ሥራውን ሲጀምሩ የቤተሠባቸውን የዕለት ጉርስ ለመሸፈን ቢሆንም በቆይታ ግን በርካቶች መንግሥት ባመቻቸላቸው ዕድል ተለውጠው መመልከታቸው ወኔን ፈጥሮላቸዋል። በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ችግራቸውን ከማቃለል ባሻገር የተለያዩ ድጋፎች ተጠቅመው ከራሳቸው አልፈው አገራቸው በሀብቷ በአግባቡ ባለመጠቀሟ በየዓመቱ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ በምታወጣበት የእንጨት ምርት ሥራ ላይ ለመሠማራትም ይወስናሉ።
በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ነዋሪ አቶ ኬሮ መላኩ ተመሳሳይ ሀሳብ ካነገቡ ወዳጆቻቸው ጋር ልዩ እንጨትና ብረታ ብረት ሥራ ማህበርን ይመሠርታሉ። የብድርና ሌሎች ድጋፎች እንደተደረገላቸውና ለሥራቸው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ለማሟላት መንግሥት በፈጠረላቸው ትስስር ከደቡብ ካፒታልና ፋይናንስ ተቋም 400 ሺህ ብር በሚጠጋ ገንዘብ ማሽን እንደወሰዱም ያስታውሳሉ። የማሽን ድጋፉም የእነርሱን ማህበር ጨምሮ ለሌሎች 18 ማህበራት የተደረገ ነበር። ዳሩ ግን ነገሮች አልጋ በአልጋ አልሆኑላቸውም።
በብድር የወሰዱት ማሽን ምላጭ ሣምንት ሳይሞላው በመበጠሱ አዲስ አበባ ድረስ በመጓዝ በዘጠኝ ሺህ አምስት መቶ ብር ምላጭ ለመግዛት እንደተገደዱ ነው የተናገሩት። በርካታ ኪሎ ሜትሮችን እያቋረጡ የሚገዙት ምላጭም የአምስት ሺህ ብር ሥራ እንኳ ሳይሠራ ስለሚበጠስ ለችግራቸው ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጣቸው አልቻለም። ይልቁንም ለትርፍ ያሰቡት ሥራቸው ይብስ ብሎ ከኪሳቸው ያላቸውንም ይጨርስና ብድራቸውን መክፈል አቅቷቸዋል። ችግሩ ቤተሠባቸውንም ላላሰቡት ችግር እየዳረገ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ዳግም ወደ ተረጂነት እንደሚሸጋገሩ ተናግረዋል።
የእንጨት ሥራው በአቅራቢያቸው የሚገኝን ጥሬ ዕቃ ወደ ምርት መቀየር በመሆኑ በቀን እስከ ሁለት ሺህ ብር ይሠሩ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የማሽኑ ተጠቃሚና በክልሉ በወላይታ ቦዲቲ ከተማ ላይ አካል የእንጨትና ብረታ ብረት አምራች ማህበር ተወካይ አቶ ፍቃዱ ደበበ ናቸው።ይሁን እንጂ በምላጩ ችግር ሳቢያ በካሬ የሚከፍሉበትን የማምረቻና መሸጫ ሼድ ክፍያ እንኳ መሸፈን አቅቷቸዋል።
ማሽኑን ሲረከቡ ሁለት ምላጭ ቢሰጣቸውም ብዙም ሳይጠቀሙበት እየተበጠሰ አስቸግሯቸዋል። ለዳግም ሥራ ለማዋል ቢበየድም ሊሠሩበት ግን አልቻሉም።ማሽኑ ካለምላጭ ስለማይሠራ በሥራ ከሚያሳልፉት ይልቅ ያለሥራ የሚያሳልፉት ጊዜ የበለጠ እንዲሆን አድርጎታል። ችግሩ ዕዳቸውን መመለስ እንዳይችሉ ከማድረጉ በተጨማሪ ሥራውን ሲጀምሩ ራሳቸውንና ማህበራቸውን ለመለወጥ የሰነቁትን ተስፋ እንዳመከነውም ተናግረዋል።
የፈጠራ ባለሙያ አቶ ሰለሞን ሰብስቤ፤ ኢትዮጵያ እንጨት ማምረት እየቻለችና ዓመቱን ሙሉ ለዚህ ምቹና ተስማሚ የአየር ፀባይ እያላት ከምዕራባውያኑ ለአንድ ሜትር ኪዩብ ጣውላ በትንሹ 500 ዶላር ወጪ አድርጋ እንደምትገዛ ጠቁመዋል። አገሪቱ ያላትን ሰፊ ሀብት መጠቀም ባለመቻሏ ግንዱ ያለ ጥቅም በየመንገዱ ወድቆ አገሪቱ በሌላት የውጭ ምንዛሪ ደግሞ በከፍተኛ ወጪ ጣውላ ታስገባለች።
በሌላ በኩል በክልሉ እንኳ ከተደራጁ ኢንተርፕራይዞች መካከል አንዱ ኢንተርፕራይዝ በቀን ውስጥ 20 ሜትር ኪዩብ ጣውላ ቢሰነጥቅ በአጠቃላይ ማሽኑ የተሰጣቸው 18 ኢንተርፕራይዞች 360 ሜትር ኪዩብ እንጨት መሰንጠቅ ይችላሉ። በዚህ መልኩ በዓመት ውስጥ በትንሹ 300 ቀናት ቢሠራ እንኳ 108 ሺህ ሜትር ኪዩብ ጣውላ ይቀርባል።
ይህም አገሪቱ በዓመት የምታወጣውን 54 ሚሊዮን ዶላር ማስቀረት ይቻላል። መንግሥት ለሥራ ዕድል ፈጠራ በሰጠው ልዩ ትኩረት የደቡብ ሊዝ ፋይናንስ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በተለያዩ ዞኖች በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ 18 ኢንተርፕራይዞች የግንድ መሰንጠቂያ ማሽኖችን ገዝቶ ቢያስተላልፍም ኢንተርፕራይዞቹ ማሽኖቹን ከተረከቡ በኋላ ምንም መሥራት እንዳልቻሉ መስማታቸውን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።
በዚህም ተቋሙ በርካታ ገንዘብ ወጪ አድርጎ ያስገባቸው ማሽኖች የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ባለማስገኘታቸው ተጠቃሚዎቹ ችግር ውስጥ ገብተዋል። ምላጩ ለአንድ ጊዜ ከሠራ በኋላ በድጋሚ የማያገለግል በመሆኑ ለወጪ ተዳርገዋል። ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር ባለበት እንዲሁም አገሪቱ በዘርፉ የምታወጣውን ወጪ ትርጉም ባለው ደረጃ ይቀንሳሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው ኢንተርፕራይዞች የሚጋጥማቸውን ችግር ተከታትሎ መፍትሔ ማበጀት ካልተቻለ አዳጋች በመሆኑ ለፈጠራ አነሳስቷቸዋል።
ለመፍትሔው በጋራ መሥራቱ አስፈላጊ በመሆኑ የአገሪቱን እንጨት ሊሰነጥቅ፣ የአየር ንብረቱን ሊቋቋም የሚችልና ከወጪ አንፃርም ተጠቃሚዎቹ በቀላሉ መግዛት የሚችሉትን ቴክኖሎጂ ማቅረባቸውን ገልፀዋል። የፈጠራ ባለሙያው፤ ከዚህ በኋላም ለኢንተርፕራይዞቹ በምርምር ድጋፍ እየሠጡ እንደሚሠሩ፣ ምላጩ ሲበጠስ የሚቀጥሉበት ማሽን እንዳስገቡ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ እንዲገለገሉበት መሞረጃ ማስገባታቸውን አስታውቀዋል። ቴክኖሎጂውንም 50 በመቶ ቅናሽ በማድረግ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
የአገሪቱ እንጨት ተፈጥሯዊ ይዘቱን የጠበቀ፣ የጥራት ደረጃው የተሻለ እንዲሁም ለብዙ ዓመታት አገልግሎት ላይ መዋል የሚችል ቢሆንም ለመንገድ ሥራ የሚመነጠረው እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የሚወድቁ ግንዶችን በጥቅም ላይ ማዋል ይገባል። ይህን በማድረግ ምርቱ ያለውን ጠቀሜታ ሠዎች ሲገነዘቡም ዋጋ እንደሚያወጣ ስለሚታወቅ በድጋሚ ሊተከል ብሎም ጥበቃ እንዲደረግለት ያስችላል።ለዚህም ሁሉም በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በደቡብ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ኩባንያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ምህረቱ ዮሴፍ እንደሚሉት፤ በእንጨት መሰንጠቂያ ማሽኑ ላይ የምላጭ መበጠስ ችግር እንዳጋጠማቸው ኢንተርፕራይዞቹ በተደጋጋሚ ቅሬታዎችን አቅርበዋል። በተያያዘ ምላጩን በአቅራቢያቸው በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ይቸገራሉ።በወቅቱ አንዱ ማሽን 350 ሺህ ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት በብድር የተላለፈ ነው።
ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ከተቻለ መሰንጠቂያው ሥራውን ሳያቋርጥ ማከናወን ይችላል። ኢንተርፕራይዞቹም የምላጭ ችግር ሲፈታላቸው ብድሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠናቅቁ ያቀርባሉ። ለዚህም የፈጠራ ባለሙያው ያቀረቡት ቴክኖሎጂ ችግሩን በሰፊው እንደሚያቃልል ይታመናል። የኢንተርፕራይዞች ችግር መፍትሔ ማግኘቱም አገሪቱ ከዚህ ጋር ተያይዞ የምታወጣውን ወጪ ይቀንሳል ተብሎም ይጠበቃል።
አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ገንዘብ የሚቀይር ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ ለከፍተኛ ወጪ ተዳርጋለች። በመሆኑም ኢንተርፕራይዞቹ ደረጃ በደረጃው ጤታማ ሲሆኑ ከውጭ የሚገቡትን የጣውላ ምርቶች በአገር ውስጥ ማምረት ያስችላቸዋል። ይህንንም ከውጤት ለማብቃት ኢንተርፕራይዞቹ የሚያጋጥማቸው ችግር ላይ በቅርበት እየተወያዩ የመፍትሔ ሀሳቦችን እያቀረቡ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እንደሚሠሩ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2012
ፍዮሪተወልደ