሳፊ ጠቅሰዋል። የተባበሩት መንግሥታት የስነ ህዝብ ፈንድ ዩኤንኤፍፒኤ /UNFPA/ ይህን ቆጠራ ለማካሄድ ቀዳሚ አጋር በመሆን ከስታትስቲክስ ኤጀንሲው ጋር በቅርበት በመስራት ላይ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሳፊ፣ በዚህም አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆንና የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ሀገሮች ልምድ በመውሰድ ቆጠራው የተሳካ እንዲሆን ከኤጀንሲው ጋር በቅርበት እየሰራ ነው ብለዋል።
ቆጠራው የተሳካ እንዲሁን መንግስት ሃላፊነት ቢኖርበትም፤ ማህበረሰቡ በቆጠራው ወቅት የቤተሰብ አባላቱን በሙሉ በማስቆጠርና ስለቤተሰብ አባላቱ ሙሉ መረጃ በመስጠት ትልቁን ሚና ሊጫወት እንደሚገባ አሳስበዋል ። ምክንያቱም ማህበረሰቡ ትክክለኛውን የቤተሰብ ቁጥርና መረጃ ከሰጠ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የሚሆነው ራሱ መሆኑን አመልክተዋል። ቆጠራው በዚህ ዓመት መካሄድ አለበት። ያለበለዚያ በሀገሪቱ ያሉትን ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኝት ያዳግታል።
ኤጀንሲው ይህን ቆጠራ ሊያካሂድ የነበረው ባለፈው ዓመት ነበር። ፓርላማው በነበረው የሀገሪቱ የፀጥታ ችግር ምክንያት እንዲራዘም ስለተደረገ ነው። 4ኛው ብሄራዊ የህዝብና ቤት ቆጠራ ለሁለት ጊዜ እንደተራዘመ እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው አመት ቆጠራው በ2011 በጀት አመት እንዲካሄድ ማራዘሙን አስታውሰዋል።
ነገር ግን ቆጠራው የሚካሄድበት ቀኑ ተለይቶ ባይታወቅም ኤጀንሲው ቆጠራውን እንደሚያካሂድ ተስፋ አለው ሲሉ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የህዝብና ቤት ቆጠራ በየአስር አመቱ ታካሂዳለች። ቆጠራው ለመንግስት ትልቅ ፋይዳ ያለው ሲሆን፣ መንግስት የህዝብ ቁጥርና ወቅታዊ ሁኔታ በቀላሉ በማወቅ፣ የሚያስፈልገውን መሰረታዊ ልማት በመለየት እንደ ውሃ፣ መብራትና ትምህርት ቤት የመሳሰሉ መሰረታዊ ልማቶችን ለማሟላት ያስችለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
በሰለሞን በየነ