አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ዓርብ ወደ ህዋ ያመጠቀቻት ሳተላይት በተሳካ ሁኔታ ምህዋር ላይ ማረፏና በአሁኑ ሰዓትም በመልካም ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በትናንትናው እለት የሳተላይቷን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ በኢንስቲትዩቱ አዳራሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ኢትዮጵያ ከቻይና መንግሥት ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ ያመጠቀቻትና 70 ኪሎ ግራም ክብደት ያላት ሳተላይት በአስተማማኝ ደህንነት ላይ የምትገኝ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም የሚጠበቅባትን የሙከራ ተግባር በመወጣት ላይ ትገኛለች።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት፣ ከቻይና የተለቀቀችው ሳተላይት በአሁኑ ሰዓት ያለችው በሙከራ ተግባር ላይ ሲሆን ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ወደ ሥራ ትገባለች።
እንደ ዶክተር ሰለሞን ማብራሪያ ሳተላይቷ የተሰራችውና እንድትመጥቅ የተደረገው በአላማ (ሚሽን)፤ በተለይም ለመሬት ምልከታ ተግባር ነው። በመሆኑም የሙከራ ጊዜዋን እንደጨረሰች በቀጥታ ወደ እዚሁ ተግባሯ ትሰማራለች።
ሳተላይቷ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት የህዋ ላይ እድሜ (Operational life time) እንዲኖራት ታስቦ ነው ዲዛይን የተደረገችው የሚሉት ዶክተሩ ፤የህዋ ላይ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ አስቸጋሪ በመሆኑ ምክንያት ያንን መቋቋም የምትችልበት ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ ነው የእድሜዋ ጉዳይ እንዲወሰን የተደረገው ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት በማን ነው የምትመራው፤ ክትትልና ቁጥጥሩንስ ማን ነው እያደረገ የሚገኘው? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም ሲመልሱ፤ይህን እያደረገ ያለው የቻይና መንግሥት ነው። ይህ የሆነበትም ምክንያት የሰራው እሱ ስለሆነ አጠቃላይ ጤንነቷንና ብቃቷን በማረጋገጥ ማስረከብ አለበት።
በዓለም አቀፍ ደረጃም መመዝገብ አለበት። ከቻይና መንግሥት ከተረከብን፣ ጉዳዩ ከሚመለከተው ዓለም አቀፍ ተቋም ፈቃድ ከተሰጠና እውቅና ካገኘን በኋላ ግን ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ከዚሁ ከእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ ማእከል ነው የሚመራው ብለዋል። ርክክቡ አይፈፀም እንጂ በአሁኑ ሰዓት በማእከላችን በቀን አራት ጊዜ መረጃ እየተቀበልን በመልካም ሁኔታ ላይ መገኘቷን እያረጋገጡ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ዶክተር ሰሎሞን ማብራሪያ ከሆነ በአሁኑ ሰዓት ሳተላይትን የማስተዳደር አቅምን በተመለከተ ኢትዮጵያ ችግር የለባትም። ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ማስተዳደርና ማስኬድ የሚችል አቅም አላት። የህዋ ሳይንስ ምንም አይነት ስህተት እንዲኖር የማይገባ (0 error) ከመሆኑ አኳያም ምንም ችግር የለም። የባለሙያ አቅም አለ።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የአጭር፣ መካከለኛና ረጅም ጊዜ እቅድ አውጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ፤ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የባለሙያዎችን ቁጥር 500፤ በሚቀጥሉት 15 ዓመታት የሳተላይቶችን ቁጥር 10 ለማድረስ እየሰራ መሆኑንም ከተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2012
ግርማ መንግሥቴ