አዲስ አበባ፡- ለአገሪቱ የወጪ ንግድ ዘርፍ ችግሮች አስቸኳይ መፍትሄ መፈለግ እንደሚገባ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የአግሮፕሮሰሲንግና ፋርማሲቲካል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረእየሱስ እንደተናገሩት፣ የአገሪቱ የወጪ ንግድ አፈፃፀም እየቀነሰ በመምጣቱና ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ እድገት እየተመዘገበበት ባለመሆኑ በአገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው።በመሆኑም ለችግሩ ዘላቂ የሆነ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይገባል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ የዘርፉ ችግሮች ከዓመታት በፊት ጀምረው የተከማቹ በመሆናቸው ዝርዝር ጥናትና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ይፈልጋሉ።የችግሮቹን ምንጭንና መፍትሄ የሚያሳይ ግልፅ አቅጣጫ ሊኖር ይገባል።ከዚህ አንፃር ሚኒስቴሩ ጥናት በማካሄድ የዘርፉን ዋነኛ ችግሮች ለይቷል።
በጥናቱ ከተለዩት የማምረቻው ዘርፍ የወጪ ንግድ ችግሮች መካከል የውጭ ምንዛሪና የሥራ ማስኬጃ ብድር አቅርቦት ውስንነት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ የወደብ አገልግሎት ክፍያ መወደድ፣ የሠራተኞች የክህሎትና የአመለካከት ችግሮችና የክልሎች ሚና ደካማነት እንዲሁም የሎጂስቲክስና የጉምሩክ አገልግሎት ችግሮች ዋነኞቹ ናቸው።
በእርዳታና በብድር የሚገኙ የውጭ ምንዛሪዎች ቀጣይና አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጮች ባለመሆናቸው ለወጪ ንግድ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።ባለፉት 10 ዓመታት የአገሪቱ የንግድ ጉድለት እየሰፋ መምጣቱን ጠቁመው፣ በግብርና ምርቶች ላይ የተወሰነውን የወጪ ንግድ በጥራትና በዓይነት ማብዛት እንደሚገባም ገልጸዋል።ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ለማቃለል በአገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሐ ግብር በኩል እንደመፍትሄ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል›› ብለዋል።
‹‹እንደ አገር አሁን ባለው የወጪ ንግድ አፈፃፀም መቀጠል አንችልም›› ያሉት አቶ ተካ፣ ችግሩ እጅግ አደገኛ በመሆኑ ዘርፉ የሚመራበት አቅጣጫ በማዘጋጀትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2012
አንተነህ ቸሬ