• ተፈጥሯዊ የውሃ ፍሰት ይጠበቅ የሚለው ሃሳብ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት የለውም
አዲስ አበባ:- ኢትዮጵያ በድርቅ ወቅት የግድቡ የውሃ መጠን ከ35 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በታች ካልሆነ ውሃ እንደማትለቀ አቋሟን ገልጻለች። ተፈጥሯዊ የውሃ ፍሰት ይጠበቅ የሚለው ሃሳብ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት እንደሌለው ተጠቆመ።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ፤የህዳሴውን ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ በተመለከተ ሱዳን ካርቱም የተካሄደውን የሦስትዮሽ ውይይትን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፤ በውይይቱ ወቅት ግብጽ በድርቅ ወቅት የህዳሴ ግድቡ የውሃ መጠን 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ሲደርስ ኢትዮጵያ ውሃ እንድትለቅ የሚል ሀሳብ ብታነሳም፤ ኢትዮጵያ ከ35 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በታች እስካልሆነ ድረስ ውሃ አትለቅም።
ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ በካርቱም በተደረገው ድርድር የግድቡን ሙሌት በተመለከተ የመጨረሻውን ውይይት ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ በዚህም ግድቡ በመሰረታዊነት ከአራት እስከ ሰባት ዓመት እንዲሞላ በኢትዮጵያ በኩል ሰንጠረዠ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በግብጽ በኩል በአምስት ደረጃዎች እንዲሞላ የሚል ሰንጠረዠ የሚያሳይ በመሆኑ በውሃ ሙሊቱ ላይ ተመሳሳይ አቋም በመኖሩ የጋራ ስምምነት አለ።
ባለፉት ዓመታት በውሃ የመሙላት ጊዜ ድርቅ እስካልተከሰተ ድረስ ከአራት እስከ ሰባት ዓመት ውስጥ እንዲሞላ የሚደረግ ሲሆን፤ የድርቅ ትርጓሜ ላይ በተነጋገሩበት ወቅት፥ የድርቅ ትርጓሜ ኢትዮጵያ ከ35 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በታች ውሃ ሲፈስ ነው ስትል፣ ግብጽ ደግሞ ከ40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በታች ይሁን ማለታቸውን ተከትሎ ሳይስማሙ እንደቀሩ አመልክተዋል።
ሌላው ግብፅ ያቀረበችው አዲስ ሃሳብ የአባይ ወንዝ ተፈጥሯዊ ፍሰቱ ይጠበቅ የሚል መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ይህንን ሀሳብ እንዳልተቀበለች፤ ተፈጥሯዊ ፍሰቱ ከተጠበቀ የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራትን የመጠቀም መብት ይገታል የሚል አመክንዮ በማቅረቧም ግብጽም ላስብበት እንዳለች አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ መደራደር የሚቻለው ወደ ግድቡ በገባው የውሃ መጠን አማካኝ ወደ ተፋሰሱ አገራት የሚፍሰውን የውሃ ፍሰት ሚዛኑን ጠብቆ እንዲፈስ ማድረግ ላይ ነው። ተፈጥሯዊ ፍሰት መጠበቅ ማለት ውሃው ጥቅም ላይ ሳይውል እንዲፈስ የሚያስገድድ በመሆኑ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት የለውም፡፡
ኢትዮጵያ ከኃይል ማመንጨት በተጨማሪ በአካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች ንጹህ ውሃ እንዲያገኙ፤ አነስተኛ መስኖዎች ሥራ ላይ እንዲውሉ፤ ለቱሪዝም መስህብነትን ጥቅም ላይ ለማዋል ስለምትፈልግ፣ ተፈጥሯዊ ፍሰት ይጠበቅ ማለት የኢትዮጵያን ውሃ የመጠቀም መብት የሚገድብ ስለሆነ በፍጹም መነሳት እንደሌለበት በግልጽ ቋንቋ አስረድታለች። ቀጣዩ ውይይት እአአ ጥር 8 እና 9/2020 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2012
ሶሎሞን በየነ