በባሌ ዞን የግብርና ሥራ ውጤታማነት ጎልቶ ከሚታይባቸው አካባቢዎች መካከል በአጋርፋ ወረዳ የምትገኘው የአሊ ቀበሌ አንዷ ነች፡፡ የዚህች መንደር አርሶ አደሮች የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ግኝቶችን ጥቅም ላይ በማዋል የተለያዩ የግብርና ሥራዎችን በአንድ ላይ ያከናውናሉ፡፡ ያርሳሉ፣ ከብት ያረባሉ ፣ያደልባሉ፣ ንብም ያንባሉ፡፡
አርሶ አደር አህመድ ጠይብ ሀጂ ኡመር ከአሊ ቀበሌ ስመጥር አርሶ አደሮች ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚገልጹት በአካባቢው የእንስሳት መኖ ሳርንም ሆነ ንቦች የሚቀስሟቸውን የተለያዩ የአበባ ዓይነቶች መዝራት እምብዛም የተለመደ አይደለም፡፡ የሲናና ግብርና ማዕከል ያስተዋወቃቸውን ‹ዴሾ› እና ‹ሲናር› የተባሉ የሣር አይነቶችን በመዝራት ከብቶችን እያደለቡ ለገበያ ያቀርባሉ፡፡
እንደ ፋሶሊያ የመሳሰሉ አበቦችን በመዝራትም እስከ 26 ቀፎ ንብ ያንባሉ፡፡ በግቢያቸው ውስጥ የዝናብ ውሃ ማቆሪያ ጉድጓድ በመቆፈር በበጋ ወራት ንቦች የሚቀስሙትን አበባና ከብቶቻቸው የሚግጡትን ሳር ያጠጣሉ፡፡ አርሶ አደሩ የግብርና ዘርፎችን በማስፋት ገቢያቸውን አሳድገው ዛሬ የተሻለ ኑሮ መኖር መጀመራቸውን ይናገራሉ:: በአቅራቢያቸው በሚገኝ ከተማ ዘመናዊ ቤት በመሥራት ለልጆቻቸው ምቹ የትምህርት ዕድል እንደፈጠሩም ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ በፊት ከብቶቻቸውን በዘፈቀደ እንደሚያሠማሩ የተናገሩት አርሶ አደሩ አሁን ግን ከሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ባገኙት ድጋፍ ተስማሚ የሳር አይነቶችን በመዝራት የበጋ ወራትን ለከብቶቹ ቀለብ ያለስጋት ያልፉታል፡፡ በርከት ያለ የማር ምርት ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን አሳድገዋል፡፡
እንደ አርሶ አደሩ አባባል የግብርና ሥራ የተለያዩ ጸጋዎች አሉት፡፡ አርሶ አደሩ በእጁ ላይ ያሉ እድሎችን ሁሉ ቢጠቀም ከራሱ የሚተርፍ ጥቅም ያገኛል፡፡ በተለይ ንብ የማነብ ሥራ ከግብርና ሥራዎች ውስጥ በጣም ቀላል ሆኖ ሳለ አብዛኛው አርሶ አደር የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ያለመሆኑ ያስቆጫቸዋል:: በአካባቢያቸው በርካታ ያልተሞከሩ የግብርና ሥራ ዘርፎች እንዳሉ የተናገሩት አርሶ አደሩ ወደፊት በተለያዩ ሥራዎች ላይ በመሰማራት ገቢያቸውን የማሳደግ ዕቅድ ይዘዋል፡፡
አርሶ አደር በያን አብዱርአማን የሲናና ግብርና ማዕከል የምርምር ውጤቶችን ተጠቅመው ትርፋማ የሆኑ አርሶ አደሮችን ማየታቸው ተነሳሽነት ፈጥሮባቸዋል፡፡ ይሁንና በአቅርቦት ማነስ ምክንያት የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን አለመቻላቸውን ይናገራሉ:: ማዕከሉ ለሁሉም አርሶ አደሮች ተደራሽ የመሆን አቅሙን ሊያሳድግ ይገባል ይላሉ፡፡ እርሳቸውም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ አርሶ አደር አህመድ ጠይብ የተለያዩ የግብርና አማራጮችን በመጠቀም ገቢያቸውን ለማሳደግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የአጋርፋ ወረዳ የግብርና ኤክስቴንሺን ሥራ ኃላፊ አቶ አማን አብዱል ቃዲር እንደሚያስረዱት የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል በየጊዜው የሚያስተዋውቃቸውን አዳዲስ ግኝቶች ለአርሶ አደሩ የማስተዋወቅ እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ይሰራል፡፡ እንደ አርሶ አደር አህመድ ጠይብ አይነቶቹ ፈጥነው ወደሥራ ይገባሉ፡፡ አንዳንዶች ግን ጥርጣሬ ያድርባቸዋል ፡፡ በዚህም ሁሉም አርሶ አደር እኩል ተጠቃሚ አልሆነም፡፡ አሁን ግን ውጤቱን ሲያዩ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ በቀጣይ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ አርሶ አደሩ የተለያዩ የሥራ ዘርፎችን ተጠቅሞ ገቢውን እንዲያሳድግም ይሰራል ብለዋል፡፡
የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ መሀመድ በሪሶ እንደሚያስረዱት ማዕከሉ ከሚያ ወጣቸው አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች በተ ጨማሪ አርሶ አደሩ አማራጭ የግብርና ዘርፎችን እንዲፈጥር የሚያስችሉ ዕድሎችን ይፈጥራል፡፡ ከእነዚህም የከብት መኖ ሳር ዝርያን ማቅረብ አንዱ ነው:: በአጠቃላይ በዞኑ ሶስት ወረዳዎች ሰባት ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት በሳር ዝርያዎች ተሸፍኗል:: ይህም አርሶ አደሩ ከእርሻ በተጨማሪ ከብቶችን እያደለበ ለመሸጥ ያስችለዋል፡፡
በመሆኑም ለከብት ገንቢና አቅም ሰጪ የሆኑ እንደሲናር፣ ቬትበርግ፣ አልፋ አልፋ፣ ዴሾን የመሳሰሉ የሳር አይነቶች ከምርምር ማዕከሉ ተለቀው ጥቅም እየሰጡ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚስ ፋፋው እርሻ ምክንያት የግጦሽ መሬት እጥረትን ለመቅረፍ የተለያዩ የሳር አይነቶችን መዝራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የአካባቢው አርሶ አደሮች ንብ ማንባትን የግብርናው አንድ አካል እንዲያደርጉ ጅምር ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ጣፋጭ ፈሳሽ /ኔክታር/ ያላቸው እንደ ፋሶሊያን የመሳሰሉ አበቦችን ለንቦች መኖነት የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ እንዳለና ወደፊትም በሰፊው ለመስራት እንደታቀደ አቶ አህመድ ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2012
ኢያሱ መሰለ